Monday, March 4, 2013

የሸሪያ ፍርድ ቤት” በጅጅጋ የአማራ ተወላጆችን ሰለባ አደረገ



ካለፉት አርባ ዓመታት ጀምሮ በሶማሊ ክልል በጅጅጋ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ቤቶቻቸውን እያስረከቡ ለጎዳና ህይወት እየተዳረጉ መሆናቸውን ኢሳት አስታወቀ።
 እስካሁን ድረስ በከተማዋ ውስጥ ዋና ዋና የንግድ ቦታዎች የነበሩዋቸው የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ንብረታቸውን ...ለክልሉ ተወላጆች እንዲያስረክቡ በመዳረጋቸው ብዙዎች ድርጅቶቻቸውን አስረክበው ወደ መሀል አገር ሄደዋል በማለት ኢሳት የዘገበው የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ ም ነው። ተወልደው ያደጉበትን ቦታ አንለቅም በማለት እስካሁን የቆዩትም በተለያዩ አስተዳዳራዊ ጫናዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ በደብዳቤ እና በቃል ተነግሯቸዋል።
በጅጅጋ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ለኢሳት በጻፉት ደብዳቤ “የአንድ ብሄር የበላይነት በሰፈነበት መልኩ አማራ ወይም ሀበሻ የሚል መጠሪያ ተደርጎልን እነሆ ከህጻናት እስከ ትልቅ በመንገድም በቢሮም እየተሰደብንና እየተተፋብን መኖራችን ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ ያለምንም ልዋጭ ቤታችን ተቀምቶ ጎዳና ላይ ተጥለን እንገኛለን” ብለዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም “የእኛ ልጆች እንደልብ በመንገድ ላይ መሄድ አይችሉም፣ ሱሪ የለበሰች ሴት በፖሊስ ዱላ ትደበደባለች፣ ማን ፖሊስ ማን ሀላፊ እንደሆነ በማናውቀው ሁኔታ፣ የሸሪያ ፍርድ ቤት የሚል ተቋቁሞ ቤታችንን እንድንለቅ እያስገደደን ነው። ተወልደን ባደግንበት አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንደቆሻሻ እየታየን ነው” ብለዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የከተማው ነዋሪ በክልሉ የመኖር ተስፋቸው መሟጠጡን ተናግረዋል። ኢሳት በጅጅጋ ከተማ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል በተደጋጋሚ መዘገቡንና መንግስትም ዝምታ መምረጡን አስታውቃል።

No comments: