Friday, June 13, 2014

ከህወሀት/ኢህአዴግ ጓዳ በሀብታሙ አያሌው ላይ የተወረወረች ቀስት

June13/2014
ከዘላለም ደበበ

ይህን ፅሁፍ በሎሚ መፅሄት ላይ ባለፈው ሳምንት አወጣሁት፡፡ መፅሄቱ ላልደረሳችሁ ይኸው እዚህ ለጠፍኩት፡፡
በቅድሚያ እንኳን ወታደራዊ አምባገነኖች ተደምስሰው ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› አምባገነኖች ለተተኩበት የግምቦት 20 በአል አደረሳችሁ፡፡ ዛሬ ዝምታ ሲበዛ ፍርሀት፣ ውሸት ደግሞ ሲደጋገም እውነት ይሆናልና የማውቀውንና የተሰማኝን ለአምባቢም ግልፅ ሊሆንለት የሚገባ ጉዳይን በወፍ በረር ላስቃኝ ወደድኩ፡፡

ለፅሁፌ መነሻ የሆነኝ ሎሚ መፅሄት አቤል ኤፍሬም በተባለ ግለሰብ የቀረበውንና መፅሄቱ ይዞት የወጣው ፅሁፍ ነው፡፡ ፅሁፉም በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ላይ ያነጣጠረ ግልፅ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ እኔም ይህንን ፅሁፍ ያዘጋጀሁት የአቶ ሀብታሙ ተሟጋች ሆኜ ሳይሆን እውነታው ግን በፅሁፉ ከቀረበው ጋር ፍፁም የተለያየ ስለሆነ እና የፅሁፉ ‹‹ሞቲቭ›› አላማ ስም በማጉደፍ አምባገነኑ ስርዓት እንዲቀጥል ማስቻል ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ከህወሃት/ ኢህአዴግ መንደር ወደ ወጣቱ ፖለቲከኛ የተወረወረች ትንሽ ቀስት መሆኗን መጠቆም ስለሚገባ ነው፡፡

በፅሁፉ ላይ በኢህአዴግ ስልጣን እንደነበራቸው ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ ነው በማለት ለመጠቃቀስ ተሞክሯል፡፡ ነገርግን ምነው እነዚህን ዘለላችኋቸው ሌሎቹ ስልጣኖቹ እነዚህ ነበሩ በትምህርት ቢሮ የትምህርት ካውንስል ቦርድ አባል፣ የመገናኛ ብዙሀን ቦርድ አባል፣ የአፍሪካ እርስ በእርስ መገማገሚያ አህጉራዊ ገምጋሚ ምክር ቤት አባል፣ የወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የጃልሜዳ ስፖርት ማእከል የቦርድ አባል፣ የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያ ቢሮ ቦርድ አባል ሌላም ሌላም እንደነበሩስ መረጃው የለዎትም? እሳቸው ግን እነዚህን ሁሉ ኃላፊነት እንደነበራቸው በቃለ መጠይቃቸው ወቅት ገልፀዋል ታዲያስ ይህንን ሁሉ ጥለው የወጡ ጥቂቶች ብቻ ስለሆኑ ብትረበሹ አይደንቅም፡፡ እርግጥ ነው ሀብታሙ ኢህአዴግ ቤት ነበር፡፡ ይህንንም ሲክድ ሰምቸ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ፈንጅ አምካኝ ስላልነበረ ኢህአዴግ የሚከተለው መስመር ለህዝብ እንደማይጠቅም ተሎ በመማር ለሁለት አመታት የዘለቀውን ኢህአዴጋዊ ጋብቻ ለመቅደድ ፈጥኖ መወሰኑ ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስወቅሰው ባልተገባ ነበር፡፡

እዚህች ጋር አንድ ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ አቶ ሀብታሙ አያሌው ራሱን ከኢህአዴግ አባልነቱ ያገለለው ከምርጫ 2002 ማግስት ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ሀገር ውስጥ በሚታተሙ ሁሉም ሊባል በሚቻል መልኩ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ እንዲሁ ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎችም ጭምር ከስርአቱ እንዴትና በምን አይነት ሂደት እንደወጣ ከቃለ መጠይቆቹ ተረድተናል፡፡ ልብ በሉ አቶ ሀብታሙ ላይ በቅድሚያ የተጀመረው ዘመቻ እጅግ በጣም የተቀነባበር ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም. አቶ ሀብታሙ በግልፅ መልቀቂያ አስገብተው ከፓርቲው ከለቀቁ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለትምህርት ከሄዱ በኋላ በሀገር ውስጥ ያሉት የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጭንቀት ላይ ወደቁ፡፡ የጭንቀታቸውም መንስኤ ከሀገር ከወጣ በኋላ ለኢሳትና ለተለያዩ ሚድያዎች ጉዳችንን ያዝረከርክብናል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ትልቅ ኪሳራ ነው ምክንያቱም የሀገሪቱ የወጣቶች ፎረም ሰብሳቢ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ስልጣን እና ጥቅማ ጥቅም ሰጥተውት ጓዳቸው ድረስ ገብቶ የወደፊቱ የግፍ መሀንዲስ እንዲሆን ከፍ ከፍ ያደረጉት ሰው ድንገት ባላሰቡት ሰዓት ከድርጅቱ ለቅቄያለሁ ብሎ ወደ ውጭ ሀገር ሲሄድ መደናገጣቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ደንግጠውም ግን አልቀሩም በአቤል ኤፍሬም አይነት ጥላሸት መቀባት በሚችሉ ግለሰቦች አማካኝነት አንድ ነገር ጀመሩ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካሄዱ:: ሀብታሙ በ2010 እ.ኤ.አ. በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የአለም ዋንጫ በማስመልከት አሁን በእስር ላይ ከሚገኘው አስካሉካን ትሬዲንግ ከተባለው ድርጅት ባለቤት ጋር በመሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብን ዘርፎ ነው የሄደው ስለዚህም ይህ ሰው በስርቆት ወንጀል ተሳትፏል የሚል ዘመቻ ነው፡፡ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት በዛው ወደ አሜሪካን እና ሌሎች አገሮች ሄዶ ከቀረ ተአማኒነቱን እናሳጣዋለን ተመልሶ ከመጣ ግን ዝም ብለን ነገሩን አድበስብሰን ተመልሶ የፓርቲው አባል እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን የሚል ዘዴ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህን ጊዜ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ስብሰባ እንደሚያደርግ አቶ ሀብታሙ በተለያዩ ሚድያዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኔም ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ግልፅ ያልሆኑልኝ ነገሮች ግልፅ እንዲሆኑልኝ አነጋግሬያቸው ምላሻቸውን አግኝቻለሁ፡፡ እንግዲህ የአዲስ አበባ ፎረም በአሁኑ ሰዐት በከፍተኛ የሚኒስትርነት ማዕረግ ላይ ያሉት አቶ ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች እና የፎረሙ አባላት በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ሞልተዋል ስብሰባውን የሚመራው የወቅቱ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ፀሀፊ ኤልያስ ባህሩ ነበር፡፡ እንግዲህ ወሳኙ ነገር እዚህ ጋር ነው ያለው፡፡

ቀድሞውኑ ስብሰባው ይደረግ እንደነበር ኢንፎርሜሽኑ የነበራቸው አቶ ሀብታሙ በስብሰባው ዋዜማ ከደቡብ አፍሪካ አዲስ አበባ ገብተው ነበርና ቀጥታ በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ አዳራሽ ሲገቡ በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ተሰብሳቢ ከወንበሩ በመነሳት በፉጨት እና በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው፡፡ እዚህ ጋር በነሬድዋን እና በሌሎቹ ባለስልጣናት ፊት ላይ ይነበብ የነበረውን ድንጋጤ ግን አንባቢ እንዲረዳልኝ እፈልጋለው፡፡ ታዲያ አቶ ሀብታሙ በአዳራሹ ውስጥ ተገኝተው መናገር እንደሚፈልጉ ይናገራሉ አሁንም እድሉ እንዲሰጣቸው እና እንዲናገሩ የጉባኤተኛው ሙሉ ፍቃድ ነበርና ይናገሩ የሚሉ ድምፆች ሲበረክቱ ተፈቅዶላቸው ወደ መድረኩ ወጡ፡፡ አቶ ሀብታሙንም ሆነ ሌሎች በጉባኤው ላይ የነበራችሁ በሙሉ የቀናነስኩት እና የዘነጋሁት ነገር ካለ ልታርሙኝ ትችላላችሁ፡፡ አቶ ሀብታሙም ወደ መድረኩ ወጥተው መነጋገሪያውን እንዳነሱ እንዲህ አሉ ‹‹እኔ ፍትህን በመሸሽ ሳይሆን በመጋፈጥ ነው የማምነው፡፡ ዘርፎ ነው ሀገር ጥሎ የሄደው፤ የብዙ ኢትዮጵውያንን ንብረት ዘርፏል እያለችሁ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍታችሁ ነበር፡፡ እውነት ዘርፌ ከሆነ ይኸው እጄን ለካቴና አንገቴን ለገመድ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ እውነት ዘርፌ ከሆነ በአደባባይ ስቅላትም ቢሆን ቢፈረድብኝ ወስኜ ነው የመጣሁት፤ አሁኑኑ ልታስሩኝ ትችላላችሁ፡፡ ማጭበርበር ሌብነት አስተዳደጌም ኢትዮጵያዊ ማንነቴም አይፈቅድልኝም ነግር ግን አብሬያችሁ ለሁለት አመት መቆየቴ ለኔ ስህተት እንደሆነ ተሰምቶኛል፤ በሀገር አንድነት ጉዳይ የማይታረቅ ልዩነት እንዳለን ልታውቁት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ላይ እጀን አላነሳም›› ካለ በኋላ አዳራሹን ለቆ ወጣ፡፡

በዚህም ምክንያት አቶ ሀብታሙ በዛ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መረጃ ሰታችኋል የተባሉ የአዲስ አበባ ፎረም አባላት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል፤ የወቅቱ ምክትል ሊቀመንበር ወጣት ዳዊት ግርማ፤ ዋና ጸሐፊ ወጣት ኤልያስ ባህሩ እና ሌሎችም በህይወት ስላሉ ምስክርነቱን ለመስጠት ምስክርነት ለመስጠትም ወደ ኋላ እንደማይሉ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው 2002 ዓ.ም ላይ ሆኖ ሳለ ከ3 አመት በኋላ ምን ተገኝቶ ነው ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲህ የተበራከተው የሚለው ነገር በአፅንኦት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በ2010 የአለም ዋንጫም ገንዘብ አጭበርብሮ ከሆነ የዛኔውኑ ለፍርድ አቅርቦ ውሳኔ ማሰጠት እየተቻለ በአቶ አቤል ኤፍሬምና መሰሎቻቸው አንዴ በፌስ ቡክ ሌላ ጊዜ በህትመት ሚዲያ በአሁኑ ሰአት ምን ፍለጋ ይሄ ዘመቻ ተጀመረ የሚለውን ነገር ካየነው በግልፅ ከህወሓት ጓዳ የወጡ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ለመሆናቸው እራሱን የሰማያዊ ፓርቲ አባል እንደሆነ አድርጎ የሚያየው (እዚህ ጋር ሰማያዊ እንዲህ አይነት አባል ይኖረዋል ብዬ ስለማላስብ ነው) አቤል ኤፍሬም የተባለ ቀንደኛ የስርአቱ ደጋፊ ተቆርቋሪ በመምሰል የሚያሰራጫቸው ፅሁፎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ፀሀፊው ይሄንኑ ፅሁፉን በአዲስ ዘመን ገፅ 3 ላይ እንዲሁም ደግሞ በአይጋ ፎረም ላይ የተለያዩ ሰዎች ሀሳብ በማስመሰል አውጥቶታል፡፡ አንባቢ ግን ልብ ሊል የሚገባው ነገር ኢህአዴግ ይህንን ዘመቻውን የጀመረው አንድነት ፓርቲ በሚያደርጋቸው ከህዝብ ጋር በሚያገኛኙ ጉዳዮች ላይ ሀብታሙ ግምባር ቀደም በመሆን የአምበሳውን ድርሻ ይዞ ጠንካራ ተቃዋሚነቱን ሲያሳይ ኢህአዴግ ህዝብ እየጨቆነ የሚገዛበት ጊዜ ሩቅ እንዳይሆን በማድረግ በኩል ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብሎ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ ሰዎች ላይ ይሄንን የስም ማጥፋት ዘመቻ ተያይዞት ነበር፡፡ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ብናነሳ ሀሳቡን ያለ ፍርሀት በመግለጽ የኢትዮጵያ ህዝብ አፍና ጆሮ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ እንዲህ አይነት ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተከፍተውበት ነበር፡፡ ተመስጌን ኢህአዴግ ነው፣ ካልሆነ ለምን እስካሁን አልታሰረም፣ የህወሓት ተላላኪ ነው፣ አብረውት ያሉትን ጋዜጠኞችን እንዲሰልልላቸው ነው በማለት በተለያዬ መንገድ በተከፈተው የስም ማጥፋት ዘመ እጅግ ብዙ ብዙ ነገሮችን…… ተባለ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ በዚህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከኪሳራ በቀር ትርፍ ሲያጣበት ተመስገን ደሳለኝን ነውጠኛ፣ አሸባሪ፣ አብዮት ናፋቂ፣….. በማለት በተለያዩ ክሶች ሊበላው እያዘጋጀው እንዳለ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ታዲያ ፍርሃት የማያውቀው ብርቱ ታጋይ ሀብታሙ አያሌው ላይ የተጀመረው ይህ ዘመቻም ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሆን እንዴ? ሀብታሙን በልደቱ ጫማ ለማስረገጥ መሞከር ህልም እንጂ እውን እንደማይሆን መረዳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ የስም ማጥፋት ዘመቻው ተጠናክሮ ሊቀጥል የከፋው እርምጃም ሊከት ግድ ነውንና ሀብታሙ ፅናቱን ይስጥህ ልልህ እወዳለሁ፡፡ ፅናትህን አውቃለሁና ለቀስት ወርዋሪዎቹ የህወሓት ስውር እጆች …..ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሎቹም ጉዟቸውን ቀጥለዋል በልልኝ ፡፡ ቸር ያሰንብተን፡፡

No comments: