Saturday, August 23, 2014

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

August23/2014
 የሸክ ኑሩ ግድያ ሴራ ነው
• ኢህአዴግ በሉዓላዊነት ላይ ያለውን ፖሊሲ ተቃውመዋል
• ‹‹አማኞችን በአሸባሪነት መክሰስ ትውልዱን ለመግደል የተደረገ የኢህአዴግ ሴራ ነው፡፡››
• ህወሓት ከስሯል
• የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ
• አዲሲቷ ኢትዮጵያ የትኛዋ ናት?

ነገረ ኢትዮጵያ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስ፣ ደሴ፣ ወልደያ፣ ደብረታቦርና ሌሎችም የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ባገኘችው መረጃ መሰረት የተነሱትን ዋና ዋና ተቃውሞወች እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡

አርሶ አደሩ አሁንም ድረስ ኢህአዴግ እየተደረገ ያለው የመሬት ድልደላ የፓርቲው አባል አይደሉም የሚባሉት አርሶ አደሮችን መሬት አልባ በማድረግ ለደጋፊዎቹ እየሰጠ መሆኑን በውይይቱ ወቅት ተገልጾአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅንጅትን መርጣችኋል እየተባሉ አሁንም ድረስ ጫና እየደረሰባቸው እንደሚገኝና፣ ይህም ለምርጫው ዝግጅት እንዳይሆን ተማሪዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የእምነት ነጻነት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለሶስት አመታት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጻቸው እንዲሰማ ቢጥሩም መንግስት እየወሰደው ያለው አፈና አግባብ አለመሆኑን፣ በተለይም በርካታ ቁጥር ያለውን ሙስሊሙን ማህበረሰብ በጅምላ አሸባሪ ብሎ መፈረጅ ስህተት መሆኑን በተማሪዎቹ ተነስቷል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹ኢህአዴግ ማህበረ ቅዱሳንን አሸባሪ የሚልበት ምክንያት ምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ የተነሳ ሲሆን የግቢ ጉባዔ የማህበረ ቅዱሳን አንድ ክንፍ ነው ተብሎ በመፈረጁ አዲስ ህግ ወጥቶ ዩኒቨርሰቲ ውስጥ በጾም ወቅት ይሰጠን የነበረው አገልግሎትን ጨምሮ እምነታችን እንዳንተገብር መከልከላችን ለጣልቃ ገብነቱ ማሳያ ምክንያት ነው›› ብለዋል፡፡

ይህም መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በእምነት ላይ ጣልቃ እየገባ መሆኑን በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ እንደ ምሳሌም በ1989ና 1994 ዓ.ም የኃይማኖት አባቶች በተለይም ቄሶች የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል ተብለው ድብደባ እንደደረሰባቸው በመግለጽ የጣልቃገብነቱን አስከፊነት ገልጸዋል፡፡ ሉዓላዊነት ሉዓላዊነትን በተመለከተ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ የተነሳ ሲሆን በተለይም በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ወልደያ፣ ደሴና ደብረማርቆስ ዪኒቨርሲቲዎች ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡ ተማሪዎቹ ‹‹መሬቱን ቆርሶ የሰጠው ኢህአዴግ ነው፣ በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ አገራችን ከነበራት ክብር እያሳነሰው ነው፣ ኢትዮጵያ አንድነትን ለመጠበቅ የጣረውን ምኒልክን እየወቀሰ ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት መሬት ቆርሶ መስጠቱ አላማውን በግልጽ የሚያሳይ ነው›› በማለት በሉዓላዊነት ላይ የተሳሳተ ፖሊሲ እንዳለው ተከራክረዋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹ኤርትራ ተገንጥላለች፣ አሰብን አጥነተናል፣ ባድመ ላይ ወጣቱ አልቆ መሬቱን አሳልፎ ሰጥቷል፣ አሁን ደግሞ የመተማን መሬት አሳልፎ ለመስጠት በድብቅ መፈራረሙ በሉዓላዊነታችን ላይ ያለውን አሉታዊ አቋም የሚያሳይ ነው፡፡›› በሚል በሉዓላዊነት ላይ ያለውን የተሳሳተ ፖሊሲ ተቃውመዋል፡፡ በተመሳሳይ ተማሪዎቹ አያሌው ጎበዜ የፕሬዝዳንትነት ስልጣኑን ሳይጨርስ የወረደው መሬቱን ፈርሜ አልሰጥም ስላለ ነው፡፡›› ያሉት ተማሪዎቹ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ የሸህ ኑሩ ግድያ ደሴ ላይ የተማሪው ትልቅ መወያያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የሸህ ኑሩ ግድያ በቀዳሚነት እንደሚገኝ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

slide-15ከተወያዮቹ መካከል ‹‹የሸክ ኑሩ ገዳይ የኢህአዴግ ደህንነቶች ናቸው፡፡ ይህም የተደረገው ኢህአዴግ በሙስሊሙ መካከል ልዩነት ለመፍጠርና እርምጃም ለመውሰድ እንዲመቸው የወሰደው ነው፡፡›› ማለታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ ደብረማርቆስ በሚገኙ ተወያዮች አጀንዳ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ተማሪዎቹ ‹‹የመን አንዳርጋቸውን አሳልፋ መስጠቷ ትክክል አይደለም፣ የአንዳርጋቸው ጉዳይ ሽብርን መዋጋት ነው ወይንስ የፖለቲካ ባላንጣነት? የእንግሊዝ ዜጋ የሆነውንና እንግሊዝ በአሸባሪነት ያልፈረጀችውን ሰው አሸባሪ ማለቱ ጸረ ሽብር ህጉ ከእንግሊዝ ተመሳሳይ ህግ ጋር በምን ቢለያይ ነው? በጸረ ሽብር ኢህአዴግ ከእንግሊዝ በልጦ ነው ወይ? አሁን ያለበት ሁኔታም ለህዝብ ይፋ ሊሆን ይገባል የመሳሰሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ማፈናቀል የከተማ ነዋሪዎችን ማፈናቀል በባህርዳር፣ ጎንደርና ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ የሚገኙት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተነስቷል፡፡

ተማሪዎቹ ‹‹በተለያዩ ከተሞች ድሃዎችን በማፈናቀልና ቤታቸውን በማፍረስ ለሀብታም እየተሰጠ ነው፡፡ ይህ የጭቆና የመጨረሻው ደረጃ ነው፡፡›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹የመሬት መቀራመት መሬት በቀብሬ ላይ ይቀየራል ከሚለው የኢህአዴግ ፖሊሲ የመነጨ ነው፡፡ የመሬት ክፍፍሉ አርሶ አደሩን ያገለለና ለስርዓቱ መጠቀሚያ የሆነ ነው፡፡ የሊዝ ህጉ መሰረዝ ይገባዋል፣ አርሶ አደሩ ከመሬት እየተነቀለ ነው፣ 1ለ5 አርሶ አደሩን ለማፈን የተደረገ ነው፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ህዝብ እንጅ የመንግስትና የፓርቲ መሆን የለበትም›› የሚሉ ተቃውሞዎች ተነስተዋል፡፡ የባህር ዳሩ ግጭት የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ የተፈጠረው ግጭትን በተመለከተ ደሴ፣ ደብረታቦር፣ ባህርዳርና ጎንደር ላይ መወያያ ሆኖ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባህርዳር ላይ በተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ የተፈጠረው ግጭት ብአዴን በበላይነት የመራው ሴራ መሆኑን፣ ይህም አማርኛ ተናጋሪውን እንደማይወክል፣ የብአዴን ፖለቲከኞች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ በአደባባይ ሲሳደቡ መስተዋላቸው የሚያሳየው ለህዝብ ያልቆሙ እንደሆነ ተማሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ርዕዮት-ዓለም በተለይ ባህረዳር ውስጥ ድባንቄ የተባለ ቦታ ላይ የሚገኙት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሰልጣኞች በርዕዮት ዓለም ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹እስከ 1994 ዓ.ም ኢህአዴግ ፖሊሲ አልነበረውም፣ ተቃዋዎችን ፖሊሲ የላቸውም እያለ ለመተቼት ምን ሞራል አለው፣ ሌብራሊዝም ተቃዋሚዎቹ ስለሚከተሉት ብቻ ትክክል እንዳልሆነ እየተነገረን ነው፣ ከቻይና ተገለበጠ የሚባል ርዕዮት ዓለም ለኢትዮጵያ እየጠቀመ አይደለም፣ መነሻውና መድረሻው የማይታወቅ የኢህአዴግ ርዕዮት ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፣ ማህበረቅዱሳንንና ሙስሊሙን ማህበረሰብ አሸባሪ ማለት እምነት አልባ ትውልድ ለመፍጠር የተደረገ ሴራ ነው፣ ይህ ትውልዱን ለመግደል የተደረገ የኢህአዴግ ሴራ ነው፡፡

ትምህርት ‹‹ትምህርትን በኢህአዴግ ዘመን ወድቋል፡፡ ትምህርቱ ጥራት ቢኖረው ኖሮ ተመርቆ ስራ አያጣም ነበር፡፡ አሁንም ስራ እንይዛለን የሚል ተስፋ የለንም፡፡ ኢህአዴግ ዘመን ትምህርት ወድቆ ትምህርት ስርዓቱን የጀመሩትን ስርዓቶች የማውገዝ ሞራል አላችሁ ሆይ?›› የሚሉ ተቃውሞዎች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በየ ዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሴቶች በትምህርት ስርዓቱ ውድቀትና በድህነት ምክንያት ገላቸውን እየሸጡ ነው፡፡ ኢህአዴግ በግብረ ሰዶማውያን ላይ ያለው አቋም የተሳሳተ ነው፡፡ ይህም የሚደረገው ትውልዱ ማንነቱን ትቶ ውድቀት ላይ እንዲወድቅ ለማድረግ ነው፡፡ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሌብራሊዝምን እያንቋሸሸ የወሲብ ሌብራሊዝምን ግፍ ከሚገባው በላይ ለቆታል፡፡ ይህ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለማቆየት የሚያደርገው ስልት ነው፡፡ ይህ በተሳሳተ የኢኮኖሚ ምክንያት በመጣው ድህነት የተነሳ ነው፡፡ በትምህርት ውድቀትና በድህነቱ ምክንያት ተማሪዎች ድንጋይ መቀጥቀጥ አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ ሴቶች የወሲብ ንግድን እንዲቀላቀሉ እንዲሁም ወንዶች የጎዳና ተዳዳሪ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ የሚሉ ተቃውሞዎችን ማቅረባቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡›› የሚሉ ተቃውሞዎች ተነስተዋል፡፡

ኢዲሲቷ ኢትዮጵያ የትኛዋ ናት? ለስልጠና በቀረቡት ሰነዶች አብዛኛዎቹ ክፍሎች ውስጥ ‹‹አዲሲቷ ኢትዮጵያ›› የሚል ቃል የተደጋገመ ሲሆን ተማሪዎቹም ‹‹ኢዲሲቷ ኢትዮጵያ የትኛዋ ናት? ኤርትራ የተገነጠለችባት፣ በቋንቋ የተከፋፈልንባት፣ ወደብ አልባ የሆንንባት፣ የኢትዮጵያ ገናናነት የወረደባት ኢትዮጵያ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ልትባል ትችላለች? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ብሄር ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚለው ወልደያ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስ በሚገኙ ሰልጣኞች ሰፊ ክርክር አስነስቷል፡፡ ፋብሪካዎች ደብረማርቆስ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‹‹ደብረ ማርቆስ ውስጥ ሊገነባ የነበረ የመኪና መገጣጠሚያ እንደገና እንዲቀር ተደርጓል፣ በክልሉ የቢራ እንጅ ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ አይደረግም›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹በስፋት ደን ይመነጠራል፡፡ ደን እየተመነጠረ እንዴት አረንጓዴ ልማት አለ ይባላል?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ተጠይቀዋል፡፡

ህወሓት ከስሯል

በመቀሌ ዪኒቨርሲቲ የሚገኙ ሰልጣኝ ተማሪዎች በተለይም በህወሓት ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አሰልጣኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ‹‹የትግራይ ህዝብ በህወሓት አምኖና ከሌላው ህዝብ ተለይቶ እንዲኖር ህወሓት ብዙ ስራ ሰርቶ ነበር፡፡ ከክፍፍሉ በኋላ ግን ህወሓት ከስሯል፡፡ የትግራይ ህዝብን ጥያቄ ያልተመለሰ ለመሆኑ የአረና መፈጠር አንድ ማሳያ ነው፡፡›› ማለታቸውን አሰልጣኙ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አብርሃ ደስታ ላይ የተወሰደው እርምጃም መነጋገሪያ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል፡፡ ተማሪዎቹ አብርሃ ደስታ መፈታት እንዳበት መጠየቃቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄውን ያነሱት ተማሪዎች በቡድን ውይይት ወቅት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነም ተገልጾአል፡፡ በጅማ፣ አዳ፣ ሀዋሳና ሌሎች ከተሞች የሚሰለጥኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያሰሙትን ተቃውሞና መከራከሪያዎች በቀጣይነት ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)

No comments: