Tuesday, March 12, 2013

የህወሓት ጉባኤ ምልመላ ፈተና ገጠመው

ባለፈው በህወሓት ኣመራር በተፈጠረው ኣለመግባባት ምክንያት ሌላኛው ቡድን ለማሸነፍ ሲባል የነ ኣባይ ወልዱ ቡድን በተመረጡ የትግራይ ከተሞች በመንቀሳቀስ ለህወሓት ጉባኤ የሚሳተፉ ታማኝ የተባሉ፣ የደም ትሥሥር ያላቸው፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆኑና በህወሓት ታሪክ የመቃወም መንፈስ ኣሳይተው የማያውቁ ካድሬዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ መመልመላቸው ፅፌ ነበር።

ኣሁን ከህወሓት መንደር...ያገኘሁት መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ኣባይ ወልዱ የመለመላቸው የጉባኤ ተሳታፊዎች በሌሎች የህወሓት ኣባላት ፈተና ገጥሟቸዋል። በጉባኤው ለመሳተፍ ያልተመለመሉ የህወሓት ኣባላት (በነ ኣርከበ ዕቁባይ ደጋፊዎች ተነሳሽነት በመታገዝ) ያኮረፉ ሲሆን በተሳታፊዎች ምልመላ ወገንተኝነት ጥያቄ ኣስነስተዋል።

እነዚህ ያልተመለመሉ የህወሓት ኣባላት የምልመላው ሂደት በመቃወም በነ ኣባይ ወልዱ በተመለመሉ (በጉባኤው እንዲሳተፉ በተመረጡ ኣባላት) ላይ የተናጠል እርምጃ እንደሚወስዱና ቡድኑ ካሸነፈ ከህወሓት ኣባልነታቸው ራሳቸው እንደሚያገሉ ኣሳውቀዋል። የተመለመሉ ኣባላትም የተለያየ ዛቻና መገለል እየደረሰባቸው በመሆኑ ብዙዎቹ በጉባኤው ለመሳተፍ እንደ ማይፈልጉ እያሳወቁ ይገኛሉ።

ይሄንን በጉባኤው ለመሳተፍ ያለመፈለግ ጉዳይ የህወሓት ኣመራሮች እንቅልፍ ያሳጣቸው ሲሆን በኣሁኑ ሰዓት (ሌት ተቀን) በስብሰባና እርስበርስ ግምገማ ተጠምደዋል። የስብሰባው ኣጀንዳ፡ ‘ለምንድነው እነዚህ የተመለመሉ ኣባላት በጉባኤው ላለመሳተፍ የወሰኑ?’ የሚል ነው።

በግምገማው፡ እነዚህ የተመለመሉ ኣባላት፡ ለምን መሳተፍ እንዳልፈለጉና ማን እንዳስገደዳቸው ይጠየቃሉ። ከዛ እንዲሳተፉ ይመከራሉ። ምክሩን ካልሰሙና ለመሳተፍ ፍቃደኛ ካልሆኑ ግን በተቃዋሚነት ተፈርጀው ከሓላፊነታቸውና ከስራ ገበታቸው እንደሚባረሩ ይነገራቸዋል።

በትእምት ኩባኒያዎች ግምገማው እየተካሄደ ነው። በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለምሳሌ ግምገማውና ኣለመግባባቱ ቀጥሏል።

በመላ ትግራይ ተቃውሞ ስላየለባቸው፣ የነ ኣባይ ወልዱ ቡድን ‘መተካካት’ የተባለው መርህ እንደሚተገብርና ስልጣን ለወጣት ተተኪዎች እንደሚያስረክብ የተናገረበት ‘ሁኔታ ነው ያለው’። (የፖለቲካ ቀውሱ እየተባባሰ በመሄዱ የመተካካት ጉዳይ እንዲያነሱ ተገደዋል።) ስለዚ ከሁለቱም ቡድኖች ከስልጣን የሚወገዱ ነባር ኣመራሮች ይኖራሉ ማለት ነው።

ችግሩ ለማቃለል ሲባልና የህዝብ ድጋፍ (ኣመኔታ) ለማግኘት በሚቀጥለው ቅዳሜ (መጋቢት 7, 2005 በጉባኤው ዋዜማ መሆኑ ነው) በመቀሌ ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ይጠራል። የህወሓት የ21 ዓመት ጉዞ በትእምት ተሽከርካሪዎች ታጅቦ ለህዝብ ይቀርባል። ለህዝቡ “ኣለን፣ ኣልሞትንም፣ ድጋፋቹ እንዳይለየን” የሚል መልእክት ለማስተላለፍና ዉስጣዊ ችግራቸው ለመሸፈን ታልሞ ነው።

በሦስት ቀናት እንዲጠናቀቅ ታስቦ የነበረው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ወደ ስድስት ቀናት ይፈጃል። ሌሎች ከዚህ በፊት ያልተያዙ ኣጀንዳዎችም ተጨምረዋል። በዚ መሰረት ጉባኤው መጋቢት 8 ማታ ተጀምሮ በ 13 ይጠናቀቃል ተብሎ መርሃ ግብር ወጥቶለታል።

እኔም በድርጅታዊ ጉባኤያቸው ዋዜማ ‘የህወሓት መሪዎች ሆይ ! እባካቹ ለህዝብ ቅድምያ ስጡ፤ ፍትሕ ኣስፍኑ፣ በቅንነት ህዝብን ኣገልግሉ (ለስልጣናቹ ከመኖር ይልቅ)። የሚል መልእክቴን ኣስተላልፋለሁ።

ለመረጃ ያህል፡

እነ ኣባይ ወልዱ በመተካካት ስም ‘የተማረው የህወሓት ኣባል’ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው። ኣብዛኛው ሙሁር ኣባል ይደግፋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን በቡድኑ መሪዎች ኣንድነት የለም። ለምሳሌ ኪሮስ ቢተው መጀመርያ ከነ ኣባይ ወልዱ ቡድን የነበረ ሲሆን የኣባላቱ ተቃውሞ ከተገነዘበ በኋላ የመሃል ሰፋሪነቱ ቦታ ተረክበዋል።

ኣዲስ ኣበባ የሚገኙ የህወሓት ኣባላትና የደህንነት ሰራተኞች ግን የነ ኣርከበ ዕቁባይ (ወይ ደብረፅዮን) ቡድን ደጋፊዎች ናቸው። ትግራይ ዉስጥ ያሉ ኣባላት ግን ፍርሓት ውስጥ ናቸው። ማንን መደገፍ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል።

ኣብዛኞቹ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላትና የድሮ ባለስልጣናት የነ ኣርከበ ቡድን ሲደግፉ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በረከት ስምዖን፣ ኣዲሱ ለገሰና ኩማ ደመቅሳ የነ ኣባይ ወልዱ ደጋፊዎች ሁነዋል።

የከረረ ጠብ ያለ በኣዜብ መስፍና ኣርከበ ዕቁባይ ሲሆን በኣባይ ወልዱና ደብረፂዮን ገብረሚካኤል መካካልም ከፍተኛ ኣለመግባባት ኣለ። ስብሓት ነጋና በረከት ስምዖንም ኣይዋደዱም።

በኣሁኑ ሰዓት የህወሓት መሪዎች (የሁለቱም ቡድኖች ተወካዮች) በመቀሌ ከተማ ተሰብስበው እየተነታረኩ (እየተጨቃጨቁ) ይገኛሉ። መግባባት ባለ መቻላቸው ከኣዲስ ኣበባ የመጡ እነ ኣርከበ ዕቁባይ የሚንቀሳቀሱበት መኪና ኣልተሰጣቸውም። በእግርና በቤተሰብ መኪና ይንቀሳቀሳሉ።

No comments: