Thursday, June 5, 2014

ወጣቶች እየመጡ ነው!!!

June 5/2014
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ “ወጣት፤ የነብር ጣት!” በሚል ርዕስ ጥር 26 ቀን 2003 ዓ.ም. በቁጥር 142 ባወጣው ርዕሰ አንቀጹ “ወጣት በነብር ጣት መመሰል ያንሰው እንደሆን እንጂ አይበዛበትም። የኢትዮጵያም ወጣት የነብር ጣት ሆኖ ያውቃል … አሁንም ነው” ብሎ ነበር። በዚያ ጽሁፍ እና በሌሎችም አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ እንዳብራራው ግንቦት 7 በወጣቱ ችሎታና ተነሳሽነት ላይ ከፍተኛ እምነት አለው። የወደፊቷ ብቻ ሳይሆን የአሁኗ ኢትዮጵያም የወጣቱ መሆኗን ግንቦት 7 ያምናል። ግንቦት 7: ወጣቶችን ለማሳተፍና ለመሪነት ለማብቃት የሚጥር፤ ራሱም በወጣቶች የተገነባ ድርጅት ነው።
ኢትዮጵያ አገራችንና ሕዝቧን ከወያኔ አደንቋሪ አገዛዝ ለማላቀቅ ቆርጠው የተነሱ ወጣቶች እየበረከቱ መምጣታቸው የግንቦት 7 እምነትን የሚያጠናክር ሆኗል። አምባገነኑን የወያኔ አገዛዝን በትጥቅ ትግል መፋለም ይኖርብናል ብለው የተነሱ ወጣቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተደራጁ መሆናቸውን እንሰማለን። እድሜያቸው በሀያዎችና በሠላሳዎች መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ለጋ ወጣቶች ናቸው የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የሚባለውን የትግል ድርጅትን የፈጠሩት። ይህ ኃይል ሰሞኑን ለአራተኛ ጊዜ እጩዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን በተለያዩ ሚዲያዎች ባሰራጨው ዜና ገልጿል። በተመሳሳይም የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሰልጥኖ ለወሳኝ ትግል ዝግጁ መሆኑን አብስሯል። የኢትዮጵያ አርበኖች ግንባርም በወጣቶች የተሞላ ለትግል የተዘጋጀ ድርጅት ነው። ሌሎችም አሉ። እነዚህን ድርጅቶች ድርጅት ያደረጓቸው ወጣቶች ናቸው።
በሰላማዊ የትግል ዘርፍም ወያኔ የሚያደርስባቸው እስር፣ ዱላና እንግልት እየተቋቋሙ በየእለቱ እየበረቱ የመጡ ጀግኖች ወጣቶችን ማየት ችለናል። ወያኔ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ብሩህ አዕምሮና ልብ ያላቸው ወጣቶችን አስሬ፣ አሸማቅቄ ጨረስኩ ሲል ከዚያ የባሱ እየፈለቁ ነው። በነፃነት ሲጽፉ የነበሩ እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ እና ርዕዮተ ዓለሙ በሀሰት ክስና ምስክር ሲታሰሩ ወያኔ ተስፋ እንዳደረገው ወጣቶች በፍርሃት ተሸማቀው ልሳኖቻቸውን አልዘጉም። እንዲያውም ከነሱ የባሱ፣ የበሰሉ ጦማርተኞች መጡ። ሰላማዊ ታጋዮቹ እነ አንዱ ዓለም አራጌና ናትናኤል መኮንንን ሲያስር ከእነሱ የበለጡ ወጣት ወንድና ሴት ታጋዮች መጡ። እስከ ድል ድረስ ይህ ዑደት ይቀጥላል፤ ኢትዮጵያ ወጣት ጀግኖችን ማፍራቷ አያቋርጥም።
ወያኔ “ኢህአዴግ” በሚባል ቀፎ በሰበሰባቸው አድርባይ ድርጅት ውስጥ የተሰባሰቡ ወጣቶችም ወደ ህሊናቸው እየተመለሱ፣ ድፍረት እያገኙና እየከዱት ነው። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በወያኔ ድርጅቶች ውስጥ የገቡ ህሊና ያላቸው ወጣቶች “ምን እናርግ?” እያሉ ነው። ለእነዚህ ወገኖቻችን ግንቦት 7 አጭር ምላሽ አለው – “ከቻላችሁ ጥላችሁ ውጡና የነፃነት ትግሉን በይፋ ተቀላቀሉ፤ ካልቻላችሁ ኢህአዴግን ከውስጥ ሆናችሁ ውጉት፣ አዳክሙት፣ ግደሉት” ።
በሁሉም ረገድ በኢትዮጵያ ወጣት ላይ ያለ ተስፋን የሚያጠናክሩ ነገሮችን የምናስተውልበት ወቅት ላይ መሆናችን የሚያስደስት ነገር ነው። “እንዴት ልታገል? ከማን ጋር ልታገል?” የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል። ነፃነቱን የሚወድ ወጣት ሁሉ እንደ ፍላጎቱና ዝንባሌው የሚሳተፍበት መድረክ ተዘጋጅቶለታል።
ወያኔ፣ ወጣቱን ያህል የጎዳው የኢትዮጵያ የኅበረተሰብ ክፍል የለም። የህወሓት መሪዎች በወጣትነታቸው ዘመን “መብት ተነፈግን” ብለው ብረት አንስተዋል፤ የዛሬው ወጣት ግን እነሱ ያኔ የነበራቸውን እኩሌታ ያህል እንኳን መብት እንዳያገኝ አድርገዋል። የህወሓት ሁሉንም ጠቅልሎ የመግዛት ፍላጎት ወጣቱን መናገርም ሆነ መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማሰብ እንኳን እንዳይችል ለማድረግ እየሞከረ ነው።
የኑሮ እድሎች የሚከፋፈሉት በዘርና በፓለቲካ ወገንተኝተኝነት በመሆኑ ከሁለቱም ያልሆነው ወጣት ኑሮው የተጎሳቆለ፤ የነገ ተስፋውም የጨለመ ሆኗል። ስደት የኢትዮጵያ ወጣት እጣ ፈንታ ሆኗል። ዛሬ የተማረውና ከተሜው ብቻ ሳይሆን በትምህርት ያልገፋውና በገጠር በግብርና የሚተዳደረውም ወጣት ስደተኛ ሆኗል። አረብ አገራት፣ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪቃ በኢትዮጵያውያን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ተጨናንቀዋል። ወያኔ ወጣቱን በእድሜና በዝንባሌ ሳይሆን በዘር በማደራጀት የጎንደሩ ለባሌ፤ የሸዋው ለአሩሲ፤ የትግራዩ ለባህርዳር፣ የደሴው ለለቀምት ፈጽሞ ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ አድርጓል። ወያኔ፣ የኢትዮጵያን ወጣት በኢትዮጵያ ወጣት ላይ እንዲዘምት አድርጓል።
ያም ሆኖ ግን የወያኔ ፋሺስታዊ የጥፋት ፕሮጀክት እየተናደ ነው። በተስፋና በወኔ የተሞሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች በበረሃዎችና በሜዳዎች ላይ በአንድነት ሲዘምሩ ስናይ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ መሆኑ ይሰማናል። አዎ!!! የኢትዮጵያ ወጣቶች ከየአቅጣጫው እየመጡ ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልማቸውን ያልማል፤ ዜማቸውን ያዜማል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁሌም አብሯቸው ነው። ኢትዮጵያ በወጣቶቿ ብርቱ ትግል ከአገዛዝ ነፃ ትወጣለች።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments: