Monday, June 30, 2014

እያበበ የመጣዉ ህዝባዊ ትግል

June 29/2014
ኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት እንወድሀለን በሚሉት ነገስታት ተረግጧል፤ ህብረተሰብዓዊነት አመጣንልህ ባሉት ወታደራዊ አምባገነኖችም ለ17 አመት እጅና እግሩን ታስሮ ተገዝቷል። እነዚህ ሁለት ለህዝብ ደንታ የሌላቸዉ መንግስታት ተራ በተራ በህዝብ ትግል ተንኮታኩተዉ የታሪክ ቅርጫት ዉስጥ ገብተዋል፤ ሆኖም ሁለቱንም መንግስታት በመራራ ትግል አሸንፎ የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግሉን ዉጤት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ይህ ኃያልና የረጂም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነ ህዝብ ዛሬም ነፃ አወጣንህ በሚሉት ዘረኛ አምባገነኖች እየተረገጠ ነዉ። አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም እየተረገጠ ነዉ። ዛሬም አየታሰረ ነዉ። ዛሬም እየተገደለ ነዉ። ዛሬም ይህንን ሁሉ በደል የሚያደርሱበትን የአንድ ወንዝና የአንድ መንደር ምርት የሆኑ ዘረኛ አምባገነን ገዢዎችን ከጭንቅላቱ ላይ ለማዉረድ እየታገለ ነዉ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ከምን ግዜም በተለየ መልኩ የወያኔን ዘረኛ አገዛዝ አምርሮ እየታገለ ነዉ፤ በተለይ በዚህ በያዝነዉ አመት ወያኔንና ሃያ ሁለት አመት ሙሉ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐቱን ለመደምሰስና ኢትዮጵያ ዉስጥ በፍትህና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዐት ለመገንባት የሚደረገዉ የሞት የሽረት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ወያኔ እግሩ አዲስ አበባን ከረገጠበት ግዜ ጀምሮ የጭቆና ተቋሞቹን በየቦታዉ ተክሎና ተደላድሎ ህዝብን እንዳሰኘዉ መርገጥ እስከጀመረበት ግዜ ድረስ አንዴ ሰዉ በላዉን የደርግ ስርዐት አስወገድኩላችሁ እያለ ሌላ ግዜ ደግሞ ፌዴራል ስርዐት መስርቼ ብሄር ብሄረሰቦችን ነፃ አወጣሁ እያለ ለተወስነ ግዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ያ በፌዴራሊዝም፤ በዲሞክራሲና በይስሙላ ምርጫ የተሸፈነዉ የወያኔ አስቀያሚ ገበና ይፋ እየሆነ መጥቶ ወያኔ አርግጫዉንና ግድያዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ትግሉን፤ እስሩንና ስደቱን ተያያዙት።
የወያኔን መሰሪ አላማ ገና ከጧቱ የተረዱ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ይህንን መሰሪ አገዛዝ በተደራጀ፤ ባልተደራጀ፤ በተባበረና በተበታተነ መልኩ ሲታገሉ ቆይተዋል። ሆኖም የአገራችንን የፖለቲካና የኤኮኖሚ መዋቅሮች ሙሉ ለሙሉ ከሚቆጣጠረዉ ወያኔ ጋር በቁጥር፤ በአይነትና በይዘት የሚመጥን ትግል ማካሄድ ባለመቻላቸዉና እንዲሁም ብትራቸዉን ወያኔ ላይ ብቻ ከመሰንዘር ይልቅ እርስ በርስ ስለሚላተሙበት ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ በሌለዉ ወያኔ ላይ የትግል የበላይነት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ወያኔም እኛዉ ዉስጥ ከመካከላችን የበቀለ እሾክ በመሆኑና ደካማ ጎናችንን በሚገባ ስለሚያዉቀዉ በዚሁ ደካማ ጎናችን እየገባና እርስ በርስ እያባላን የስልጣን ዘመኑን እስከዛሬ ማራዘም ችሏል።
ወያኔ የአንድን አካባቢ ህዝብ ከሌላዉ አካባቢ ህዝብ፤ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል ከሌላ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሆነዉ ባልሆነዉ ምክንያት እየፈጠረ ማጋጨቱን አሁንም አላቆመም፤ እንዲያዉም ይበልላችሁ ብሎ በስፋት እንደቀጠለበት ነዉ። ዘንድሮ ግን ህዝብ፤ የተቃዋሚ ኃይሎችና በወያኔ ተንኮል ተታልለዉ የእርስ በርስ ሽኩቻ ዉስጥ ገብተዉ የነበሩ የህዝብ ወገኖች ሁሉ የወያኔን የከፋፍለህ ግዛዉ ደባና ሴራ በሚገባ ያወቁ ይመስላል። ለምሳሌ በቅርቡ አምቦና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ ከፍተኛ ፀረ ወያኔ የተቃዉሞ ሰልፍ በተካሄደ ግዜ የወያኔ ካድሬዎች የኦሮሞ ህዝብ ቁጣና መነሳሳት አቅጣጫዉን ቀይሮ በትግል አጋሩ በአማራ ህዝብ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ያልፈነቀሉት ዲንጋይ አልነበረም። ሆኖም ወያኔን ከስልጣን ለማባረርና የአገራቸንን ወደፊት በህዝብ እጅ ላይ ለማስቀመጥ ቁልፉ መተባባርና አንድ ላይ መቆም መሆኑን የተረዳዉ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ቁጣ ይበልጥ በወያኔ ላይ ነደደ እንጂ አንደቀድሞዉ ለወያኔ የተንኮል ሴራ እጁን አልሰጠም።
ወየኔን በተለያዩ የትግል ስልቶች የሚፋለሙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በፀረ ወያኔ አቋማቸዉና በአላማቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ከጎናቸዉ እንዳለ እንኳን እኛ ወያኔም በሚገባ ያዉቃል። ህዝብን የመሰለ እንደ ዉኃ ማጥለቅለቅ የሚችል ኃይል ከጎናቸዉ ያሰለፉ ድርጅቶች ደግሞ ወያኔን የመሰለ ምንም ህዝባዊ መሰረት የሌለዉን ኃይል ቀርቶ ፊታቸዉ ላይ የቆመን ምንም አይነት ኃይል ከማሸነፍ የሚገታቸዉ ምንም ነገር የለም።
ሆኖም ዉኃም ቢሆን ምን ያክል ኃይለኛ መሆኑ የሚታወቀዉ ተገድቦ ወደ ተፈለገበት አቅጣጫ እንዲሄድ ሲደረግ ነዉና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችም ከጎናቸዉ የቆመዉን ህዝብ አስተባብረዉ አገራችንን ወደ ድል መምራት የሚችሉት መጀመሪያ እነሱ ተባብረዉ ህዝብን በአንድ አላማና በአንድ አመራር ስር ማሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነዉ። ዛሬ በሁሉም አካባቢዎች ባይሆንም አገር ዉስጥና ካገር ዉጭ በተለያዩ አካባቢዎቸ ይቅናችሁ በሚያሰኝ መልኩ ጎልተዉ የሚታዩ ብዙ የትብብርና የትግል ቅንጅት ጅምሮች አሉ። በገበሬዉና በሰራተኛዉ፤በወጣቱና በወታደሩ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ብሄረሰቦችና በተለያዪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከመለያየት ይልቅ የመቀራረብ፤ ከመወቃቀስ ይልቅ የመወያየት ከመጠላለፍ ይልቅ የመተቃቀፍ አዝማሚያዎች በብዛት እየታዩ ነዉ።
ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ጀምሮ እስከቅርብ ግዜ ድረስ የተቃዋሚዉን ጎራ በተለይም አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኙትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልህቃን ለሁለት ከፍሎ ሲያጨቃጭቅ የከረመዉ ወያኔን በህዝባዊ አመጽ ወይስ በህዝባዊ እምቢተኝነት ታግለን እናዉርደዉ የሚለዉ ጥያቄ ዛሬም ድረስ አዎንታዊ እልባት ባያገኝም ዛሬ ሌላ ቢቀር እንደቀድሞዉ የተቃዋሚዉን ጎራ ለሁለት ከፍሎ የወያኔ መጠቀሚያ ማድረግ አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብም እኔ ያለሁት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉና ወይ ተደጋግፋችሁ አዉጡኝ አለዚያም በቻላችሁትና በሚታያችሁ መንገድ አዉጡኝ ነዉ የሚለን እንጂ በኛ መጨቃጨቅ የሱ የጉድጓድ ዉስጥ ቆይታ ዬትየለሌ እንዲሆን አይፈልግም። ዛሬ ይህንን ተደጋግፋችሁ ነጻ አዉጡኝ የሚለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ሰምተዉ በየጫካዉና በየበረሃዉ ከወያኔ ጋር የሞት የሽረት ትግል ለማድረግ የቆረጡ ኃይሎች የሚያደርጉት መሰባሰብና በተባበር ወገንን እጅግ የሚያበረታታ ጠላትን ደግሞ ያንኑ ያክል የሚያንቀጠቅጥ መልካም ጅምር ነዉ።
ከተለያዩ የአገራችን ኣካባቢዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተዉጣጥተዉ ወያኔን በሚገባዉ ብቸኛ ቋንቋ ለማነጋገር ቆርጠዉ የተነሱት የኢትዮጵያ ልጆች ወያኔን አንከባልለዉ የሚጥሉት ባነገቡት ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን በህብረታቸዉና በአላማ ጽናታቸዉ እንደሆነ በሚገባ ያዉቃሉ። ለዚህም ነዉ ዛሬ እነዚህ ጀግኖች ባሉበት ጫካና በረሃ ሁሉ የሚሰማዉ መዝሙር . . . . ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ . . . ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ደሜን የማፈሰዉ የሆነዉ።
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከዘረኞችና እነሱ ከገነቡት ዘረኛ ስርዐት ለማላቀቅ ዉስብስብነት ገብቷቸዉ ይህንን ዉስብስብ ትግል ከመታግል ዉጭ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለ ተረድተዉ የትግል ህብረትና አንድነት የጀመሩ ብዙ ወገኖች አሉ። ይህ የሚያበረታታና ተስፋዉ የለመለመ ጅምር የሁላችንም ድጋፍና ተሳትፎ የሚያስፈልገዉና አለንልህ ሊባል የሚገባዉ አገራዊ ጅምር ነዉ። በዚህ ጅምር ዉስጥ ትንቅንቅ አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ መስዋዕትነት አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ ድል አለ። በህዝባዊ እምቢተኝነቱ ጎራ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በብዙ የኢትዮጵያ ከተማዎች ዉስጥ ህዝቡ የወያኔን ግልምጫ፤ እስርና ድብደባና ግድያ ከምንም ባለመቁጠር በየአደባባዩ ወያኔን ፊት ለፊት መጋፈት ጀምሯል። ወያኔን በብዕራቸዉ የሚታገሉ ወጣቶችም ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት ይሻለናል ብለዉ በሰላ ብዕራቸዉ ህዝብን እንዳስተማሩ ቃሊቲ ወርደዋል። በህዝባዊ አመጹ ጎራ ደግሞ የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም ቆርጦ የተነሳዉ የኢትዮጵያ ወጣት አዲሱን የኢትዮጵያ የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት ታሪክ በደሙ ለመጻፍ የከተማ ኑሮ በቃኝ ብሎ የጫካና የበረሃ ኑሮዉን ተያይዞታል።
ዛሬ ይህንን እንዳባቶቹ ዱር ቤቴ ብሎና ጠመንጃቸዉን አንግቦ ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ የጀመረዉን ህዝባዊ አርበኛ የብሄረሰብ ስብጥር የተመከለተ ማንም ሰዉ የአገራችን ኢትዮጵያ ዳግማይ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑን በሙሉ አፉ ደፍሮ መናገር ይችላል። ወያኔ በነጋ በጠባ ከሚያስረዉና የወደፊቱን ካጨለመበት ወጣት ጀምሮ ገዳማቸዉን ካፈረሰባቸዉ መነኮሳትና ቤ/ክርስቲያናቸዉን አስካረከሰባቸዉ ካህናት ድረስ የትግሉ ጎራ ሁሉንም አይነት ኢትዮጵያዉያን በብዛት አካትቶ ይዟል።
ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በሚቆይባት በእያንዳንዷ ቀን ተጨማሪ ወጣቶች እንደሚታሰሩ፤ተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፈኞች እንደሚገደሉ፤ተጨማሪ ጋዜጠኞች ሽብርተኞች ተብለዉ እንደሚታሰሩ፤ ተጨማሪ ምሁራን አገራቸዉን ለቅቀዉ እንደሚሰደዱና የአገራችን የኢትዮጵያም አንድነት የበለጠ እየላላ እንደሚሄድ ሁላችንም በሚገባ እናዉቃለን። በሌላ አነጋገር ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የመቆየት አንድ ተጨማሪ ቀን በሰጠነዉ ቁጥር የኛም ሆነ የአገራችን ህልዉና በቀላሉ የማናበጀዉ እጥፍ ድርብ ችግር ዉስጥ ይወድቃል። ይህ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነዉ ችግርና መከራ ገና ከጧቱ የታያቸዉ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ አመታት የየራሳቸዉን እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት ዉስጥ አንዳንዶች ዉድ ህይወታቸዉን ገብረዋል፤ ሌሎች ደግሞ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፤ አገር ለቅዉ ተሰድደዋል። እዚህ ላይ አንድ ሁላችንም በትክክል ልንገነዘበዉ የሚገባን ሀቅ አለ፤ እሱም የኢትዮጵያ ችግር የአንድና የሁለት ሰዉ ችግር አይደለም፤ በአንድና በሁለት ሰዎች የሚፈታ ችግርም አይደለም። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፤ ችግሩም የሁላችንም ነዉ፤ ወያኔን በቆራጥነት ታግለን አገራችንን ከመበታተን ህዝባችንን ደግሞ ከዘረኝነትና ከድህነት ማላቀቅ ያለብንም እኛዉ ነን። ወያኔ ስለጠላነዉ፤ ስለሰደብነዉ ወይም ስለጮህንበት ብቻ በህዝብና በአገር ላይ በደል መፈጸሙን አያቆምም:፡ እነዚህ በደሎችና ችግሮች የሚቆሙትና የኢትዮጳያ ህዝብ የሰላም አየር መተንፈስ የሚችለዉ ወያኔ ከስልጣን ሲወገድና በምትኩ ኢትዮጵያዉያንን በእኩልነት የሚያስተናግድ መንግስት በኢትዮጵያዉያን ተመርጦ ስልጣን ሲይዝ ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰብዓዊ መብቱ፤ ለነጻነቱና ለእናት አገሩ አንድነት መከበር ትናንት ካደረገዉ ትገል የዛሬዉ እጅጉን የሚያበረታታ ቢሆንም አሁንም ይህንን ህዝባዊ አደራ ከተሸከሙ ኃይሎች የሚጠበቅ ብዙ ስራ አለ። ከላይ ከፍ ሲል ደጋግመን እንደጠቀስነዉ ከወያኔ ጋር በሚደረገዉ የትግል ሂደት ዉስጥ የህዝብ ኃይሎች የሚመኩበት ትልቁ ኃይል ህብረታቸዉና ከጎናቸዉ የተሰለፈዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ። የተቃዋሚ ኃይሎች አለመተባበርና አለመግባባት ከጎናቸዉ በተሰለፈዉ ህዝብ ዉስጥም አለመግባባትና አለመተባበር ይፈጥራል:፡ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ እየተቃወምነዉና እየታገልነዉ ዛሬ ድረስ የደረሰዉ እኛ ዉስጥ የነገሰዉ አለመተባበርና አለመግባባት እየረዳዉ ነዉ። ስለዚህ ዛሬ ወያኔን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከተወገደ በኋላም የሚገጥሙንን ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን የመገንባትና ህዝባዊ ስርዐትን የመፍጠር አደራ ጭምር ለመወጣት በህብረትና በአንድነት መቆም አለብን። አንድነታችንና ህብረታችን አንድ ስራ ሰርቶ ወያም አንድ ነጣላ አላማ ከግብ አድርሶ የሚቆም ሳይሆን የእኛን ሀላፊነት ተወጥተን ለልጅ ልጆቻችን የምናስተላልፈዉ ብሄራዊ ቅርስ መሆን አለበት።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments: