Sunday, June 29, 2014

የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

June29/2014
ኢ.ኤም.ኤፍ – በድረ ገጾች ላይ ሃሳባቸውን በጽሁፍ ሲገልጹ የነበሩ፤ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ማህሌት፣ ኣቤልና በፈቃዱ በተሰጣቸው ቀጠሮ መሰረት ዛሬ እሁድ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ሆኖም እንደተለመደው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ለተጨማሪ ምርመራ እንደገና ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል። በዚህ አይነት የፍርድ ቤት ምልልስ ወጣት ጦማሪዎቹ ሁለት ወራትን አስቆጥረዋል።ከጦምሪዎቹ መካከል አቤል፣ ማህሌትና በፍቃዱ በፍርድ ቤቱ የተገኙት ከጠበቃቸው ኣመሃ መኮንን ጋር ነበር።
የዛሬውን ውሎ ከዘገቡት ድረ ገጾች መካከል ኢትዮ ሪፈረንስ እንዲህ በማለት ዘገባውን አቅርቧል። ጠበቃ አምሃ እንዳሉት ፖሊስ እንደለመደው 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ዳኛዋ የጠበቆቹን አስተያየት ሳትጠይቅ 14 ቀን ጦማሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ ፈቅዳለች።በዚህም መሰረት ቀጣዩ ቀጠሮ ለሃምሌ 7 ተብሎኣል ።በዚያች በነበረችው የ ኣስር ደቂቃ የችሎት ጊዜ ጦማሪ በፈቃዱ ዘሃይሉ ”በፖሊሶች ሃሰተኛ ቃል አንድሰጥ ማሰገደድ ተደርጎብኛል” ሲል ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱ ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት የጦማሪዎቹን የፍርድ ሁኔታ ለመከታተል ከ300 በላይ ሰዎች በስፍራው የነበሩ ቢሆንም የኣራዳን ግቢና ኣካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ፖሊሶች ሲያስገድዷቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ የታሰረው ዮናታን
ዛሬ የታሰረው ዮናታን
ወጣት ምኞት መኮንን
ወጣት ምኞት መኮንን
ከአነዚህም መሃል፣ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊን ዮናታን ተስፋየን (ፎቶ ይመልከቱ) ”ፎቶ ስታነሳ ነበር” በማለት ወደ አስር ቤት አንደወሰዱት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።በተመሳሳይ መልኩ በስፍራው  የነበረች  ወጣት ምኞት መኮንንም (ፎቶዋን ይመልከቱ) ”ፎቶ ኣንስተሻል” በሚል በፍርድ ቤት ፊት ለፊት በፖሊሶች ተደብድባ ወደ አስር ቤት መወሰዷ ተመስክሯል።
የጦማሪያኑን የፍርድ ውሎ የሚከታተለው ሰው ዛሬም እንደወትሮው በጠዋት ነው የተገኘው፡፡ አራት ሰዓት ካለፈ በኋላ የጦማሪያኑ ጠበቃ ‹‹መዝገብ ቤቷ ስለሌለች ነገ ከሰዓት ተብሏል›› ብለው ሲነግሩን በርካታ ህዝብ በተገኘበት አንዲት መዝገብ ቤት በመቅረቷ ብቻ የፍርድ ውሎው እንዲራዘም መደረጉ ገርሞን ስለጉዳዩ እያወራን ለጥቂት ደቂቃዎች ግቢው ውስጥ ቆየን፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እየመጡ ነው ተባለ፡፡
የውሎው ትዕይንት እዚህ ላይ ነው የተጀመረው፡፡
“ያለፈቃድ መሬቱንም ቢሆን ፎቶ ማንሳት አይቻልም” በማለት ፖሊስ ህዝቡን ያንገላታ እንደነበር የገለጸው ደግሞ ‘ፍሪደም ፎር ኢትዮጵያ’ የተባለው ድረ ገጽ ነበር። ዝርዝር ዘገባውን እንዲህ በማለት አቅርቧል።
ሶስቱም ጦማሪያን ሲመጡ ህዝቡ በጭብጨባ ተቀበላቸው፡፡ በድንገት እዚህ እዚያ የሚራወጡት ፖሊሶች ወደተሰበሰበው ሰው እየሮጡ በመምጣት የሰማያዊ ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ አባል የሆነችውን ምኞት መኮንንን ‹‹ፎቶ ግራፍ አንስተሻል፡፡›› በሚል ማንገላላት ጀመሩ፡፡ በኃይል እየጎተቱ ሲወስዷትም ዮናታን ተስፋዬ ‹‹እኔን ውሰዱኝ›› ብሎ ምኞትን በኃይል እየገፈተሩ የሚወስዱት ፖሊሶች መሃል ገባ፡፡ ፖሊስ ግን እሱንም ማንገላላት ጀመረ፡፡ እሱንም አብረው ወሰዱት፡፡ ምኞትና ዮናታን ጦማሪያኑን ተከትለው ችሎቱ ወደሚገኝበት ቦታ ከተወሰዱ በኋላ ፖሊሶቹ ህዝቡ እንዲበተን ማስፈራራት ጀመሩ፡፡
ፖሊሶቹ ከሚመጡበት በኩል የርዕዮት ዓለሙ አባት ጠበቃ አለሙ፣ እህቷ እስከዳር አለሙ፣ ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ፣ 6 ያህል የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አባላትና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ‹‹ወዴት ነው የምንሄደው?›› በሚል እንደማይወጡ አሳወቁ፡፡ ፖሊሶቹ ‹‹ታዘነ ነው፡፡ ትወጡ እንደሆነ ውጡ!›› እያሉ ማስፈራራት ጀመሩ፡፡ ከፊት ያሉት ሰዎች ‹‹ችሎት መከታተል መብታችን ነው!›› ብለው አንወጣም ሲሏቸው እነ ምኞት ላይ የተወሰደውን እርምጃ ትክክለኛነት ለመግለጽ ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ በተለይ አንዱ ፖሊስ ‹‹ያለ ፈቃድ ፎቶ ማንሳት አይቻልም፡፡ ሳይፈቀድ መሬቱንም ቢሆን ፎቶ ማንሳት አይቻልም›› ያለበት ሁሉንም ያስገረመ ነበር፡፡ በዚህ ፖሊስ አባባል የተሰበሰበው ሁሉ እያረረም ቢሆን ፈገግ ብሎበታል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ቃል አቀባይ በበኩሉ ይህንን መልዕክት አስተላልፏል። በዛሬው በአራዳ ችሎት ከተገኙት የሰማዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች መሀከል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆነው ዮናታን ተሰፋዬን እና የሴቶች ጉዳይ አባል የሆነችውን ምኞት መኮንን “ፎቶ አንስታችኋል ለጥያቄ እንፍልጋችኻለን” በማለት የውስዷቸው ሲሆን በአሁኑ ሰአት የት እንዳሉ ስንጠይቅ ማእከላዊ “ኑ፡ የሚል መልስ ሰጥተውናል፤ ብሏል።
የጦማርያኑን ሁኔታ በቅርብ ሲከታተሉ ከነበሩት መካከል ጋዜጠኛ ደረጀ ሃብተወልድ “ሁሉም ያው ናቸው” በማለት ትዝብቱን አስፍሯል። የጋዜጠኛ ደረጀን አስተያየት ከዚህ ቀጥሎ አቅርበነዋል።
<<በፖሊስ 28 ቀን ተጨማሪ ቀጠሮ ተጠይቆ 14 ቀን ብቻ ተፈቀደ፤ ዻኛዋ አቃቤ ህግን አስጠነቀቁ…” ምናምን የሚለው ነገር ብዙውን ጊዜ ድራማ ነው። ፍትሐዊ ዻኝነት እንዳለ ለማስመሰል የሚደረግ የተቀናጀ ጨዋታ ነው። ለህሊናውና ለሙያው ያደረ እውነተኛ ዳኛ ቢኖርማ ብርቱካን ሚዴቅሳ- ስዬን እንዳሰናበተቻችው ፦<<እኚህን ልጆች ዋስትና የሚያስከለክል ቀርቶ አንድም ቀን እስር ቤት የሚያሳድር ክስ አላገኘሁባቸውም” ብሎ ቢያንስ በዋስ ያሰናብታቸው ነበር። ይህን ስል አንዳንድ ደፋር ወሳኔ የሚሰጡ፣ለሙያቸው እና ለህሊናቸው ያደሩ ዳኞች የሉም እያልኩ አይደለም። ለምሳሌ የጦማርያኑ ክስ እንደተጀመረ ጉዳዩን ይዘውት የነበሩትንና በጦማርያኑ ላይ የተመሰረተውን የሽብርተኝነት ክስ ያልተቀበሉትን ዳኛ መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም አልፎ አልፎ እንደዛ ያሉ ደፋር ዳኞች ብቅ ሲሉ ከሚያስችሉት ችሎት ተነስተው በሌሎች እንዲተኩ ይደረጋሉ። ብዙዎቹ ግን <<አስፈቅደው>>ለማስመሰል ደፈር ያለ ነገር እየተናገሩ በ አጉል ተስፋ ንጹሀንን የሚያሹ፣የሚቀጡና በፍትህ ስም እኩይ ተልእኮ የሚፈጽሙ ሆዳሞች ናቸው።
አንዳንዴማ ልክ ቁጪ በሉዎች ሊሰርቁ ሲሉ እንደሚፈጥሩት የውሸት አምባጉዋሮ፤ ዳኞችና አቃቤ ህጎች እርስበርስ የውሸት እሰጥ እገባ በመግባት ድራማ እስከመሥራት ይደርሳሉ።ያኔ ልጁ፣እናቱ፣አባቱ፣ወዳጁ… የታሰረበት ፍትሕ የተጠማ ወገን ከጭንቀቱ ማየል የተነሳ የሰማው እሰጥ እገባ እውነት እየመሰለው <<ዳኛው እንዲህ አሉ፣ አቃቤ ህግን ገሰጹ፣ማረሚያ ቤትን አስጠነቀቁ …ፖሊስ ይህን ያህል ቀን ተጨማሪ ቀጠሮ ጠይቆ ይህን ያህል ብቻ ፈቀዱ..” እያለ ትንሽ ተስፋ ያደርጋል።
እውነታው ግን ሌላ ነው። የችሎት ሂደቱ የሚሄድበትም ሆነ ተከሳሾች የሚቀጡበት ወሳኔ ከመጋረጃ ጀርባ በቀጭን ሽቦ የሚመጣ እንጂ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ የሚወጣ አይደለም። አዎ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ምንም ተስፋ የለውም-ምንም! እዛ ፍርድ ቤት የሚደረገው ነገር ሁሉ ቴአትር ነው። ጉዳዩን እያስቻሉ ያሉት ዳኞች የድርሰቱ መሪ ተዋናይ ናቸው። ለህሊናቸው ያደሩ እውነተኛ ዳኞች ንጹሀን አንድ ቀንም እንዲታሰሩ አይፈቅዱም። የእውነተኛ ዳኞች መርህ፦” አንድ ንጹህ ሰው ያለጥፋቱ ከሚታሰር፤ እልፍ ተጠርጣሪዎች ቢያመልጡ ይሻላል” የሚል ነው። እውነተኛ ዳኞች በሙያቸውና በህሊናቸው የሚመሩ እንጂ፤ በባለስልጣናት ትእዛዝ የሚሽከረከሩ አይደሉም።
እና…እኒህኞቹ ማለትም፣ 28 ቀን ቀጠሮ ሲጠየቅ- 14 ቀን እያሉ፣ ተክሳሾች በማረሚያ ቤት ተደበደብን ሲሉ ደብዳቢውን በመቅጣት ፋንታ ፦” ሁለተኛ እንዲህ ያለ ነገር እንዳይደገም…” እያሉ የሚቀልዱት ዳኞች ከዐቃቤ ህጎቹና ከባለስልጣናቱ የተለዩ አይደሉም። እንደውም ከስርአቱ ቁንጮዎችና ከዐቃቤ ህጎቹ ባልተናነሰ ሁኔታ በህግም፣በታሪክም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው፤ ንጹሀን የሚንገላቱበትን የትእዛዝ(የድርሰት) ፍትህ በመተወን እያስፈጸሙ ያሉት እንዲህ ያሉ አስመሳይ ዳኞች ናቸው።
ድሮ ሀገሬው በጉቦ ተቸግሮ ፍትሕ ቢያጣ ጊዜ፦
የጅብ ሊቀ-መንበር፣የዝንጀሮ ዳኛ፣ የጦጣ ጸሀፊ፣
ሁሉም ሌቦች ናቸው፣ ዘራፊ ቀጣፊ>> ብሎ ነበር። አዎ፣ሁሉም ያው ናቸው።

No comments: