Tuesday, March 19, 2013

ኢህአዴግ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተነክሯል

ኢህአዴግ በዘር ማጥፋት ወንጀል መነከሩ በተግባር በተደጋጋሚ እየታየ ነው። በተለይም አማርኛ በሚናገሩ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ወንጀልና ወንጀሉን የሚፈጽሙትን ክፍሎች የሚገስጽ መጥፋቱ ጉዳዩን እያወሳሰበው ነው። ኢሳት መኢአድ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው “በቋንቋ ማንነት ህዝብን መግደል፣ ማፋናቀል እና ማሰር የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተናገሪ ማህበረሰብ ላይ የተከፈተው ማፈናቀል፣ በጅጅጋ እና በአፋርም የቀጠለ ሲሆን በመላው አገሪቱ የአማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ቤት እንዳይኖረው፣ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንዳይሳተፍ በተለያየ ስልት ድሃ ሆኖ በጎዳና እንዲበተን የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ትእዛዝ የሰጡ ሲሆን በአዲስ አበባ ከፈረሱ እና እያፈረሱ ካሉ ቤቶች አብዛኞቹ የአማራ ተናጋሪዎች መኖሪያ መሆናቸውን መታዘቡን ገልጿል። የባንክ ብድርን መከልከልን ጨምሮ መሬት እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ ከፍተኛ ግብር እየተጫነባቸው ከንግድ ስርአቱ እንዲወጡ መደረጉን መኢአድ አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ ከ200 በላይ ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በባህርዳር ያለመጠለያ በጎዳና እየኖሩ መሆኑን መኢአድ በመግለጫው አመልክቷል። በባህርዳር ለጎዳናና ተዳዳሪነት ከተዳረጉት መካከል ብዙ ነፍሰጡሮችና ህጻናት እንደሚገኙበትም ገልጿል።
አማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ በብሄራዊ ጨቋኝነት በመፈረጁ በአርባ ጉጉ ፣ በበበደኖ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በጋምቤላ እንዲጨፈጨፍ ሲያደርጉ አገዛዙ ምን ያክል የአማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ለማጥፋት እንደተፈለገ አመላካች መሆኑን የጠቀሰው መኢአድ፣ ከአንድ አመት በፊት በቤንች ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ በከፍተኛ ጭካኔ በአማርኛ ተናጋሪ አርሶአደር ፣ ሴቶች፣ ነፍሰ ጡር፣ ህጻናት እና ሽማግሌዎች ላይ የተጀመረው ጭካኔ የተሞላበት ስደት ተባብሶ ቀጥሎ በየጎዳናው የሚጣለው የኔቢጤ ከመሆን አልፎ ለአውሬና ለአሰቃቂ ኑሮ የተጋለጠው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ በቤንሻንጉል ፣ በጅጅጋ፣ በአፋር እና በአንዳንድ የአሮሚያ ክልል እየቀጠለ ነው ብሏል፡፡
መኢአድ “ማንኛውም ሰው በቋንቋው ፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣ በቀለሙ እና በማንኛውም ልዩነት ምግብ ሲያጣ ፣መጠለያ ሲነፈገው ፣ጨቅላ ህጻናት በየጎዳናው ሲሞቱ፣ ነፍሰጡሮች በየበረንዳው ሲወድቁ፣ ህሊናን የሚያደማ መሆኑን ገልጾ” ይህንን ጨቋኝ ስርአት በአለም ህዝብ ፊት በዘር ማጥፋት ወንጀል ልንከሰው ይገባል” ማለቱን የኢሳት ዜና ያስረዳል።

No comments: