Saturday, March 2, 2013

የስዑዲ ማስጠንቀቂያና የኢትዮጵያ ምላሽ

    
ሰሞኑን አንድ ከፍተኛ የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣን ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ የተነሳ በግብጽና በሱዳን የአባይ ወንዝ አጠቃቀም መብት ላይ አደጋ እየጣለች ነው ማለታቸውን ሱዳን ትሪብዩን የተሰኘው ድረ ገጽ ዘግቧል። ባለስልጣኑ የተናገሩት የሳውዲ አረቢያ መንግስት
አቋም መሆን አለመሆኑን አጣርቶ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን መግለጫ እንደሚያወጣ ተዘግቧል። ሱዳን ትሪብዩን የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ የሳውዲ አረቢያ ምክትል የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልታን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለው ፕሮጀክት፣ ግብጽና ሱዳን በወንዙ ላይ ያለቸውን መብት አደጋ ላይ እንደሚጥል መናገራቸው ተሰምቷል። ከሱዳን ድንበር 12 ኪሎሜትር ርቆ እየተሰራ ያለው የህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ለፖሊቲካ አሻጥር የሚያገለግል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተባለው ዜና የሳውዲ አረቢያ መንግስት አቋም መሆኑን አጣርቶ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፣
ይህ በሰባ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በመሰራት ላይ ያለው ግዙፍ የግድብ ፕሮጀክት ተፋጥኖ እየጨመረ ያለውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመመገብና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም እንደሚረዳ የኢትዮጵያ መንግስት ይናገራል።
ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ጥሩ የኦኮኖሚ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው። በርካታ የሳውዲ አረቢያ ባለጸጋዎች መዋለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሳሉ። ታዋቂው የኢትዮጵያ ባለሐብት ሼ ሞሐመድ አል-አህሙዲም የሳውዲ አረቢያ ዜግነት አላቸው።

ኢትዮጵያ በአብዛኛው ለቤት ውስጥ ሥራዎች ብዙ ሰራተኞችን በየዓመቱ ወደ ሳውዲ አረቢያ ትልካለች። የምክትል መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን መግለጫ ኢትዮጵያ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ካላት ከዚህ ትስስር ጋር የማይሄድ ነው ይላሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤

በግብጽ የፕሬዞዳንት ሙርሲ መንግስት ስልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ በሳውዲ አረቢያና ግብጽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ይነገራል። የብሪታኒያውያኑ የፖሊቲካ ጥናት ተቋም ቻተም ሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ የፖሊቲካ አዋቂ ጃተም ሞስሊ እንዳሉት የሳውዲ አረቢያ መንግስት የአባይ ወንዝ ጉዳይ አይመለከተውም ማለት ይከብዳል፤


«የግብጽ የውሃ ጉዳይ ለግብጽ ብሔራዊ ጸጥታ በጣም አስፈላጊ ነው። የአሁኑ የግብጽ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ግብጽና ሳውዲ አረቢያ ግንኙነታቸውን አሳድገዋል። ግብጽ ለሳውድ አረብያ ቅርብ ሀገር ናት። ስለዚህ በግልጽ እንዲህ ነው ባይባልም፣ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የሳውድ አረቢያ ፍላጎት የለበትም ማለት አይቻልም።»

ግብጽ የአረቡን አቢዮት ተከትሎ በተከሰተው የውስጥ አለመረጋጋት ምክንያት በምስራቅ አፍሪቃ ያላት የፖሊቲካ ተጽዕኖ ቀንሷል። ሱዳንም የደቡብ ሱዳንና የዳርፉር ችግሮች ፊቷን ከአከባቢው ፖሊቲካ እንድታርቅ አድርጓታል። በሌላ ኢትዮጵያም የአባይ ወንዝ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በብርቱ እየገፋች ነው።
በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ንትርክ ከተጀመረ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ሆኖታል። ግብጽ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ እአአ በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ትፈልጋለች።


ኢትዮጵያና የላይኛው አባይ ተፋሰስ ሀገራት ግን ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምንነት እንዲፈረም ይሻሉ። እአአ በ2010 ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አራት የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በአባይን ውሃ ክፍፍል ላይ በዩጋንሳ ኢንቴቤ ከስምምነት ደርሰዋል። ከአንድ ዓመት በኋላም ጎራውን ተቀላቅላለች።

No comments: