Friday, March 15, 2013

“ከምድር በታች ጨለማ ቤት ውስጥ የታሰሩትን በቀን ለ10 ደቂቃ እናያቸዋልን።ስዊድናዊ የፍሪላንሰር ጋዜጠኛ ማርቲን ካርል ሻቢዬ በኖርዌይ ኦስሎ

    
the meeting
“ከምድር በታች ጨለማ ቤት ውስጥ የታሰሩትን በቀን ለ10 ደቂቃ እናያቸዋልን። ልብ የሚነካ ነው። የብርሃን ማነስ አይናቸውን እንደጎዳቸው ያስታውቃሉ … ሴቶችን በተገኘው ሰበብ ያስሯቸዋል። ምክንያት ፈልገው እስር ቤት ይከቷቸዋል። ከዚያም ይደፍሯቸዋል። በርካታ የተደፈሩ እህቶች አሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና መንግሥት ያሰማራቸው ሚሊሻዎች ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንደፈጸሙ ተነግሮናል” ይህ ማዕከላዊ እስር ቤት ታስሮ፣ ችግሩ ባለበት ቦታ ተገኝቶ የነበረው ስዊድናዊ የፍሪላንሰር ጋዜጠኛ ማርቲን ካርል ሻቢዬ ቃል ነው።
ስለ ማዕከላዊ እስር ቤት መስማት ይጨንቃል። ሰዎች በሲቃ የሚያሰሙት የጣር ድምጽ ለጆሮ የተለመደ ነው። ከመሬት በታች የጨለማ ክፍል አለ። በዚህ መታጎሪያ ውስጥ ሆነው ስቃይ የሚፈራረቅባቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ማዕከላዊ ብዙ ጉድ ያለበት ሲኦል ነው። የሰው ልጆች በግፍ ማቅቀውበታል። እየማቀቁበትም ነው። ለውጥ እስከሌለ ድረስ የሚቆም አይመስልም። በመሃላ የሚነገርለት ውርስና ይቀጥላል የሚባለው የመለስ ራዕይ አንዱ ክፍል ይህ ነው።
መጋቢት 3፤2005 (3/12/2013) በኖርዌይ ኦስሎ የሥነጽሁፍ ቤት (ሊትሬቸር ሀውስ) በተዘጋጀ የመወያያ መድረክ ላይ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ተገኝተው ነበር። መድረኩን ያዘጋጀው ደግሞ NOAS በሚል ስያሜ የሚታወቀው የስደተኞች ተሟጋች ድርጅት ነው። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አን-ማግሬት ኦስቴና ሁለቱን እንግዶች ካስተዋወቁ በኋላ መድረኩን እየመሩ ውይይቱ ተካሄደ። በዚህ ውይይት ላይ ሁለቱ ጋዜጠኞች እየተፈራረቁ የደረሰባቸውንና በትክክል ያዩትን አስታወቁ።
ማርቲን ካርል ሻቢዬና ባልደረባው የፎቶ ጋዜጠኛ ጆሃን ካርል አበክረው የሚናገሩት ስለ ሙያቸው ነው። “ጋዜጠኛ ለመጻፍ ማየትና ማነጋገር አለበት። በተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ገብተው ለመዘገብ ድንበር ያቋርጣሉ። አሁን በሶሪያ፣ ቀደም ሲል በሊቢያ የሆነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ግን ሽብርተኛ ያሰኛል” ሲሉ ግርምታቸውን ይጀምራሉ።
የ19 ዓመት ወጣት ነው። ስራዉ ሹፍርና ሲሆን “ኦነግ ነህ” ተብሎ ነው የታሰረው። መርማሪዎች ባዶ ወረቀት እየሰጡ ስለ ኦነግ ጻፍ ይሉታል። ምንም የሚያውቀው ነገር ስላልነበር መጻፍ አልቻለም። በመጨረሻ ራሳቸው ጽፈው አዘጋጅተው በራስህ እጅ ጽሁፍ ገልብጥ አሉት። እናም የተባለውን ፈጸመ። ጋዜጠኞቹ ብዙ መረጃ አላቸው። እነሱንም ያልሆኑትንና ያላደረጉትን አድርገናል እንዲሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። “በሶማሊያ አምስት ዓመት ተቀምጫለሁ እንድል አስገድደው አሳመኑኝ” በማለት ጆሃን ካርል ገለጸ።

ወ/ሮ ዙፋን አማረ
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ ሊቀመንበር ወ/ሮ ዙፋን አማረ እንደሚሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ኖርዌይ እንዲመጡ ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር ከመነጋገር ጀምሮ ማህበራቸው የበኩሉን ስለማድረጉ ይናገራሉ። ይህ እንዲሆን የታሰበው ደግሞ ጋዜጠኞቹ በትክክል ያዩትንና የደረሰባቸውን ለኖርዌይ ባለስልጣናት በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያስተካክሉ የሚደረገውን የቅንጅት ትግል ለማጠናከር እንደሆነ ወ/ሮ ዙፋን ያስረዳሉ።
ሁለቱ ጋዜጠኞችም ያሰመሩበት ጉዳይ ይህንኑ ነው። ኖርዌይ የመጡበት ዋናው ምክንያት ከተለያዩ ፖለቲከኞች፣ አግባብ ካላቸው መስሪያ ቤቶችና ከዋናው ፓርላማ በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል። በርግጠኛነት ባለስልጣናቱ ያገኙትን መረጃ ለመልካም ይጠቀሙበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሙሉዓለም
ኢትዮጵያዊያን ባሉበትና የስደተኞች ጉዳይ በሚነሳበት ሁሉ የማይጠፉት ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም የኢትዮጵያ መንግስት ስለሚፈጽመው በደልና ግፍ ለማስረዳት ብዙ መደከሙን፣ እነሱም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ምን አይነት መንግስት እንደሆነ እንደሚያውቁ፣ መንግስትም ራሱን ሊሰውር ቢል የሚፈጽመው ተግባሩ ከግብሩ ሊሰወር እንደማያስችለው በሚያስረዳ መልኩ አስተያየት ከሰጡ በኋላ “”እነዚህን ሰዎች እኮ አቁሙ የሚላቸው የለም። የምታውቁትን ያስረዳችኋቸው ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ምን ምላሽ ሰጡ?” የሚል ሁሉንም የሚወክል ጥያቄ አቀረቡ።
በተደራራቢ ስብሰባና በውይይት መዳከማቸውን የገለጹት ሁለቱ ጋዜጠኞች “የኖርዌይ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ያገኙትን መረጃ ለበጎ ይጠቀሙበታል የሚል እምነት አለን” በማለት መልስ ሰጥተዋል። ስለ አውሮፓና አሜሪካ ዝምታ ለተጠየቁት የመለሱት አሸባሪነትን በመዋጋት ስም ከፍተኛ ገንዝብ እንደሚገኝ በመግለጽ ነው። በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካው መልክ የተወሳሰበ በመሆኑ ኢህአዴግም ይህንኑ እንደሚጠቀምበት አመላክተዋል። አሜሪካንና እንግሊዝን ኮንነዋል።
ስለ ኢህአዴግ የስለላ መረብና በስደት ላይ በሚገኙ ወገኖች ላይ ስላሰማራቸው ጆሮ ጠቢዎች አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አገር ቤት ያስተዋሉትንና ያላቸውን መረጃ በማጣቀስ አድማጮችን አስፈግገዋል። በካፌና ተራ መዝናኛ ቦታዎች ጆሮ ጠቢዎች እንደሚሰማሩ፣ ሰዎች ሻይ እየጠጡ የሚያወሩትን እንደሚለቅሙ፣ በመገረም ተናግረዋል። ስደተኞችን መሰለልና መቆጣጠር አደገኛ ወንጀል እንደሆነ በሃዘን ስሜት አስረድተዋል።
እስር ቤት “ግምገማ አለ” በማለት ግምገማ የምትለዋን የአማርኛ ቃል ተጠቅመው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እስር ቤት ውስጥ ባለው ግምገማ 100 ነጥብ የሚያገኙ ይቅርታ እንደሚያገኙ፣ 10 ወይም ከዚያ በታች የሚያገኙ ደግሞ ተቃራኒው እንደሚተገበርባቸው እየሳቁ የኢህአዴግን የቆሸሸ አካሄድ ተናግረዋል።
የኖርዌይ PEN (ፔን) ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሊሳቤጥ ኤዲ “በሽርክና ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ” ሲሉ የጠሩትን የአገራቸውንና የኢትዮጵያን ግንኙነት የገለጹት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እንደሚመላለሱ መግለጽ ነው። እርሳቸውን ተከትሎ አቶ ዳዊት መሰረታዊ ጉዳዮችን አንስተው ጥያቄ የሰነዘሩ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ውስጥ መርማሪዎቹ እርስ በርስ የሚነጋገሩበት ቋንቋ በኢትዮጵያ ከሚነገሩት ቋንቋዎች የትኛው እንደሆነ እንዲያስረዱ ያቀረቡት ጥያቄ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውና አፈናውን የሚያካሂዱትን ቡድኖች የሚያጋልጥ በመሆኑ ከስብሰባው በኋላ መነጋገሪያም ነበር። የጎልጉል ዘጋቢ ያነጋገራቸው አንድ የኖርዌይ ተወላጅ በጥያቄው መነሳት መገረማቸውን አስረድተዋል። ጥያቄው የቀረበላቸው ጋዜጠኞች ግን በተለይ ቡድን ለይተው አልመለሱም። ይሁንና በቅርቡ በሚያሳትሙት መጽሃፍ ብዙ ጉዳዮች እንደሚነሱ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌዲዮን ደሳለኝ ስለ እስክንድር ነጋ አንስተው ነበር። የማህበሩ ጸሐፊ አቶ ቢኒያም በውይይቱ ላይ ከተገኙት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ ሊቀመንበሯ ወ/ሮ ዙፋን በማህበራቸው ስም ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ ከሰብአዊ መብት መጣስ ጋር በተያያዘ ጥያቄ አንስተው ነበር።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስቀድሞ በመታሰሩ የመገናኘት እድል እንዳላገኙ ያስረዱት ሁለቱ ጋዜጠኞች፣ ርዕዮት ዓለሙን እንዳገኙዋት፣ መነጋገር ስለማይቻል በምልክት ለመግባባት ይሞክሩ እንደነበር አስታውሰዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም “እነዚህ ጋዜጠኞች የታሰሩት በመጻፋቸው ነው። የተከሰሱት ስለጻፉ ነው። ጋዜጠኞቹ ሲጽፉ ይህ እንደሚደርስባቸው ያውቁ ነበር። ሃላፊነቱን ራሳቸው ወስደው ጻፉ። አገራቸውን ስለሚወዱ፣ ሙያቸውን ስለሚያከብሩ፣ ህዝባቸውን ስለሚያፈቅሩ አደረጉት። ለነሱ ልዩ ክብር አለን” ብለዋል፡፡
“እስር ቤት እያለን አንድ ስጋት ነበረን” አሉ የስዊድን ጋዜጠኞች “ፍርሃታችን የስዊድን ጋዜጦች ስለኛ መጻፍ እንዳያቆሙ ነበር። የስዊድን ሚዲያዎች ስለኛ መጻፍ ካቆሙ እንረሳለን። መወያያ አጀንዳ የምንሆነው ካልተረሳን ብቻ ነው … ” በማለት የሚዲያን የመቀስቀስ ኃይል አጉልተው አሳይተዋል። አሁን በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች “ከመቃብር በታች ናቸው” በማለት ሁሉም ሚዲያዎች ሊረሷቸው እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ውድ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ነጻ ፕሬስ ከሌለ ለአገር አደጋ ነው። ነጻ ፕሬስ የሌለበት አገር አስተማማኝ መረጋጋት አይኖርም” ሲሉ የነጻ ሚዲያን አስፈላጊነት አስምረውበታል።
ጋዜጠኞቹ መጽሃፋቸውን በቅርቡ ጽፈው ለህትመት አስኪያበቁ ድረስ ዝርዝር ጉዳዮች በሚዲያ ላለመስጠት መወሰናቸው አስቀድሞ በስብሰባው አዘጋጆች በመነገሩ የሪፖርቱ አቅራቢ በዚህ ሊገደብ ችሏል። ስለሃብት ስርጭትና ሞኖፖሊ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበውን ጥያቄ ጨምሮ ሰፊ ጉዳዮች በስብሰባው ላይ ተነስተው ነበር።
ተጋባዦቹ ጋዜጠኞች ፊትለፊት አውጥተው ባይናገሩም እስር ቤት ሆነውና፣ ኦጋዴን በአካል የታዘቡትን፣ እንዲሁም በግል ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት በቅርቡ የሚያሳትሙት መጽሃፍ ታላቅ ዋጋ ያላቸው መረጃዎች የተካተቱበት እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው። መጽሃፉ የሚታተምበት ትክክለኛ ጊዜ ባይታወቅም መጽሃፉ ከመረጃ ሰጪነቱና ኢህአዴግን ከማጋለጡ በተጨማሪ መንታ አላማ ማንገቡ የተገለጸው ሰዎቹ ከእስር እንደተፈቱ ነበር።
“በርግጥ ከእስር በመለቀቃችን እድለኞች ነን። ሆኖም ግን አዕምሯችን እረፍት አላገኘም። ምክንያቱም ብዙ ባልደረቦቻችን አሁንም እዚያው እስር ቤት ናቸው። የእስር ቤት ባልደረቦቻችን ባብዛኛው በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳሉ ራሴን እጠይቃለሁ። እስር ቤቱ ጥሩ ስፍራ አይደለም። እንዲህ ባለ እስር ቤት ውስጥ መሞት ቀላል ነው። እኛ ከመንግስታችን ባገኘነዉ ትልቅ ድጋፍ ነጻ ወጥተናል። በርካቶች ግን አልታደሉም። ባልደረቦቻችን እዚያው ናቸው። አሁንም እዚያው ናቸው” ይህ ቃል ከእስር በተፈቱ ማግስት የተናገሩት ነው። ይህ ብቻም አይደለም በስማቸው የርዳታ ድርጅት በማቋቋም የህግ፣ የመድሃኒት፣ የእስረኞቹን ቤተሰቦች በገንዘብ ለመርዳት ቃልም ገብተው ነበር።
አትረሱ! ሚዲያ አይርሳችሁ! በሚዲያ መረሳት ሞት ነው! ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር አደጋ ውስጥ ነው! ነጻ ክርክርና ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ አይደለም። ነጻ ሃሳብና ነጻ ህዝብ መፈጠር አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩም ሆነ በማንነቱ ለነጻነት አዲስ አይደለም። በእስር ለሚማቅቁ መጮህና ደጋግሞ ያለመሰልቸት መከራከር የሚዲያዎች ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። እስረኞች ሲባሉ ደግሞ ሁሉንም ነው። በሚዲያ አትረሱ! ሚዲያ ያልደረሰላቸው ወገኖች የሚዲያ ያለህ የሚሉ ወገኖች አንደበትና ጠበቃ ከመሆን በላይ ታላቅ ስራ የለም። ብዙ የተረሱ አሉ።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments: