Saturday, March 30, 2013

ርዕዮት ዓለሙ ሁለተኛ ዲግሪዋን እንዳትማር ተደረገች


ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ የርቀት ትምህርት እንዳትማር መከልከሏን የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ የርዕዮት አለሙ ቤተሰቦችም የዜናውን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡
ለፍኖተ ነፃነት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ርዕዮት እንደማንኛውም እስረኛ ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመስራት ህንድ አገር በሚገኘው የሂንድራ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅማ ብትመዘገብም ማረሚያ ቤቱ መጀመሪያ ከፈቀደ በኋላ ፖለቲካል ሳይንስ እንደምትማር ሲታወቅ ክልከላ ደርሶባታል ፡፡

የርዕዮት አለሙ እጮኛ ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ ስለጉዳዩ ጠይቀነው በሰጠን ምላሽ የርዕዮት ከዘጠኝ ወራት በፊት ትምህርቷን መቀጠል እንደምትፈልግ ለማረሚያ ቤቱ በማመልከቻ ጠይቃ እንደነበር አረጋግጧል፡፡ “ እኛ ለቱቶርና ለፈተና አንወስድሽም ግን ዩኒቨርሲቲው ፈታኝ ልኮ የሚፈትንሽ ከሆነና ቱቶር የሚሰጥሽ ከሆነ መማር ትችያለሽ የሚል ምላሽ በቃል ተሰጥቷታል፡፡ እኛም የዩኒቨርሲቲው ወኪል ከሆነው ቅ/ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር ጋር በመነጋገር ቃሊቲ ድረስ ፈታኝ ለሚላክበት ተጨማሪ አበል ለመክፈል ተስማምተን ምዝገባ አከናውነናል፡፡” በማለት የሚያስረዳው ስለሺ ሀጎስ ማረሚያ ቤቱ መስማማቱን ካረጋገጡ በኋላ ከሀያ ስድስት ሺብር በላይ ከፍለው ምዝገባውን እንዳከናወኑ ለፍኖተ ነፃነት ተናግሯል፡፡

በርዕዮት በተሰጠው ውክልና መሰረት የመማሪያ ሞጁሎች ይዞ ወደ ቃሊቲ ያቀናው እጮኛዋ ስለሺ ሐጎስ እንደሚናገረው በማረሚያቤቱ የነበረው ሀላፊ የምትወስዳቸውም የፖለቲካ ሳይንስ ሞጁሎች ርዕስ ካነበበ በኋላ አናስገባልህም ተብሏል፡፡

ከክልከላው በፊት ሁለት የማይታወቁ ሰዎች የሂንድራ ጋንዲ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ወኪል ወደሆነው ቅ/ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመሄድ “የርዕዮትን ሞጁል አምጡ” ማለታቸውን ጨምሮ የገለፀው ጋዜጠኛ ስለሺ በማረሚያ ቤቱ ክልከላ እንዳዘነ ለፍኖተ ነፃነት ተናግሯል፡፡
ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንዳለ በፍኖተ ነፃነት የተጠየቁት ወላጅ አባቷ ጠበቃ ዓለሙ ገቤቦ በሰጡት መልስ “ እውነት ነው፤ አንቺ እንድትማሪ አንፈቅድም ብለው ከልክለዋትል፡፡ በመሠረቱ አንድ በህግ ጥላ ስር ያለ እስረኛ ቀዳዳ እየተፈለገ መብቱን መንፈግ ተገቢ አይደለም፡፡ ምዝገባው ሲደረግና ሂደቶቹ ሲከናወኑ ፈቅዶ ትምህርቱ ሲጀመር መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ችግሩን መፍታት የሚችል አካል ካለ አመልክተን ትምህርቷን የምትቀጥልበት መንገድ እንሞክራለን፡፡” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ርዕዮት በቅርቡ ይቅርታ ጠይቃ እንድትፈታ በሽማግሌዎች ተጠይቃ ምንም ባልፈፀምኩት ወንጀል ይቅርታ አልጠይቅም የተፈረደብኝን ፍርድ እስር ቤት እጨርሳለሁ ብላ እንቢ በማለቷ ተደጋጋሚ አስተዳደራዊ በደል እየተፈጸመባት ይገኛል፡፡ በጡቷ ላይ በተፈጠረባት ህመም ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፖታል ሪፈር ብትባልም መኪና የለም አጃቢ አልተገኘም በሚል ምክንያቶች ህክምናው መስተጓጎሉ ይታወሳል፡፡

No comments: