Sunday, March 24, 2013

ለአቤቱታ የመጡ የደቡብ ክልል ዜጎች መታገታቸው ተዘገበ

የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ለመጠየቅ በደቡብ ክልል በቁጫ ወረዳ ለአቤቱታ የወጡ ከ1000 ያላነሱ ሰዎች በፖሊስ ታግተው መዋላቸውን የአካባቢው ሰዎችን ዋቢ በማድረግ ኢሳት ዘግቧል።
እንደ ኢሳት ዘገባ ከፍትህ ፣ ከመልካም አስተዳዳር እና ከመብት እጦት ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎችን ላለፉት 8 አመታት ሲያቀርቡ የቆዩት የቁጫ ወረዳ ነዋሪዎች፣ 7 ወኪሎቻቸው መታሰራቸውን በመቃወም ትናንት አቤቱታ ለማቅረብ ሲሰባሰቡ በፌደራል ፖሊሶች መታገታቸው ከነኝህም ታሳሪ ዜጎች ድበደባ የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረበላቸው የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ክልል ተወካይና የምክር ቤት የሆኑት አቶ ዳንኤል ሽበሺ በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች የሚታየው ችግር የቆየ መሆኑን አውስተው፣ የትናንትናው ተቃውሞ ግን የሽማግሌዎች መታሰር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሳት አክሎ እንደዘገበው አቶ ዳንኤል በሰላም በር የታሰሩት ሰዎች ህዝብን ታነሳሳለችሁ ተብለው መሆኑን መግለጻቸውን በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የመልካም አስተዳደርና ፍትህ እጦት መባባሱን ጠቅሷል።
የአገር ሽማግሌዎች ለምን ታሰሩ? ለአቤቱታ የመጡ ሰዎችስ ለምን ታገቱ በማለት ኢሳት ጥያቄ ያቀረበለት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ አኒሳ ፣ ሰዎቹ ጥያቄ ያቀረቡበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል መታሰራቸውን አምኖ፣ ሰልፈኞቹ የመጡበት መንገድ ተገቢ ባለመሆኑ እንደመለሱዋቸውም ተናግረዋል ብሏል ኢሳት።

No comments: