Tuesday, June 24, 2014

ጅቡ ሞቷል፡ ቀበሮው እየበላ ነው!

June 24/2014
ህወሓትን ስንቃወም የደርግ ናፋቂዎች ይሉናል። ህወሓትን መቃወም ደርግን መደገፍ ነው እንዴ? ደርግን ሳንደግፍ ህወሓትን መቃወም አንችልም እንዴ?
Abrha-Desta1በጎች፣ ጅብና ቀበሮ ነበሩ። ጅቡ ብዙ በጎችን ከበላ በኋላ ይሞታል። ከዛ ቀበሮ ይመጣል። በጅብ ሲበሉ፣ ሲሰቃዩ የከረሙ በጎች እንደገና በቀበሮ ሊበሉ ነው፤ ሊሰቃዩ ነው። ህይወት የመረራቸው በጎች በቀበሮ ሲበሉ “በእ” እያሉ መጮህ ጀመሩ። ቀበሮው አንድን በግ ሲበላ በጉ ይጭኽና ሌሎች በጎች ለግዜው ያመልጣሉ። ቀበሮውም አንድ መላ ይዘይዳል። በጎቹ ሲበሉ እንዳይጮሁና ሌሎችን እንዳያሰሙ ለማድረግ በጎቹን ሰብስቦ “በእ ምናምን እያላቹ አትጭሁ! ከጮኋቹ ግን ጅቡ ይነሳል። ከዛ በልቶ ይጭርሳችኋል። ስለዚህ ጅቡ እንዳይሰማቹ አትጭሁ!” ይላቸዋል።
ጅቡ ግን ሞቷል። በድን ሁኗል። ሬሳ ነው ያለው። በጎቹ ደግሞ ጅቡ በህይወት እያለ ከቀበሮ በላይ በግ-በሊታ መሆኑ ያውቁታል። ጅብ በአንዴ ብዙ በጎች (ቀበሮ ከሚበላው በላይ) ይበላ እንደነበር በደንብ ያውቃሉ።
እናም ቀበሮው “እኔ ስበላቹ የምትጮሁ ከሆነ ጭሆታቹ ጅብን ይጠራል። ጅብ ደግሞ ከኔ በላይ ይበላል። እኔ በቀን አንድ በግ ይበቃኛል። ጅብ ግን በአንዴ ይጨርሳችኋል። ስለዚህ ጅብ እንዳይሰማችሁ አትጭሁ። ዝም ብላቹ ብቻ ጅቡን እንዳይነሳ ጠብቁት፣ ተከላከሉት” ይላቸዋል። በጎችም አምነው ተቀብለው የሞተውን የጅብ በድን እንዳይነሳ ይጠብቃሉ። ቀበሮውም እነሱን አንድ በአንድ ይበላል። ሲበሉ አይጮሁም። ምክንያቱም ከጮሁማ ጅብ ድምፃቸው ሰምቶ ከሞት ይነሳል። ተነስቶ አንድ በአንድ በቀበሮ ሊበሉ የነበሩ በጎች በጅብ በአንዴ ሊበሉ ነው። ጅቡ ግን ሞቷል። አሁን ያለው ቀበሮ ነው። በጎቹ እኛ ህዝብ ነን። ቀበሮው ህወሓት ነው። ጅቡ ደግሞ ደርግ ነው። ጅቡ ሞቷል። ቀበሮው እየበላ ነው። በጎቹ ደግሞ በቀበሮው እየተበሉ የሞተውን የጅብ አስካሬን እንዳይመለስ ሳይጮሁ እየጠበቁ ነው።
የሐውዜን ጨፍጫፍ የህወሓት እጅ ነበረበት ማለት ደርግ ጨፍጫፊ አልነበረም ማለት አይደለም። ህወሓት መጥፎ ነው ማለት ደርግ ጥሩ ነበር ማለት አይደለም። ደርግ ሰዎች በልቷል። ህወሓትም ሰዎች እየበላ ነው። በህወሓትና ደርግ ያለው ልዩነት ደርግ ላይመለስ ሞቷል፤ ህወሓት ግን አለ። ስለዚህ ያሁኑ ጥረታችን በህይወት ካለው ህወሓት ጥቃት ራሳችን መከላከል እንጂ የሞተውን ደርግ መኮነን አይደለም። ምክንያቱም ደርግ ባናነሳውም ተመልሶ አይመጣም። ስለዚህ ደርግ ስጋት ሊሆን አይችልም። ያሁኑ ስጋት የህወሓት አገዛዝ ነው።
ጅቡ ሞቷል፡ ቀበሮው እየበላ ነው። ጅብን ፈርተን በቀበሮ አንበላም። ጅቡም ቀበሮውም ሊበሉን ልንፈቅድላቸው አይገባም። በጅብም በቀበሮም ከተበላን ያው መበላት ነው። መሞት ነው። ስለዚህ በሁለቱም መበላት የለብንም። ጅቡ ሞቷል፤ ቀበሮው ቀርቷል። የሞተውን ጅብ በመፍራት በህይወት ያለውን ቀበሮ ሲሳይ መሆን የለብንም። ጅብም አንፈልግም፣ ቀበሮውም አንፈልግም። ስለሞተው ጅብ እያወራን ግዜያችን አናጠፋም። ምክንያቱም ሞቷል። ስለ ቀበሮው ግን እንናገራለን። ምክንያቱም ሊጠፋን ይችላል።
እረኛ የሌለን በጎች ሆንን! በጅብ ተበላን። አሁንም በቀበሮ እየተበላን ነን። እረኛችን ከወዴት አለህ?
ድምፃችንን በማሰማት ከቀበሮ አራዊት ራሳችን እንጠብቅ።
በጎች!

No comments: