Saturday, June 28, 2014

ጥቂት ነጥቦች በፍትህ ጉዳይ ላይ

June 28/2014

ጥቂት ነጥቦች በፍትህ ጉዳይ ላይ

ጥቂት ነጥቦች በፍትህ ጉዳይ ላይ

ታደሰ ብሩ

1.     መግቢያ

ህወሓት በሥልጣን ላይ በከረመ መጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትህ እጦት የሚደርስበት መከራ እየጨመረና እየመረረ በመምጣቱ “ፍትህ አጣን፤ የፍትህ ያለህ” የሚሉ እሮሮዎች ከቀድሞው በበለጠ መልኩ እየጎሉ መጥተዋል። በከተማውም በገጠሩም፣ ከእድሜ ባለፀጋውም ከወጣቱም፣ ከወንዱም ከሴቱ፣ ከክርስቲያኑም ከሙስሊሙም ወገኖቻችን የሚሰማው ጩከት “የፍትህ ያለህ” የሚል ነው። የፍትህ እጦት ነው ወገኖቻችንን በገዛ አገራቸው ተፈናቃይ ያደረጋቸው፤ የፍትህ እጦት ነው ገበሬዎች ማሳቸው ለባዕዳን ሲሰጥ አንጀታቸው እያረረ ዝም እንዲሉ የሚያደርጋቸው፤ የፍትህ እጦት ነው ነጋዴዎች ሱቆቻቸው በእሳት ሲጋዩ “ጉዳዩ  ይጣራልን”  ማለት እንኳን ያላስቻላቸው፤ የፍትህ እጦት ነው የእምነት ነፃነታችንን እንኳን ማስከበር ያላስቻለን።
ፍትህ ሰዎች በግልም በቡድንም ተሳስበው እና ተጋግዘው እንዲኖሩ የሚያደርግ የበጎ ሥነ-ምግባር መርሆች ስብስብ ነው። ፍትህ ነው ማኅበረ-ሰብን ከማኅበረ-አራዊት የሚለየው። ማኅበራዊ ኑሯቸውን በሥርዓት አደራጅተው የሚኖሩ እንስሳት መኖራቸው ቢታወቅም (ለምሳሌ የጉንዳን ሠራዊት፤ የንብ መንጋ) በእውቅ (Consciously) የተገነባ የፍትህ ሥርዓት ያለው የሰው ልጅ ብቻ  ነው። ፍትህ ሰውኛ እሴት ነው።
ምንም ዓይነት ፍትህ የሌለበት ማኅበረሰብን ለማሰብ ብንሞክር በአዕምሮዓችን ሊመጣልን የሚችለው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ከፍ ካለ ቤተሰብ፤ ከዚህ በላይ ከፍ ካለ ደግሞ የተዛመዱ ቤተሰቦች የፈጠሩት ስብስብ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ወይም በዝምድና የተሳሰረ ስብስብ የገዛ ራሱን ወይም ቡድኑን ለማኖርና ከጥቃት ለማዳን የሚጥርበት ሥርዓት እናገኛለን። በዚህ ሥርዓት ውስጥ “የሥጋ” ዝምድና (ለምሳሌ እናትና ልጅ) ብቸኛው ማስተሳሠሪያ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ዘር ብቸኛ የስብስቡ ማስተሳሠሪያ ይሆናል። በማኅበረ-እንስሳት ውስጥ መንጋን የሚያስተሳስረው በዘር መነሻነት የተፈጠረ አብሮ ውሎ ማደር ነው። ፍትህ በሌለበት ማኅበረሰብም ውስጥ የሚዛመዱ ቤተሰቦች ራሳቸው በተለያየ ስያሜ ወደሚጠሩ ስብስቦች ማደግ ይችላሉ። ትልቅም ይሁኑ ትንሽ፣ ስብስቦቹን የሚያገናኛቸው ዝርያቸው ነው። በማኅበረ-እንስሳት ውስጥ በመንጋዎች መካከል የማያቋርጥ ትንንቅ ይኖራል። በማኅበረ-እንስሳት ደካማው ብቻ ሳይሆን ጠንካራውም ቢሆን ሕይወቱን በሰቀቀን ማሳለፉ የግድ ነው። ጠንካራው መንጋ ከሱ የባሰ ጠንካራ መንጋ  እንዳይመጣበት እንደሰጋ ይኖራል። ፍትህ የሌለበት ማኅበረሰብም እንደዚያው ነው። ፍትህ በሌለበት፣ ሰዎች በዘር መደራጀታቸው ተፈጥሮዓዊ የመሆኑን ያህል እርስ በርሳቸው መጣላታቸውም እንደዝያው የማይቀር ተፈጥሮዊ ነው። በቡድኖች መካከል ያለው ጦርነት በአንዱ ቡድን ጊዜዓዊ አሸናፊነት ጋብ ሲል በቡድኑ ውስጥ ባሉ ቤተሰቦች መካከል ጦርነት ይነሳል፤  ያ ጋብ ሲል ደግሞ በእያንዳንዱ ግለሰብ መካከል ይጀመራል። ሲከፋ ወገንና ጠላት ያልለየ ሁሉም ከሁሉም ጋር (all against all) ጦርነት ውስጥ ይገባል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ነው ህገ-አራዊት የሚባለው። ፍትህ በሌለበት የሰው ልጆች ሕይወት ወደ ህገ-አራዊት ያሽቆለቁላል።
ወያኔ አገራችንን እንዲህ ወደ አለ አስቀያሚና አስፈሪ ሁኔታ እየገፋት ነው። ፍትህ ድራሿ ጠፍቶ፣ ዘር ብቻውን የኑሮ መሠረት ሲሆን የቁልቁለት ጉዟችን የሚያደርሰን ወደ ህገ-አራዊት መሆኑ የማይቀር ነው።

2.   ህግ፣ ፍትህ እና የህግ የበላይነት

ህግ እና ፍትህ በጥብቅ የተቆራኙ ቢሆንም የተለያዩ ጽንሰ-ሀሳቦች ናቸው። ህግ “ይህንን አድርግ፤ ያንን አታድርግ” የሚል ድንጋጌ ነው። አቅም ያለው ሁሉ የፈለገውን ህግ አውጥቶ ሊያስፈጽም ይችላል። ፍትህ፣ ሰዎች ተሳስበው እና ተጋግዘው እንዲኖሩ የሚያደርግ፤ አድዎንና ጥቃትን የሚከላከል፤ በዳይን የሚቀጣ፣ ተጠቂን የሚክስ በጎነት ነው። ፍትህ የማኅበራዊ ተቋማት ቀዳሚ በጎ ውጤት ነው። ህግ መሣሪያ ሲሆን ፍትህ ህጉ በተግባር ላይ ሲውል የሚገኘው ውጤት ነው። ጥሩ ህግ በሥራ ላይ ከዋለ ፍትህን ያስገኛል። ጥሩ ህግ ኖሮ ሥራ ላይ ካልዋለ ህጉ መኖሩ ብቻውን ፍትህን አያስገኝም። መጥፎ ህግ ደግሞ ፍትህን ያጓድላል፤ ኢፍትሃዊነትን ያነግሳል። “የህግ የበላይነት” ሲባል በሁሉም ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ህግ አለ ማለት ነው።
የህግ የበላይነት እንዲከበር ቢያንስ ሁለት ነገሮች መሟላት ይኖርባቸዋል።
justice
2.1.  ህግ፣ ፍትሃዊ ይሁንም አይሁን፣ ያለ አድልዎ በሥራ ላይ መዋል አለበት
መጥፎም ይሁን ጥሩ፣ አንድ ህግ በሁሉም ላይ እኩል ሥራ ላይ ከዋለ የህግ የበላይነትን አንድ መሠረታዊ መሥፈርት አሟላ ማለት ይቻላል።  በተለይም ህግ አስፈፃሚው በህጎቹ ራሱ የሚገዛባቸው መሆን አለመሆኑ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ህግ አውጭው የሚያወጣቸውን ህጎች ህግ አስፈፃሚው ሲፈልግ በሥራ ላይ የሚያውላቸው፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚተዋቸው ከሆነ፣ የህጎቹ መኖር ለህግ የበላይነት መከበር የሚሰጠው ፋይዳ የለም።
በሀገራችን ወያኔ የሚያወጣቸው ከልካይ ህጎች ተቀናቃኞቹን እንጂ ራሱን ወያኔን አይከለክሉትም። ለምሳሌ በፀረ-ሽብር ህጉ፣ የወያኔ አሻንጉሊት ፓርላማ በሽብርትነት ከፈረጃቸው ድርጅቶች ጋር መነጋገር ያስቀጣል። ይህ ክልከላ ግን በራሱ በወያኔ ላይ አይሠራም፤ ከአብነግ ጋር ይፋ ለሆነ ድርድር ላይ መቀመጡ በራሱ ሚዲያ በይፋ ገልጿል።  “ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተባብሮ  ይሠራል” ሲል በከሀዲነት ይወነጅላል፤ ወያኔ እራሱ ግን ከሰባ ጊዜ በላይ  ከኤርትራ ጋር አብሮ ለመሥራት ሙከራ አድርጎ እንዳልተሳካለት በመግለጽ ያማርራል።
ወያኔ የሚያወጣቸው ህጎች ፍትሃዊነት የጎደላቸው ቢሆንም እንኳን በትክክል ሥራ ላይ ውለው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር። ወ/ት ርዕዮተ ዓለሙ ላይ በመጀመሪያ 14 ዓመት ከዚያ ደግሞ በይግባኝ 5 ዓመት የተፈረደባት የፀረ-ሽብር ህጉ መጥፎ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ዳኝነትና ዳኛ ቢኖር ኖሮ በዚሁ ህግ ተከራክራ ነፃ መውጣት ትችል ነበር። ዳኝነት ኖሮ ቢሆን ኖሮ እስክንድር ነጋ በተከሰበት ኢፍትሃዊ ህግም ቢሆን ተከራክሮ ነፃ ይወጣ ነበር። የአንዱዓለም፣ የሙስሊም ማኅበረሰብ መሪዎች እና ሌሎች በርካታ ወገኖቻችን ጉዳይም እንደዚሁ ነው፤ ዳኝነት ቢኖር ኖሮ በተከሰሱበት ህግ ተከራክረው ነፃ መውጣት ይችሉ ነበር። ዳኝነት ኖሮ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቹ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ ነበር።
ዛሬ አገራችን ውስጥ ያለው የህግ ችግር የመጥፎ (የኢፍትሃዊ) ህጎች መብዛት ብቻ አይደለም። ችግራችን ከዚያም ያልፋል። ባጠቃላይ የሚሠራ ህግ የለም፤ ዳኝነት የለም። ህገ-አልባነት ህግ ሆኗል።
2.2.  የህጎች ፍትሃዊ መሆን አስፈላጊነት
ህግ ሁሉ ግን ወደ ፍትህ አያደርስም። ፍትህን የሚያሰፍኑ ህጎች አሉ፤ ኢፍትሃዊነትን የሚያሰፍኑ ህጎችም ሊኖሩ ይችላሉ። የወንድና ሴት መሳሳም የሚያስቀጣበት አገር አለ። እንደኛ አገር ደግሞ መንግሥት ያልወደደውን ጋዜጣ ማንበብ የሚያስቀጣበት አገር አለ። የህግና የፍትህ ግኑኝነት ውስብስብ ነው። ለምሳሌ፣ “ሰዎች ሁሉ እኩል መስተናገድ አለባቸው” የሚል ህግ ቢወጣ በግልቡ ሲታይ ችግር ያለው ባይመስልም በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ግን ፍትሃዊ ላይሆን ይችላል። አንድ የጤና ጣቢያ ለአንድ ጤነኛ ባለጉዳይ እና የአካል ጉዳት ላለበት ሌላ ባለጉዳይ እኩል መስተንግዶ መስጠት አለብኝ ቢል ኢፍትሃዊ ነው። ከሚሰጠው አገልግሎት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአካል ጉዳተኛው የተለየ መስተንግዶ ሊሰጠው ይገባል። ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሰው ዓይነት በደምሳሳው ሲታይ ችግር ያለበት የማይመስል ቀና ህግ እንኳን በሥራ ላይ በሚውልበት በፍትህ ሚዛን መታየት ይኖርበታል።
ህግ ተብለው በሥራ የሚውሉ ድንጋጌዎች ገና ከመነሻው በማያሻማ ሁኔታ ከፍትህ ጋር የተጣሉ ሲሆኑ ምን ይደረጋል? ለምሳሌ፣ መነጋገርንና ማሰብን የሚከለክል ህግን እንዴት መቀበል ይቻላል? ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን የሚከለክል ህግን እንዴት መቀበል ይቻላል? መደራጀትን የሚከለክል ህግ እንደምን መቀበል ይቻላል? ለፍትህ ግድ ያለው ሰው ወይም ቡድን እንዲህ ዓይነት ህጎችን በማክበር ሳይሆን በመጣስ ነው ለፍትህ ዘብ መቆም የሚችለው። በህግ የበላይነት ሰበብ ለኢፍትሃዊ ህጎች መገዛት ከተጠያቂነት የማያድነውም ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነው የፍትህ ስሜት በውስጣችን ሊኖር ስለሚገባው ነው። ዛሬ በወገኖቻችን ላይ ሰቆቃ እየፈፀሙ (ቶርቸር እያደረጉ) ያሉ አረመኔዎች ዛሬ ያለው ህግ ይህን እንዲፈጽሙ ቢያዛቸው እንኳ ነገ ሲጠየቁ “እኔ ህጉ ያዘዘኝን የፈፀምኩት፤ የሥራ ግዴታዬን ነው የተወጣሁት” ማለት የማያድናቸው ኢፍትሃዊ ትዕዛዝን፣ ደንብንም ሆና አዋጅን የመቃወሚያ ህሊና የተሰጣቸው በመሆኑ ነው።
ሰው ሆነን ተፈጥረን በሰዎች ማኅበር ውስጥ በማደጋችን ብቻ የተወሰነ የፍትህ ስሜት በውስጣችን አለ።  በዚህ የፍትህ ስሜት (በተለምዶ አነጋገር በህሊና ዳኝነት) የሚገዛ ማንኛውም ሰው በራሱ ላይ እንዲደርስ የማይፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አያደርስም፤ ሌሎች በሌሎች ላይ ጥቃት ሲያደርሱም አይቶ ዝም አይልም። ህሊናችን ኢፍትሃዊ ህጎችን ይፀየፋል

3.   ኢትዮጵያ፣ ህግና ፍትህ

justice 02
ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ወለፈንዲዎች (Paradoxes) አገር ናት። ከእነዚህ ወለፈንዲዎችም አንዱ ፍትህና ህግ በኢትዮጵያ ያላቸው ቦታ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ በኩል ህግ አክባሪ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ የተነፈገ ሕዝብ ነው። እንዴት ፍትህ የተነፈገ ሕዝብ ህግ አክባሪ ይሆናል? ይህ ለመረዳት የሚቸግር ወለፈንዲ ነው
ለኢትዮጵያዊያን “በህግ አምላክ” ትልቅ ትርጉም ያለው ሀረግ ነው። ድሮ (ከወያኔ በፊት) ተበዳይ በዳያን አግኝቶ “በህግ አምላክ ቁም ብዬሃለሁ” ካለው ፓሊስ እንኳን ባይኖር ምስክር ወይም ገላጋይ እስኪመጣ ድረስ “ቁም” የተባለው ሰው ባለበት ይቆም ነበር። “የህግ አምላክን” ማክበር አምላክን ከማክበር ጋር እኩል ነበር። “የህግ አምላክ” መኖሩ ተገዢዎች በህጉ ተፈፃሚነት ላይ እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ገዢዎችም ቢሆኑ ለዳኝነት ክብር እንዲሰጡ “የህግ አምላክ” በተወሰነ መጠንም ቢሆን አገልግሏል። ከፍትህ አንፃር የቀደሙት ሥርዓቶች ብዙ ጉድለቶች የነበሩባቸው ቢሆንም ችሎትን እንደ አሁን መዘባበቻ ያላደረጉበት አንዱ ምክንያት ፍትህን ከመለኮታዊ ሥልጣን ጋር ማያያዛቸው ነው። ይህ እውነታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዲያድርበት አድርጓል። አንድ ባለጉዳይ በአንድ ዳኛ ቢፈረድበት “የህግ አምላክ” ስላለ በሚቀጥለው እርከን ላይ ያለው ዳኛ ዘንድ ፍትህን አገኛለሁ በሚል ለአቤቱታ ይጓዛል፤ እዚያም ባይሳካለት ወደሚቀጥለው እርከን አቤት ይላል። እንዲህ እያለ አንዳንዱ እንጉሥ ችሎት ዘንድ ይቀርባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ፍትህ እየተነፈገውም “በህግ አምላክ” ላይ ተስፋ የማይቆርጥ ህገ አክባሪ ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ህግ አክባሪነት በችሎቶች ደጃፎች ብቻ ሳይሆን በዘወትር ሕይወቱም የሚታይ ነው። በከተሞች ውስጥ የወርቅ ቤቶችን ግድዳዎች ተደግፈው የሚያድሩ ድሆች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ጠመንጃ ይዞ “አገሬ መግቢያ መሳፈሪያ ሙሉልኝ” ወይም “ራበኝ፣ ለምሳ ተዘከሩኝ” የሚል ወታደር የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ ሁሉ መልካም ባህል አሁን በዘመነ ወያኔ በዓይኖቻችን ሥር እየተንኮታኮተ ነው። ይህ በቀላሉ የማይገነባ ክቡር ባህል እያጣን ነው።
አሳዛኙ ነገር በዚህ ህግ አክባሪ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተጫኑ ገዢዎች የሕዝቡን ህግ አክባሪነት በሚመጥን መጠን ህግን አክብረው የሚያስከብሩ አለመሆናቸው ነው። በህግ አጠባበቅ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ያለው የቁልቁለት ጉዞ አስፈሪ ነው። ኢትዮጵያ ከአንድ ገዢ መዳፍ ወደ ሌላው በተወረወረች ቁጥር ፍትህ ከቀድሞው በባሰ እየተረገጠች መጥታለች። የቅርቡን ዓመታት እንኳን በምሳሌነት ብንጠቅስ የአጼ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ኢፍትሃዊነት ያስመረራቸው ወገኖች ሥርዓቱን ታገሉት፤ በትግሉ አሸንፎ የወጣው ግን ከቀድሞው የባሰው ደርግ ሆነ። የደርግ ሥርዓት ያስመረራቸው ታገሉት፤ በትግሉ አሸንፎ  የወጣው ግን ከደርግ የባሰው ወያኔ ሆነ።  ይህ የቁልቁለት ጉዞ ካልተሰበረ  አደጋው በዚሁ ዓይነት ሊቀጥል ይችላል።
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የፍትህ እሳቤያችን ራሱ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነው። ቀድሞ፣ ከላይ እንደተገለፀው፣ ፍትህ መለኮታዊ ፀጋ ተደርጋ ትወሰድ ነበር፤ መቀመጫዋም ከአማልክት ጎን ነበር። “በህግ አምላክ” ሲባልም የአማልክት መቀመጫ ነው ተብሎ ወደሚታሰበው ሰማይ እየታየ ነበር። ከማርክሳዊ ሌሊናዊ ርዕዮተዓለም መምጣት ጋር ፍትህ ከሰማየ ሰማያት ወርዳ መሬት ላይ ተፈጠፈጠች። ፍትህ ሰዎችን ሁሉ በእኩል ማየቷ ቀረናመደባዊ ሆነች። በዚህ አዲሱ ዕይታ መሠረት የላብአደሩ ፍትህ እና የቡርዣው ፍትህ ለየቅል ብቻ ሳይሆን ተቃራኒ ሆነው ተገኙ። ለአንዱ ፍትሃዊ የሆነ ነገር ሁሉ ለሌላው ኢፍትሃዊ ነው። ከወያኔ መምጣት ጋር ደግሞ ፍትህ መሬት ላይ መንደባለሏም በዝቶ ጉድጓድ ተቆፍሮ እጉድጓጉ ውስጥ ተጣለች። በአዲሱ ወያኔ አመጣሽ ዕይታ እያንዳንዱ ዘር (ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ) በየራሱ ጉድጓድ ውስጥ የቀበራት የራሱ ፍትህ አለው። የትግሬ ፍትህ እና የአማራው ፍትህ አይተዋወቁም። አሮሞው፣ አደሬው፣ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ሲዳማው፣ ጉራጌው …. እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ፍትህ አላቸው። አንዱ ዘንድ ፍትሃዊ የሆነ ሌላው ጋር ፍትሃዊም ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። እንደመደብ ትንተናው እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። በዚህም ምክንያት ነው ማኅበረሰባችን ብዥታ በበዛበት ሁኔታ ላይ የሚገኘው። ለምሳሌ አንዱ ዘር በገነባው ሀውልት በሀሴት ሲጨፍር፤ ሌላው በንዴት ይበግናል፤ ሶስተኛው ደግሞ ምንም ስሜት አይሰጠውም። በአንድ ቋንቋ እየተነጋገርን መሰማማት የቸገረንም በዚህ የፍትህ እሳቤ መዛባት ጭምርም ነው።

4.   ምልከታ ወደፊት

ይህ ሁሉ የሚያመለክተው (1) አገራችን የምትገኝበት አሳሳቢ ደረጃ፣ እና (2) እኛ (ማለትም በዚህ ዘመን ያለነው ኢትዮጵያዊያን) ላይ የወደቀውን የኃላፊነት ክብደት ነው። ዜጎች ፍትህ የማግኘት ተስፋቸው ሲሟጠጥ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ላይ የነበራቸው ተስፋ ይጨልማል። “ታግለን ሥርዓቱን ወደ መልካምነት ልንቀይረው እንችላለን” የሚለው እምነት ካልዳበረ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለመጪው ትውልድ መጨነቅ ያቆሙና እያንዳንዱ ሰው “እኔ ምን አቀበጠኝ” እያለ  ሁሉም ጭቆናን ችለው ለመኖር ሊመርጡ ይችላሉ። ይህ እንዳይመጣ መወሰን ያለብን በየግላችን ነው።
ይህን ወሳኝ የግል ውሳኔ የሰጠን ሰዎች ደግሞ መሰባሰብና ተግባሮቻችን ማቀናጀት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን በአገራችን የተንሰራፋውን ኢፍትሃዊነትን መዋጋት የሚቻለው በፓለቲካ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ ሲመጣ መሆኑን ለማመን ጊዜ አይወስድብንም።  ከዚህ ቀጥሎ  የሚመጣው አቢይ ጥያቄ “ለውጥ እንዴት?” የሚለው ይሆናል።  ከዚያ በፊት ግን በለውጡ አስፈላጊነት እና ይህ ለውጥ ካልመጣ  ሰዎች ሆነን የመቀጠላችን ጉዳይ እንኳን አጠራጣሪ መሆኑ በትክክል ልንረዳ ይገባል።  ይህ ቁርጠኝነት ሥር እንዲሰድ ስለ ፍትህ ያለን ግንዛቤ በየጊዜው መዳበር ይኖርበታል።
በፍትህ እጦት ሳቢያ በየእስር ቤቶች እየተሰቃዩ ላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፤ ከማሳዎቻቸው ተፈናቅለው ለተበተኑ ወገኖቻችን፤ አደገኛ የበረሃና የባህር ጉዞ በማድረግ ለተሰደዱ ወገኖቻችን፣ ለራሳችን እና ለመጪው ትውልድ ልንደርስለት ይገባል። ፍትህን ከተቀበረችበት ጉድጓድ በቶሎ ካላወጣናት አገር አይኖረንም፤ እኛም ሰዎች ሆነን አንቀጥልም። በዚህ የኃላፊነት እና የአጣዳፊነት ስሜት ነው የፍትህ ግንዛቤዓችን መገንባት የሚኖርበት።

    ፀሐፊውን በ tkersmo@gmail.com ማግኘት ይቻላል

    No comments: