Saturday, March 23, 2013

ባሁኑ ሰዓት በአማራው ወገናችን ላይ እየደረሰ ያለው አማራን የማጥፋት ሴራ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የሚካሄደው ተግባር ዋናው አካል ነው።

 
በአሁኑ ሰዓት አማርኛ ተናጋሪው ወገናችን ላይ መለኪያ የሌለው ግፍ እየተፈፀመበት ነው። ይህ ግፍ፤ የአማራውን ወገናችን ለማጥፋት ከሚደረግ ወንጀል ሌላ፤ መገንዘቢያ ቀመር የለውም። የዛሬው እስከመቼ ይኼን ጉዳይ ይመለከታል።

በሥልጣን ላይ ያለው ዘውገኛ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ አስተዳደሩ በዘውግ ላይ የተመሠረት ስለሆነ፤ አንደኛውን አስበልጦ ሌላውን አሳንሶ መመልከቱና በዚያ ፈለጥ ማስተዳደሩ ምንነቱ ነው። አልፎ ተርፎ ግን፤ አንድን ወገን ለይቶ፤ በዚህ ወገን ላይ የተለዬና ጭካኔ የተሞላበት በደል መፈፀም፤ መሠረታዊ ተልዕኮውን እንድንመረምር ያስገድደናል።

ዘውገኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ለምን አማራውን ለይቶ ማጥቃት ፈለገ? ለምን? የአማራው ወገን የፖለቲካ ምኅዳሩ ለኔ በተለዬ ተዘጋብኝ ብሎ አልጮኸም። በአስተዳደር የሚደርስበትን በደል ለማሰማት እጁን አላወጣም። የሚወክለውና ጥብቅና የቆመለት፤ ከአምባገነኑም ክፍል ይሁን ከዚያ ውጪ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ የለውም። ታዲያ ለምን ጥቃት ተፈረደበት?

ከኛ በኩል የሚታየን እንዲህ ነው። አማራው፤ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ብሎ፤ በሀገሪቱ ውስጥ በየትም ቦታ ሠፍሯል። በደርግ ጊዜና በዘውገኛው አምባገነን ጊዜ ደግሞ፤ አማራ የሆኑ ወገኖቻችን፤ የሚኖሩበት ቦታ መሽንሸኑና መራቆቱ ስለበዛበት፤ ከተወለዱበት ክልል ውጪ፤ በጠፍ መሬቶች፤ መሬቱን አልምተውና ከብት አርብተው ይኖራሉ። ባሁኑ ሰዓት፤ ከያሉበት እየተለቀሙ፣ ሀብታቸው እየተዘረፈ፤ አንዳንዶቹ እየታሰሩ፤ ሌሎች ደግሞ እየተገደሉ፤ ድራሻቸው እንዲጠፋ፤ በሁሉም የዘውገኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መዋቅሮች አየተዋከቡ ነው። ይህ በአማራው ወገናችን በተለይ የሚፈፀም ተግባር ነው። ይኼም የሚደረገው ኢትዮጵያዊ ነን ብለው በማመናቸውና ኢትዮጵያ የኔም ነች ብለው በመቆማቸው ነው። ታዲያ እኛ ምን እንላለን?

ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ የዘውገኛውን አምባገነን የትግሬዎች ግንባር መንግሥት እቃወማለሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን መንግሥት እንዲያቋቁም እታገላለሁና በኢትዮጵያዊነቴ ቆሜያለሁ ያልን በሙሉ፤ ሰዓቱ አሁን ነው። ይህ በደል የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በደል ነው። ይኼን በደል ተቃውሞ መነሳት፤ ለኢትዮጵያዊነት መነሳት ነው። ለዚህ ጉዳይ ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ፊትን ማዞር፤ ኢትዮጵያዊነትን መካድ ነው። ለዚህ ያልቆምን ለምን? ከዚህስ የበለጠ ኢትዮጵያዊነት ከየት ሊመጣ? አማራው አልቆ በሌሎቻችን እስኪመጡብን ድረስ ልንጠብቅ ነው ወይ?

የአምባገነኖች ሂደት ግልፅ ነው። ፋሽስቱ ሞሶሎኒ፤ በአይሁዳዊያን ተደግፎ ቆሞ፤ መጀመሪያ አጠቃቸው፤ ቀጥሎ ደግሞ የራሱን የልጁን ባል ረሸነው። ይኼ ዘውገኛ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት ደግሞ ዛሬ አማራዎች ላይ ቢዘምት፤ ነገ ተከታይ ተጠቂ ፈላጊ መሆኑን አንዘንጋ። ሌሎቻችን ቀርቶ የትግራይም ወገናችን ተራውን ጠባቂ ነው። ልብ በሉ፤ በዚህ የአማራውን ወገናችንን የማጥፋት ዘመቻው ጎን ለጎን፤ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወገናችንን ማጥቅት ይዟል። ለምን? የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠበበብን ብለው አልተነሱም። በቀላሉ ሊመለሱ የሚገባቸውና የሚችሉ ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ አቀረቡ። የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፤ በዘውግ አልተነሱም። ጥያቄያቸው ተገቢና ቀላል ነበር። ነገር ግን ሁሉን ኢትዮጵያዊያን የሚመለከት ጥያቄ ነበር። መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ ነው። ይኼ ግን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስትያን ተከታዮችም ያነሱት ጥያቄ ነው። በዚህም ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት በኢትዮጵያዊነት አሰባሰቡ። ይኼን ኢትዮጵያዊነት የሚጠላው ዘውገኛ አምባገነን ዘመተባቸው።

እንግዲህ የምንመለከተው፤ የኢትዮጵያን ዳር ደንበር ቆርሶ ለባዕድ መስጠት፣ ለሙን መሬት ባለቤቶቹን ነዋሪዋች አባሮ ለውጭ ከበርቴ አልምቶ ወደ ሀገሩ ምርቱን እንዲወስድ መስጠት፣ የተማረውን ኢትዮጵያዊ በሙሉ ማባረርና ኢትዮጵያዊ የሆነን በሙሉ ማጥቃት ትርጉሙ፤ ኢትዮጵያን ከመጥላትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከማጥፋት ዕቅድ የመነጨ ነው። እናም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የፈለገ ሁሉ ይኼን ለመቋቋም መነሳት አለበት።

ባሁን ሰዓት በአማራው ወገናችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን የወገን ማጥፋት በደል ተቃውሞ መነሳት ለኢትዮጵያዊነት መቆም ነው። ይኼን አለማድረግ ደግሞ በተቃራኒው መሆን ነው። ስለዚህ፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፤ በያለንበት የፖለቲካ ፓርቲ፣ የኅብረተሰብ ድርጅቶችና በግለሰብ፤ የአማራውን መጨፍጨፍ በመቃወም መነሳት አለብን። ይህ ጉዳይ የተጨፍጫፊው ወገናችን ጉዳይ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ነኝ ያለ ሁሉ፤ ጉዳዩ ነው።
 
 ድል ለ ኢትዮጵያ ህዝብ !!!

                                                                                          

No comments: