Wednesday, June 11, 2014

ኦባንግ “ከምርጫው” በፊት ለተቃዋሚዎች “ምርጫ” አቀረቡ

June 11/2014
ometho


ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና አግባብ አላቸው ለሚሏቸው አካላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው እንዲመክሩ ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ኢህአዴግ በውስጥ ችግሩ፣ በውጭ ተጽዕኖ ወይም በፖለቲካው የተፈጥሮ ባህርይ የሚከስምበት ደረጃ መድረሱን ያሳሰበው በ”ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ስምና ፊርማ የተበተነው የአኢጋን ደብዳቤ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አጥብበው እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡ ይህንን ለኢትዮጵያና ለሕዝባቸው ሲሉ መሥራት የማይችሉ ከሆነ ከኢህአዴግ በላይ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የፖለቲካ ዕርቅ በመጀመሪያ በተቃዋሚዎች ደጅ ሊተገበር እንደሚገባው ያሳሰበው አኢጋን፤ ይህንኑ ዕርቅ መሠረት በማድረግ ወደ ኅብረት እንዲመጡ በደብዳቤው ገልጾዋል፡፡ ወደ ኅብረት ሲመጡ የፖለቲካ ሥልጣን የመጨበጥ ዓላማቸውን ወደ ጎን መተው እንዳለባቸውና ኢትዮጵያን በማዳን ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
መግለጫው ሲቀጥልም “የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለውበጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪመሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል” በማለት በመረጃ ላይ የተደገፈ ጭብጥ አቅርቧል፡፡
ሰሞኑን የዚህ ዓመት የSEED ተሸላሚ የሆኑት ይህ የአቶ ኦባንግ የምርጫ አማራጭ ግልጽ ደብዳቤ መጪውን ሁኔታ በሚከተለው ሁኔታ ገልጾታል፤ “አገራችን በበርካታ ድሎች ያንጸባረቀ ታሪክ ያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድልየምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደአድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካውሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
በአኢጋን አድራሻና በዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ስምና ፊርማ የተሰራጨው ይህ የማሳሰቢያ ግልጽ ደብዳቤ አኢጋን በተለይ በዕርቅ ዙሪያ የሚጠየቀውን ማንኛውንም ጥያቄ ድጋፍ እንደሚሰጥ ያረጋገጠ ነው፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“ነጻነትነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም!”
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች ያስተላለፈው ግልጽ መልዕክት
የተወደዳችሁ በኢትዮጵያ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤
በቅድሚያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ በትግሉ መስክ የምትከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያደንቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ ጠብቦ የለም የሚባልበት ደረጃ በደረሰበት ወቅት በምታገኙት ስንጥቅ ሁሉ እየተጠቀማችሁ ለህዝባችሁ የብርሃን ጭላንጭል ስለምትፈነጥቁ አኢጋን ሥራችሁን ያደንቃል፤ ያከብራል፡፡ እኛ በሥራችሁ ስኬት የምንመኘው ለቆማችሁለት የፖለቲካ ዓላማ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት አቅቷቸው መፈናፈኛ ላጡትም የመወሰን ኃይል እንደምትሰጧቸው በማመን ነው፡፡
አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የበርካታዎች ጥያቄ “ህወሃት/ኢህአዴግን በምን ዓይነት የተሻለ አስተዳደር እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው?” ይህ ጥያቄ “እኛ ኢትዮጵያውያን የዘርና የጎሣ ትንንሽ አጥሮቻንን አፍርሰን ሁሉን አቀፍ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ?” ብለን ራሳችንን መልሰን አንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ እንዲሁም ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠትሁሉም ነጻ ሳይወጣ ራሳችንን ነጻ ለማውጣት እንችላለን ወይ? ብለንም እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው እንዲሁም ለመላው አፍሪካ “የሚተርፍ” እኩይ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ በማስፋፋት አገራችንን እንደዚህ ባለ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በጣለበት በአሁኑ ወቅት የብዙዎች ጭንቀት አገራችን ወደ ምን ዓይነት አዘቀት ውስጥ እየገባች ይሆን የሚለው ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ፍርሃት ወደ ተስፋ የሚቀይር አማራጭ እስካሁን ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ አማራጭ የጠፋ ይመስል ህወሃት/ኢህአዴግም “እኔ ከሌለሁ …” እያለ ያስፈራራል፤ ተቃዋሚዎችም በእርስበርስ ሽኩቻ የህዝብ አመኔታ በማጣት ወደ አለመታመን ከመሄዳቸው የተነሳ መልሶ ተዓማኒነትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀር አለ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለኢትዮጵያ ሕጋዊ አማራጭ በመሆን ለሕዝባችን መፍትሔ የምታመጡበት ወሳኝ ጊዜ አሁን መሆኑን የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
እንደምታውቁት የዛሬ ዓመት ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ነው፡፡ ምርጫውንና አመራረጡን ከሥሩ ጀምሮ የተቆጣጠረው ህወሃት/ኢህአዴግ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የሚፈለገው ተግባር ከተከናወነ በአገራችን እውነተኛ ለውጥ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ዓመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ከተገኘ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ህወሃት/ኢህአዴግን አንቅሮ ለመትፋት ከምንጊዜውም ይልቅ ዝግጁ ነው፡፡ ይህንንም የምንለው ከምንም ተነስተን ሳይሆን ድርጅታችን በአውሮጳ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ባለው የግንኙነት መስመር ከሚያገኘው ተጨባጭና ተዓማኒ መረጃ በመነሳት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ህወሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ፣ የሚከተለው እጅግ ጭቋኝ ፖሊሲ፣ በየጊዜው በሚያወጣቸው አረመኔያዊ ህግጋት፣ ወዘተ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ አደጋ የጣለና ለአህጉሩ መጥፎ ምሳሌ እየሆነ በመምጣቱ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ የመከሰቱ ጉዳይ ከምንጊዜውም በላይ አሳማኝ የሆነበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁንም ጥያቄው “ህወሃት/ኢህአዴግን ማን ይተካዋል?” የሚለው ነው፡፡ይህንን የመመለሱ ኃላፊነት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የወደቀ ቢሆንም በተለይ አገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ ልትመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ አመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ሆናችሁ የመቅረባችሁ ሁኔታ ስለምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት ከመጠየቅ ባልተናነሰ መልኩ ተጠይቆ መልስ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡
አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለእናንተ ማስረዳት የሚያስፈልግ አይመስለንም፡፡ በየቀኑ የሚፈጸመውን በደልና ግፍ መከታተል ብቻ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ በበቂ ሁኔታ የሚያመላክት ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ተቀጣጣይ (ክላስተር) ቦምብ በየቦታው የበተነው የጎሣ ፖለቲካ ፈንጂ ከፋፍሎ በመግዛት ለራሱ የሥልጣን ማቆያ ቢጠቀምበትም በአሁኑ ጊዜ አገራችንን ከላይና ከታች እያነደዳት ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን ላይ ሊፈነዳ የሚችለው ነገር ሁሉንም የሚያሳስብ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱ በፈጠረው ችግርና በበተነው መርዝ ራሱን በራሱ ሊያጠፋው እንደሚችል ከድርጅቱ ውስጥ የሚታዩት የሥልጣን ሽኩቻዎች ሁሉም “ሳይቀድሙኝ ልቅደም” በሚል አስተሳሰብ እንደተወጠረ የሚያመለክት ነው፡፡ አገራችን ነጻነቷን ከመጎናጸፏ በፊት ይህንን ዓይነቱ የህወሃት/ኢህአዴግ እርስበርስ መበላላት የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካቶች ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እናንተ ባላችሁ ኃላፊነት ይህንን በውል የምታጤኑት እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከውስጥ በሚነሳበት ግፊትና የመበላላት ስጋት፤ ከውጪ በሚመጣበት ተጽዕኖ ወይም በሁለቱ ጥምረት ከሥልጣን መወገዱ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን የሚቀበል ካልሆነም ሥርነቀል ተሃድሶ ማድረጉ እየጎመዘዘው የሚጠጣው ሐቅ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚከሰተው ለውጥ አገራችንን መልሶ መልኩን ለቀየረ በዘር ላይ ለተመሠረተ አገዛዝ አሳልፎ የሚሰጣት መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የሚመጣው ለውጥ ሕዝባችንን እውነተኛ ነጻነት የሚያጎናጽፍ፣ ፍትሕ የሚሰጥና ወደ ዕርቅ የሚመራ መሆን ይገባዋል፡፡ አገራችን በዚህ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ የማድረጉ ኃላፊነት የእናንተ እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያሳስባል፡፡
ይህ ደግሞ ሥልጣን ከመጨበጥ ባለፈ ምኞት ላይ የተመሠረተና እያንዳንዱ ነጠላ ፓርቲ ከሌሎች ጋር በኅብረት በመሥራት ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባው መሠረታዊ ዓላማ ነው፡፡ አገራችን ካለችበት ታላቅ ችግር አኳያ የፓርቲዎች መተባበርና ከተቻለም መዋሃድ ወደ መፍትሔ በሚወስደው መንገድ ላይ የመጀመሪያው ስኬት ነው፡፡ ይህ ግን በቀላሉ አይገኝም፤ ሆደ ሰፊ መሆንን፣ ከራስ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ማሰብን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከፍተኛ የመንፈስ ልዕልናን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሥልጣንን፣ የራስን ክብር፣ የበላይነትን፣ “እኔ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ” ማለትን፣ ወዘተ እያውጠነጠኑ ለአገር አስባለሁ ማለት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ከጠላት” የላቀ የመንፈስ ልዕልና ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
በመጪው ምርጫ ከምንጊዜውም በበለጠ በመጽናት ለለውጥና ለነጻነታችን የምንታገልበት ሊሆን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀውን ነጻነት ሊጎናጸፍ የሚችልበት አማራጭ ሊፈጠር እንደሚችል አኢጋን ያምናል፡፡ ይህ ሊከሰት የሚችለው በአገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቃቅን ልዩነታችሁን አስወግዳችሁ አጀንዳችሁን ሕዝባዊ በማድረግ በኅብረት ለመሥራት ስትወስኑ ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ባደረገው ጥናት አብዛኞቻችሁ ያላችሁ ልዩነት መሠረታዊ እንዳልሆነ ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው እርስበርስ ከሚያለያያችሁ ነገሮች ይልቅ ሊያስማሟችሁ የሚችሉት በርካታዎች እንደሆኑ ነው፡፡ በተለይ በአመራር ላይ ያላችሁ በተለያየ ጊዜ ከሌሎች ጋር የተከሰቱ ልዩነቶችና ግጭቶች እንዲሰፉ ምክንያት ከመሆን ይልቅ ለአገርና ሕዝብ በማሰብ ኢትዮጵያን የመታደግ ኃላፊነት ወድቆባችኋል፡፡ አገር ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም፤ እንደ ትልቅ የያዛችሁት ልዩነትና ችግርም ከንቱ ይሆናል፤ አብሮ ይከስማል፡፡
በተደጋጋሚ የሚሰማው ነጠላ ዜማ “በኢትዮጵያዊ ውስጥ ተስፋ የሚጣልበት ተቃዋሚ ፓርቲ የለም” የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ ዋንኛ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡ ምክንያቱም በአስመሳይ ዲሞክራሲና ተግባራዊ ባልሆነ ሕገመንግሥት ሕዝባችንን ከመጠርነፍ አልፎ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ሸብቧቸዋል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ያደረገ ለመሆኑ ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በኢህአዴግ ብቻ እያመካኙ መኖር ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡እያንዳንዱ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ ዓላማው የኢህአዴግን መሰሪነትና አፋኝነት ለመስበክ ሳይሆን ሕዝብን ለነጻነት ማብቃት ነው፡፡ እታገለዋለሁ ከሚለው አካል መላቅ ካልቻለ ለትግል ብቁ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ሽንፈት ላይ እያተኮሩና የጠላትን ኃይለኛነት እየሰበኩ ድል አይገኝም፡፡ ልዩነትን እያራመዱ ኅብረትና አንድነት ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ለአገራዊ ዕርቅ እንሰራለን እያሉ በፓርቲ መካከል ከዚያም በታች በግለሰብ ደረጃ መተራረቅ ካልተቻለ ብሔራዊ ዕርቅ ከቀን ቅዠት አያልፍም፡፡ እያንዳንዳችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ፣ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ ኦህኮ፣ አረና፣ እና ሌሎች እጅግ በርካታ ፓርቲዎች የተቋቋማችሁትና ዓላማ ያደረጋችሁት ኢህአዴግን እየተቃወማችሁ ለመኖር እንዳልሆነ የፓርቲ ፕሮግራማችሁ ይመሰክራል፡፡ ወይም ዓላማችሁ የራሳችሁን የፓርቲ ምርጫ የማድረግና ፕሬዚዳንት (ሊቀመንበር)፣ ምክትል፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ … በመምረጥ አዙሪት ውስጥ ራሳችሁን ላለማሽከርከር እንደሆነ ከማንም በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በጥንቃቄና በብዙ ጥናት የተቀመጠው የፓርቲያችሁ ፕሮግራምና ዓላማ ለአገራችን አንዳች ለውጥ ሳያመጣ እንደዚሁ እንዳማረበት ቢቀመጥ ለሕዝብ የሚያመጣው ትርፍ ምንድርነው? እናንተንስ ለመቃወም ብቻ የምትሰሩ አያደርጋችሁምን? ለኢህአዴግና ወዳጆቹስ ጣት የሚጠቁሙበትን ዕድል እየሰጣችሁ እስከመቼ ትኖራላችሁ? ስለዚህ የእስካሁኑ በነጠላ የመጓዙ ጉዳይ ካልሰራ በኅብረት የመሥራቱ ጉዳይ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡
የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ “ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለው በጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪ መሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል” በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ ንግግር በአገር ውስጥ ለምትገኙት ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ለምንገኘውም ልንገነዘብ የሚገባው ሐቅ ነው፡፡ ነጻነት ከምዕራቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያንም ሊመጣ አይችልም፡፡ የነጻነታችንን ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆነው እናንተ በአገር ውስጥ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኅብረት በመሥራት ሕዝባችንን ለለውጥ ስታስተባብሩት ብቻ ነው፡፡ እኛ ይህንን ከራሳችን ትከሻ ላይ ለማውረድና እናንተን በኃላፊነት ለመጠየቅ የምንጭነው ሳይሆን አገር ውስጥና ውጭ መሆናችን በታሪክም ይሁን በሌላ ምክንያት የተከሰተ በመሆኑ በቅንነትና በሐቅ የምንናገረው እውነታ ነው፡፡ እኛም ከአገር ውጭ ነን በማለት እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል የመደገፍ፣ የማገዝ፣ የምዕራባውያንን አመለካከት የማስቀየር፣ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የማሳወቅ፣ … ኃላፊነት እንዳለብን በመገንዘብ ነው፡፡ አኢጋን ይህንን ዓይነቱን ተግባር ሲያካሂድ የቆየ አሁንም ከአገር ውስጥ የሚመጣውን ጥያቄ ለመመለስና በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ሙሉ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡
ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች እንደታየውና በፓርቲያችሁ ፕሮግራም ላይ እንደሰፈረው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ተወዳድራችሁ ሥልጣን የመያዝ ዓላማ እንዳላችሁ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ማናችሁም ብትሆኑ በነጠላ ፓርቲነት ተወዳድራችሁ ሥልጣን በመያዝ ለውጥ እንደማታመጡ በግልጽ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ በምርጫ አሸነፋችሁ ቢባል እንኳን ሥልጣን የሌለው ቢሮ ከመያዝና የህወሃት/ኢህአዴግ አሻንጉሊት ከመሆን እንደማታመልጡ እሙን ነው፡፡ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ አካሄድ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም ለሚደሰኩረው የይስሙላ ዴሞክራሲ ማረጋገጫ ሆኖ በማቅረብ የኢህአዴግ ዕድሜ መቀጠያ መድሃኒት ነው የምትሆኑለት፡፡ ስለዚህ ከመጪው ምርጫ አኳያ ትግሉ የተናጠል ሳይሆን ፓርቲዎች በኅብረት በመሆን ኢህአዴግን በእርግጠኝነት ሊተኩ የሚችሉበት አማራጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በበርካታ አገሮች እንደሚታየው እናንተም በኅብረት በመሆን ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ለሕዝባችሁ ስትሉ እርስ በርስ መጠላለፍ፣ መነቋቆር፣ መካሰስ፣ ወዘተ አሁኑኑ ማቆም ይገባችኋል፡፡ በእስራኤል፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ … በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት በመመሥረት ሕዝባቸውን ታድገዋል፣ አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያስ ይህ ሊሆን የማይቻልበት ምክንያት ምንድርነው? መልሱን መመለስ የሚገባችሁ እያንዳንዳችሁ የፓርቲ አመራሮች ናችሁ፡፡
ይህ ሳይሆን የሚቀር ከሆነ በቅርቡ የፖለቲካ ታሪካችን እንደታየው በዚህም ዘመን በተመሳሳይ መልኩ ይደገማል፡፡ በዘመነ አጼ ኃይለሥላሴ የተነሳው የህዝብ ብሶት ዳር ሳይደርስ ደርግ ለራሱ አስቀረው፡፡ በደርግ ዘመን መከራውንና ስቃዩን ያየው ሕዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ “የሕዝብ ብሶት” የወለደኝ ነው ብሎ ሲመጣ የመከራው ዘመን ማብቂያው የደረሰ መስሎት ተስፋ አደረገ፡፡ “ብሶት” ወለደኝ ያለው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ታይቶ በማይታወቅ የዘር “ድንበር” ከፋፍሎ የሕዝባችንን ብሶት ለ23ዓመታት በየቀኑ እያበዛው ይገኛል፡፡ አሁንም ጥንቃቄ ወስዳችሁ ሁላችሁም ለሕዝባችን የሚሆን መፍትሔ የማታመጡ ከሆነ የሕዝባችን ብሶት እንዲቀጥል የምታደርጉ ብቻ ሳይሆን በመጪው ትውልድም ከመጠየቅ አታመልጡም፡፡
በቅንጅት ጊዜ ሕዝብ እጅግ ተስፋ አድርጎ ውጤት ሲጠብቅ ቅንጅቶች “መቀናጀት” አቅቷቸው ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው የሕዝባችን ድል ገደል ገባ፤ በራሱ ተቀናጅቶ የነበረው ሕዝብ የህወሃት/ኢህአዴግ የበቀል እርምጃ ሰለባ ሆነ፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለው ግንኙነት አሁንም ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል እያሉ ስጋታቸውን የሚገልጹልን ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ በአገራችን ላይ በርካታ ችግሮች የተጋፈጥን ቢሆንም ከፈጣሪ በኩል ግን ሁልጊዜ መፍትሔና የተበላሸውን የማስተካከል ዕድል አለ፡፡ ይህም ዕድል አሁን እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጥቂት ሃሳቦችን ለማካፈል እንወዳለን፤
  1. በምንም መልኩ በኢትዮጵያ አማራጭ ፓርቲ የለም የሚለውን ተስፋ አስቆራጭ ንግግር አትቀበሉ፡፡
  2. ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብራችሁ ልትሰሩ የሚያስችላችሁን ነጥቦች ዘርዝሮ በማውጣት በሚያስማማችሁ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተሳሰብ ልትወስዱ የምትችሉበትን መንገድ አመቻቹ፡፡
  3. በዕቅዳችሁና ከሌሎች ጋር በጥምረት በመሆን ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆን በዋንኛነት በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር የሚሰፋበትንና ዕርቅ የሚመጣበትን መንገድ ከመቀየስ ተስፋ አትቁረጡ፡፡
  4. የፓርቲ ፕሮግራምና ማኒፌስቶ ከሰማይ የወረደ፣ የማይገሰስ፣ የማይሻርና የማይለወጥ የፈጣሪ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደ ውኅደት በሚደረገው ጉዞ መሻሻል፣ መለወጥ፣ መስተካከል፣ የሚገባው የፕሮግራም አንቀጽ የፓርቲያችሁን ኅልውና አደጋ ላይ እስካልጣለ ድረስ ተፈጻሚ ለማድረግ ሆደሰፊ ሁኑ፡፡
  5. ከመሪዎች ጀምሮ በፓርቲያችሁ ውስጥ ውህደትን፣ ጥምረትን፣ … ተግባራዊ ለማድረግና በጋራ ለመሥራት ዕንቅፋት የሚሆኑ ግለሰቦችን በግልጽ መውቀስና እንዲታረሙ ወዲያውኑ ማድረግ ወሳኝነት ያለው ተግባር ነው፡፡ “እገሌን እንዴት እወቅሰዋለሁ” ወይም “አቶ እገሌ የፓርቲያችን የጀርባ አጥንት ነው እንዴት ተሳስተሃል እላልሁ” በሚሉ የይሉኝታ አስተሳሰቦች ለአንድ ሰው ሲባል አገርና ሕዝብ መከራና ስቃይ እንዲቀጥል መደረግ የለበትም፡፡ አገር ለመምራት ፓርቲ መሥርታችሁ ሕዝብን በይሉኝታ መንግሥት ማስተዳደር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ለይሉኝታ በራችሁን ዝግ ይሁን፡፡
  6. ሁልጊዜ ለመምራት ሳይሆን ለመመራት ተዘጋጁ፡፡ የሰላማዊ ትግል መሪ መመሪያ ይኸው ነው፡፡ ለመመራት የተዘጋጀ መሪ ለመሆን ምንም አይቸግረውም፡፡ ከሥልጣንህም ተነሳ ሲባል ፓርቲውን አይገነጥልም ወይም “እኔ ከሞትኩ …” በሚል ጭፍን አስተሳሰብ በሕዝብ ላይ የውድመት ተግባር አይፈጽምም፡፡ ይህ ምንም የምንደባበቅበት ነገር አይደለም በተግባር ሲፈጸም የኖረ ነው፤ መስተካከልና መሻሻል የሚያስፈልገው ነው፡፡ ከመገልገል ይልቅ ለማገልገል ትሁት ሁኑ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ትክክለኛ አስተዳደር ነው እንጂ ህወሃት/ኢህአዴግን በሌላ መተካት አይደለም፡፡ ሕዝባችን ይህ ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ስለሆነም “ኢህአዴግ ይነሳ እንጂ” የሚለው ጠባብና ሰንካላ ሃሳብ የእውነተኛ ለውጥ መርህ ስላልሆነ በጭራሽ ለሕዝባችን አትመኙለት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ የሚያስፈልገው “ከጎሣና ዘረኝነት ይልቅ ሰብዓዊነት”የሚያብብባትና “አንዱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነጻ የወጣባትን”፤ ፍትህ፣ ሰላምና ዕርቅ የሰፈነባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ከዚህ ያነሰ ለውጥ በለውጥ ደረጃ ሊታሰብም ሆነ ሊታቀድ አይገባውም፡፡
እናንተ አገር ውስጥ ሆናችሁ በየጊዜው በምታደርጉት የመስዋዕትነት ተግባር የጋራ ንቅናቄያችን ከጎናችሁ ይቆማል፡፡ ሥራችሁንም በታላቅ አክብሮት ይከታተላል፡፡ የመስዋዕትነታችሁ ውጤት ፍሬ እንዲያፈራ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በውጭ ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለን ግንኙነት ለምትፈልጉን ሥራ በምንችለው ሁሉ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናችን እንገልጻለን፡፡ በተለይ በዕርቅ መንገድ ላይ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን ይገልጻል፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ ደብዳቤ ላይ ለፕሮቶኮል ብለን የምንናገረው እንዳልሆነ እንድትረዱልን እንፈልጋለን፡፡
አገራችን በበርካታ ድሎች ያንጸባረቀ ታሪክ ያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድል የምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደ አድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካው ሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
እርስበርሳችን እንደ ወንድምና እህት ለመተያየትና ለመግባባት ፈጣሪ ቅን ልብ ይስጠን፡፡ እናንተንም ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለሰብዓዊነት፣ ለፍቅርና ዕርቅ ስትታገሉ ማስተዋልንና ጥበብን ይስጣችሁ፡፡
ከአክብሮት ጋር ለአገራችን ፈውስ እንዲመጣ የትግል አጋራችሁ፤
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

No comments: