Thursday, August 28, 2014

በድርጅቶች ውህደትና ቅንጅት አገርን ማዳን!!!

August28/2014
ኢትዮጵያዊያንን በዘር እና በሀይማኖት ለያይቶን እርስ በርስ እያጋጨን በመግዛት ላይ ያለውን ወያኔን ለማሸነፍ እና ከምትኩም ከራሷ ጋር የታረቀች፤ ፍትህ የሰፈነባት፤ እኩልነት የተረጋገጠባት እና በኃያላን አገሮች እርጥባን ሳይሆን በራሷ አቅም የምትተማመን ጠንካራ ሀገር እንድትኖረን የነፃነትና የዲሞክራሲ ኃይሎት መተባበር እንዳለባቸው ሲነገርና ሲወተወት ቆይቷል። ይሁን እንጂ በህወሓት የከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ እና በፓለቲካ ባህላችን ኋላቀርነት ምክንያት እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ቀድሞ የተደረጉት ጥረቶች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘት ተስፋ ሳያቆርጠን ከእያንዳንዱ ጥረት ልምድ እየወሰደን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ አዳዲስ የትብብር ጥረቶችን ማድረግ ያለብን መሆኑ ያምናል። በዚህም መሠረት የትብብር መርህ ነድፎ ትግል ውስጥ ካሉ ሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሲነጋገር እና ሲደራደር ቆይቷል። እንደሚታወቀው የንቅናቄዓችን አበይት የትብብር መርሆች ሁለት ናቸው። መርህ አንድ፣ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገለው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ መሆኑ ማመን ነው። መርህ ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚገባው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ መሆኑን መቀበል ናቸው።
በምድር ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ኃይሎች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ሁለቱንም መርሆዎች የሚያሟሉ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ከንቅናቄዓችን የተለየ አቋም የላቸውም። በአለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ ተቀራርበው እንዲሠሩ በመደረጉ ከአመራር አልፎ አባላት መካከል መልካም ወዳጅነት መመሥረት ተችሏል። የነፃነት ትግላችን የደረሰበት ደረጃ እና የድርጅቶቹም ቅርርብ በመገምገም ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ መዋሃዳቸው ትግሉን ያራምዳል ተብሎ ታምኖበታል። በዚህም መሠረት ሶስቱ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማምተን ስምምነታቸንን ይፋ አድርገናል። ድርጅቶቹን የማዋሃድ ዝርዝር ሥራም ተጀምሯል።
ከስትራቴጄ አንፃር የትብብር ጥረታችን በዚህ አያበቃም። በዓላማ የምንቀራረብ ሆኖ የአደረጃጀት ልዩነት ያለን የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር በጥምረት እየሠራን ድርጅቶቻችን ይበልጥ ለማቀራረብ ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ነው። ንቅናቄዓችን ከትህዴን ጋር ከፍተኛ በሆነ መቀራረብና መተማመን ይሠራል። ይህ መቀራረብና መተማመን ጎልብቶ አንድ የጋራ አመራር የሚፈጥርበት ጊዜ እንዲቀርብ ጥረት እናደርጋለን። ምድር ላይ ከሚገኙ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋርም በመደጋገፍ እንሠራለን። በመጨረሻም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ካሉ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ለመወያየት ዝግጁዎች መሆናችንን ደግመን እናረጋግጣለን። ልዩነቶቻችን ማጥበብ እንኳን ባንችል የምንተባበርባቸው መንገዶች ይኖራሉ ብለን እናምናለን።
የጦር ኃይሉንና የስለላ መዋቅሩን ዘረኛ በሆነ መንገድ የገባውንና የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ የደረጀው ህወሓትን ለማሸነፍ ትብብር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ከወያኔ አገዛዝ ውድቀት በኋላ ወደ ተረጋጋ ሰላምና ልማት ፊታችንን የምናዞር መሆናችን ዋስትና የሚሰጠን በአንድ እዝ የሚመራ የአገር አድን ሠራዊት ማደራጀት ስንችል ነው። የአሁኑ ውህደት የዚህ አገር አገር አድን ሠራዊት ጥንስስ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ በኋላ የሚመጣው ምን እንደሆነ ባለማወቅ ሥጋት ውስጥ ሊገባ አይገባም። በዋና ዋና የአገሪቱ የፓለቲካ ድርጅቶች ውህደት እና ቅንጅት የተዋቀረ በአንድ ማዕከላዊ አመራር ሥር የሆነ አገር አድን ሠራዊት በተቻለ ፍጥነት ሊገነባ ይገባል።
ሶስቱ ድርጅቶች ለማድረግ በወሰነው ውህደት የዚህ የአገር አድን ሠራዊት ምሥረታን ጀምረናል። ስለኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ደህንነት ያገባናል የምትሉ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ አገር አድን ሠራዊት ምሥረታ ላይ እንድንነጋገር አበክረን እንጠይቃለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የትብብሩ መንፈስ አገርን የማዳን ግብ ያለመ መሆኑን በመገንዘብ ከተባበረው ድርጅት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳይ የሚያገባው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲቀላቀለንና እንዲያግዘን ጥሪዓችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments: