Friday, August 29, 2014

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ፈተና

August29,2014
betre-yakob
Betre Yacob – president of Ethiopian Journalists Forum
(ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ጋዜጣ የነሐሴ 14 እትም)
“የኢትዮጵያ መንግስት በግል ፕሬሱ ላይ የተቀነባበረ የጥፋት ዘመቻ ጀምሯል፡፡ ያሁኑ እርምጃ ቀደም ሲል ከተወሰዱት አስከፊ ፀረ-ፕሬስ እርምጃዎች የሚለየው ከ2007ቱ ምርጫ በፊት የተጀመረ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
በዚህ በአሁኑ እርምጃ አንድ የጋዜጠኞች ማኅበርን ጨምሮ፣ በአንድ የጦማሪያን ስብስብ ላይ እና በአምስት መፅሔቶች እና አንድ ጋዜጣ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ እርምጃው እንደተለመደው ሕገ መንግስታዊ ሽፋን በመስጠት የተካሄደ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ መንገዶች የተቀነባበረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ገና ይቀጥላልም ተብሏል፡፡
መንግሥት የግል ሚዲያው ላይ ዘመቻ የጀመረው በህትመት ዋጋ መጨመር በቋፍ ላይ ያለውን ፕሬስ በማፈንና የነፃነት በሮችን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ጭምር ነው፡፡
መንግሥት የ2007ቱን ምርጫ እንደ ምንም ብሎ ለመሻገር ባለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ጋዜጠኞችን በክስ በማዋከብ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሥት ለህገወጥ የሽበባ ተግባሩ- ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት ሲሞክር እየተስተዋለ ነው፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ በዘዴ ህግ አጣጣስን ያውቁበት ስለነበር በሚወ ስዷ ቸው እርም ጃዎ ች እና በሚያቀርቧቸው ምክንያቶቹ በመጠኑም ቢሆን የሚደናገሩ ወገኖች አይጠፉም ነበር፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ የወጣው ኃይል ግን አካሄዱ ያልተጠና የውር-ድንብር በመሆኑ ስህተቱን ለመሸፈን ተቸግሯል፡፡ ግመል ሰርቆ ተደብቆ ሆኖበታል፡፡
መንግሥት ህገ-መንግስቱ በመጣስ፣ ዓለም አቀፍ ህግ ባለማክበር፣ የሞራል ልዕልናውን ከማጣቱ ባሻገር፣ ከአንድ መንግስት ፍፁም የማይጠበቅ ተግባር እየፈፀመም ይገኛል፡፡
በተለይም እየተጠናቀቀ በሚገኘው ዓመት ያከናወነው የጥፋት ዘመቻ የዓለም መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሦስት ጋዜጠኞችን (ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ እና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ) እና የዞን 9 ጦማሪያንን በሽብርተኛነት ከመወንጀል አልፎ በተለያዩ የፖለቲካ የክርክር መድረኮች እርቃኑን የሚያስቀሩትን ትንታግ ፖለቲከኞች ወደ እስር ቤት ርውሯል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ የሀሰት ጥናትን እና ዘጋቢ ፊልምን በሽፋንነት በመጠቀም ፕሬሱን የመጠራረግ ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዚህ ዓይን ያወጣ ዘመቻ በነፃው ፕሬስ ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞች ከመድረኩ እንዲገለሉ ደርጓል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሙያው ውስጥ የነበሩና ሌሎች ብዙ ይሰራሉ ተብለው የሚጠበቁ ወጣት ጋዜጠኞች የስደትን መንገድ እንዲከተሉ ተዳርገዋል፡፡ ለስደት ከተዳረጉት ጋዜጠኞች በርካቶቹ የፖለቲካ ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቁና አስቸጋሪውን የመንግስት ሽበባ ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የነበሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶችም ከሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ባሻገር ለውጭ የሚዲያ ተቋማት የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ሲሆኑ፣ ከነዚህ መካከል ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
አሁን የቀሩት ጥቂት አልሞት ባይ ተጋዳይ ጋዜጠኞችም አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የዚህች ሀገር ጋዜጠኝነትም ወደ ቁልቁለት እንዲወርድ ተፈርዶበታል፡፡ ከእንግዲህ በዚህች አገር ጋዜጠኝነት የተከበረ ሙያ ሳይሆን፣ በሽብርተኝነት የሚያስፈርጅ ሰዎችን ለከባድ እንግልት እና ስቃይ የሚዳርግ ሙያ እንዲሆን በመንግሥት ተፈርዶበታል፡፡
መንግሥት፣ በጣር ላይ ያለውን ነፃ ፕሬስ ቁልቁል ለመግፋት ቆርጧል፡፡ በህገ- መንግስቱ የደነገገውን አንቀፅ 29 እንኳን ሰርዞታል ወደሚባልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ መንግሥት በጉልበቱ እንጂ በሃሳብ የበላይነቱ መቀጠል ተስኖታል፡፡ መንግሥት ቀደም ሲል ዜጠኛና አክቲቭስት እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው እና ሌሎችንም ማሰሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ዓይን ያወጣ ፕረሱን የማፈን እርምጃውን የጀመረው ግን የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ሶስቱን ጋዜጠኞችን በግፍ በማሰር ቢሆንም፣ የሽብርተኝነት ድግሱን የጠነሰሰው እና በዋነኝነት ኢላማው አድርጎት የነበረው ግን አዲስ በተመሠረተው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ላይ ነበር፡፡
ኢጋመ በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር የተመሠረተው በአንድ መሠረታዊ እና አንገብጋቢ ምክንያት እንዲሁም በሁለት ወቅታዊ ምክንያቶች ነበር፡፡ ይህ መሠረታዊ ምክንያት የሀገሪቱ ጋዜጠኞች መብት አለመከበር፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ አለመረጋገጥ እና ስመጥር የሀገሪቱ ጋዜጠኞች በሀሰት የሽብር ውንጀላ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በጥቅሉ ማኅበሩ ያለፉት 23 ዓመታት የጋዜጠኞች ብሶት የወለደው ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ለማኅበሩ መመስረት ወቅታዊ ምክንያቱ ደግሞ በጥቅምት ወር 2006 መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም እዚህ አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ የሀገሪቱን ነፃ ጋዜጠኞችን በአብዛኛው ያገለለ እና የሀገሪቱን አሳሳቢ የፕረስ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ በተፈጠረ ቁጭት እንዲሁም በተመሳሳይ ወቅት በጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ላይ በተከሰተ ዘግናኝ የመኪና አደጋ ጋር የተያያዘ ስለ ነበር በሀገሪቱ ህገ-ወጥ የጋዜጠኞች እስር እና የመብት ጥሰት ሲብከነከኑ የነበሩ ጋዜጠኞች ተሰባስበው ማኅበሩን ለመመስረት ጥረት አድርገዋል፡፡
ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ ግን በመንግሥት እና ፕሬሱን እንመራዋለን በሚሉ ጥቅመኛ “ጋዜጠኞች” ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም ማኅበሩና ዞን ዘጠኝ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ጋር ተመጋግበው ሊሰሩ ይችላሉ የሚለው ከልክ ያለፈ ስጋት ክፉኛ አስበርግጓቸው ነበር፡፡ በወቅቱም የመንግስት የደህንነት ኃይሎች የዞን 9 አባላት ላይ ከማኅበሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲናገሩ ማስፈራሪያና ወከባ ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ማኅበሩ ሌሎች የጋዜጠኛ ማኅበራትን በሩቁ ሲሸሹ የነበሩ በርካታ የነፃው ፕሬስ አባላትን መማረኩና ከጎኑ ማሰለፍ መቻሉ እንዲሁም በወቅቱ የታየው ጠንካራ የትብብር መንፈስ መንግስትን እንቅልፍ አሳጥቶት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከጅምሩ ማኅበሩ ይበልጥ እንዲፈራ ያደረገው በጋዜጠኞች የተቋቋመ ከመሆኑ በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀባይነት ማግኘቱና አብረው ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢምባሲዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እምነትና ተቀባይነት ያገኘ የሙያ ማኅበር በመሆኑ ነው፡፡
የሀገሪቱን ፕሬስ በማፈን የሚታወቁ ጥቅመኛ “ጋዜጠኞች” በማኅበሩ ላይ መንጫጫት የጀመሩት ወዲያው የማኅበሩ መመስረት በተበሰረበት ማግስት ነበር፡፡ ምክንያቱም በጋዜጠኛው ሥም የሚሰበስቡትን ገንዘብ ስለሚያስቀርባቸው እና ለጋዜጠኞች ጥቅም በእውነት አለመቋቋማቸውን ስለሚያሳብቅባቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ መንግስት የሀሰት ማኅበራቱን በሽፋንነት በመጠቀም ሙሉ ትኩረቱን በአዲስ መንፈስና በተደራጀ መልክ በመጣው ማኅበር ላይ በማሳረፍ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ መንግስት በማኅበሩ የምስረታ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሶስት “የጋዜጠኛ” ማኅበራት አመራሮችን በመጠቀም በቴሌቭዥን ውንጀላ እና ማስፈራሪያ ተጀምሮ ነበር፡፡ ውንጀላና ማስፈራሪያውም የአዲሱን ማኅበር አመራር አባላት በሽብርተኝነት እና በሀገር ከሀዲነት በመፈረጅ ጋዜጠኞች ወደ ማኅበሩን እንዳይቀላቀሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ቀጥሎም ለማኅበሩ መመስረት የበኩሉን ሚና ሲጫወት በነበረው የማኅበሩን ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ላይ ውንጀላ እና ወከባ ወደ መፈፀም ገብቷል፡፡ እዚህ ላይ ፕሬዝዳንቱን በተመለከተ የሚያትት ትልቅ ጥራዝ የሀሰት ሠነድ በማዘጋጀት የአንድ ማኅበር ፕሬዝዳንት በነበሩት ግለሰብ አማካኝነት የተካሄደው የስም ማጥፋትና የማስፈራራት ዘመቻ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የማኅበሩ የህዝብ ግንኙነት በነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ ላይ ይካሄድ የነበረው ወከባ በተለይ የማኅበሩን ምስረታ በተመለከተ ከማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን ለቪኦኤ እና ለሌሎችም የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ የደህንነት ኃይሎች ክትትል ሥር መውደቁን ለጓደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹ ሲናገር ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በማኅበሩ ውስጥ የተሰጠውን ኃላፊነት ለተወሰነ ጊዜ በአግባቡ እንዳይወጣ ተደርጓል፡፡
በዚህ መልኩ በማኅበሩ አመራሮች ላይ የተጀመረው ውንጀላ እና ወከባ እየተጠናከረ መጥቶ መጋቢት 24 በታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ “ገፅ 3” እና አይጋ ፎረም ላይ የማኅበሩን አመራሮች ስም አንድ ባንድ በመዘርዘር ሁከት ለመፈፀም በመዘጋጀት፣ አመፅ በመቀስቀስ፣ ለሽብር ተልዕኮ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመደራጀት፣ መጭውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማወክ በመዘጋጀት ወዘተ በሚል በአሸባሪነት ሊፈርጅ ችሏል፡፡ ይህም በትክክል መንግስት የማኅበሩን አመራሮቹን በሽብርተኝነት ወደ እስር ቤቶቹ ለመወርወር የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ስለመድረሱ በግልፅ አመላካች ነበር፡፡
ከመጋቢት 24ቱ የአዲስ ዘመን ውንጀላ በኋላ የነበሩት ጊዚያት ለማኅበሩ አመራሮች ፈታኝ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይም ቁልፍ ሚና በነበራቸው ላይ የደህንነት ኃይሎችን በመላክ የማስፈራራት እና ማዋከብ ስራ በስፋት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከአካልና የስልክ ማስፈራሪያዎች እንዲሁም ገደብ የለሽ ከሚመስለው ክትትል ባሻገር በተለያዩ መንገዶች ሲካሄዱ የነበሩ ውንጀላዎች የእስር ድግሱ እየተደገሰ ስለመሆኑ በግልፅ የሚያሳይ ነበር፡፡ ይህን ታኮ “የቀለም አብዮት ሰለባዎች” በሚል በኢቲቪ የተላፈው ዘጋቢ ፊልም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ በመንግስት አፈቀላጤ ሚዲያዎች ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ በማኅበሩና በፕሬሱ ላይ የተቀነባበረ አፈና እንደሚካሄድ አመላካች ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማኅበሩ አመራር አባላት ማኅበሩን በሁለት እግሩ ለማቆም እውቅና ወደ ሚሰጠው የመንግስት አካል በመሄድ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም፣ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ማኅበሩ ወደ ህጋዊ መስመር እንዳይገባ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፤ ጥቃቅን ጉዳዩችን ከህግ ውጭ በቅድመ ሁኔታነት በማቅረብ እውቅና የሚገኝበትን እድል እንዲዘጋና የአመራር አባላቱ በሽብርተኝነት ተወንጅለው እንዲታሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተያይዘውት ነበር፡፡
ምንም እንኳን መንግስት ማኅበሩን ጠልፎ ለመጣል ተግቶ ቢሰራም፣ የማኅበሩ አመራር አባላት ግን ቁርጠኛና አይበገሬ ነበሩ፡፡ እንደውም ከእውቅና ጥያቄው ጎን ለጎን የዓለም ፕሬስ ቀንን ለማክበር መጠነ ሰፊ ስራዎችን መስራት ጀምረው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ መሐል ሦስት እውቅ ጋዜጠኞች እና የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ከያሉበት ተለቃቅመው ታሰሩ፡፡ ይህን እስር ተከትሎ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ሚዲያዎች ፖሊስ በኢጋመ አመራር አባላት ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደነበር እና እስሩም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ውሎ ሳያድር በተመሳሳይ መልኩ አፍሪካ ሕብረት ለጠራው ስብሰባ በውጭ አገር ይገኝ የነበረውን የጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ላይ የቤት ብርበራ በመፈፀምና ሌሎች የማኅበሩ አመራር አባላትን በተለይም በዚያው ሰሞን ሙያዊ ስልጠና ለመውሰድ ወደ ናይሮቢ አምርቶ በነበረው የማኅበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ ላይ ይደርስ የነበረው ወከባ እና ማስፈራራት መንግስት ማኅበሩን በእንጭጩ ለመቅጨት የነበረውን ከፍተኛ ፍላጎት በግልፅ ያሳየ ነበር፡፡ ዛሬ ሁለቱ ከፍተኛ የአመራር አባላት በተቀነባበረ የማዋከብ ዘመቻ ከሀገር እንዲሰደዱ ተደርጓል፡፡ ይህም መንግስት የማኅበሩን አመራሮች ከተቻለ በማሰደድ፣ ካልሆነም በተለመደው በሽብርተኝነት ወንጀል በማሰር ማኅበሩን ለማፍረስ የነበረውን እቅድ በከፊል የተሳካ አድርጎታል፡፡
ሁለቱ የማኅበሩ የአመራር አባላት በዚህ ሁኔታ ሀገር ጥለው ከተሰደዱ በኋላ የተቀሩት የማኅበሩ አመራሮች ችግሮችን ተጋፍጠው ማኅበሩ የቆመለትን ዓላማ ከዳር ላማድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የእውቅና ሂደቱ በተለያየ ምክንያት እየተስተጓጎለ በነበረበትም ሁኔታ የሀገሪቱን አስከፊ የፕረስ ሁኔታ በተመለከተ በአፕቪው ሆቴል የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ በዚህ የፓናል ውይይት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኮሙኒኬሽን የትምህርት ክፍል ኃላፊ ጥሩ የሚባል ጽሑፍ ያቀረቡበት፣ እንዲሁም ከፀረ ሽብር ህጉ አንፃር ታዋቂው የህግ ባለሙያ ተማም አባቡልጉ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡበት ፓናል እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ፓናል ግን በፖሊስ ከበባና ወከባ የተካሄደ ከመሆኑ በላይ በሶስተኛው ቀን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ሬድዩ ማኅበሩ ህገ-ወጥ ነው ተብሏል፡፡
ሆኖ ይህ ማኅበር የቆመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተቀሩት አባላቱ ተስፋ ባለመቁረጥ ከእውቅና ሰጭ አካል ጋር በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ መታገላቸውን አሁንም ቢሆን አላቆሙም፡፡ ነገር ግን ተቋሙ አንዴ ስም ቀይሩ ሲል፣ ሲቀየር፣ ሌላ ጊዜ ሌላ ሲል ከርሞ መጨረሻ ላይ ዓላማችሁን ቀይሩ በማለት ማኅበሩን አልቀበልም ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተቀሩት አራት የማኅበሩ አመራር አባላትም ቢሆኑ በእስር ወጥመድ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ከማኅበሩ ሰባት አመራር አባልት መካከል ፕሬዝዳንቱ ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ እንዲሁም ሰሞኑን በመንግስት ክስ እና ጫና ሀገር ጥለው ከተሰደዱት የአዲስ ጉዳይ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውና በማኅበሩ ምክንያት ከባድ ማስፈራሪያ ይደረስበት የነበረው ጋዜጠኛ ብታሙ ስዩም ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ለሀብታሙ መሰደድ እንደ አንድ ዋና ምክንያት የተጠቀሰው ይሄው ከማኅበሩ ጋር በተያያዘ የደረሰበት ከባድ ማሳፈራሪያ ነበር፡፡ እነዚህ ሶስቱ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ውስጥ ተስፋ የሚጣልባቸውና በሙያቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡
ለስደት የተዳረጉት እነዚህ የማኅበሩ አመራር የሆኑ ጋዜጠኞች ከሚደርስባቸው ጫና ባሻገር ለሌሎች ጋዜጠኞች መብት መከበር ያደረጉት ጥረት በሽብርተኝነት እንዲወነጀሉ አድርጓቸዋል፡፡ የተነሱለት በጎ ዓላማ በክፋት ተመንዝሮ ወደ ዳር እንዲገፉ ተደርገዋል፡፡ ለዓመታት በተስፋ ሲጠብቁት የነበረው የጋዜጠኝነት ሙያ እድገትና የባለሙያው መብት መከበር እውን እንዲሆን የጀመሩት ጥረት በስደት እንዲቋጩት ተገደዋል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ዉስጥ ሁሉን አቀፍ አደረጃጀትን መሰረት በማድረግ በሁሉም ጋዜጠኞች እምነት የሚጣልበት ፣ ለሙያዉ እና ሙያዉን በሀላፊነት መንፈስ ለሚተገብሩ ጋዜጠኞች ሁሉ ጥላ ከለላ ለመሆን የነበረዉ አላማ ዛሬ በእንዲህ አይነት መልኩ ከባድ ፈተና ላይ ወድቆ ይገኛል፡፡ ከመንግስት እየደረሰበት ያለዉ መጠነ ሰፊ ጥቃት ማህበሩን አጣብቂኝ ዉስጥ የከተተዉ ሲሆን ፣ ቁልፍ የሆኑት አመራሮቹ በፍርሀትና ተስፋ መቁረጥ መሰደድም የማህበሩን ፈተና ከምን ጊዜዉም በላይ አክብዶት ይገኛል፡፡ ይህም ለእብሪተኛዉ ገዥ ሐይል ትልቅ ስኬት ሲሆን ፣ ለኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች እና ለነፃዉ ፕሬስ ግን ከባድ ዉድቀት ነዉ፡፡

No comments: