Saturday, August 2, 2014

ስለ ዳተኛ ምሁራንቸል አንበል

August2/2014
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
ምሁር የሚለው ስያሜ እውቀት የተካነ ጥበብን አፍላቂ የዐለምን ምስጢር መርማሪ፣ እውነት መስካሪና አስተማሪ ለሆኑ የሚሰጥ መጠርያ ነው ወይንስ በአንዱ ወይም በሌላው ተቋም ውስጥ ያለፉና ያንን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት (ከአርከበ ሱቅ ከሚገዛው በቀር) ለተቀበሉ ሁሉ የሚሰጥ ነው? የሚል ጥያቄ በየወቅቱ ይነሳል። ብዙ ባለምስክር ወረቀቶች ግራና ቀኝ ማየት የማይደፍሩ፣ እውነት የማይመሰክሩ የተሻለ ደሞዝ፣ ዝናና ክብር የሚያማልላቸው ስምና የትምህርት ደረጃቸውን ለመተዳደርያ ብቻ የሚያደርጉ ሆነዋል የሚል ወቀሳም እየበዛ ነው። እንዲያውም ‘መማር እንደዚህ ከሆነ’ የሚሉ የተሳሳተ አቅጣጫ የሚይዙ ሰዎች የመጡበትም አንደኛው ምክንያት ይኸው ነው። ይህ ማለት የተማሩ ሰዎች ሁሉ እንደ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፖለቲከኛ ለምን አልሆኑም ማለት አይደለም። ፖለቲካ ሳይንስ ነው ካልን ሰዎች ባልተካኑበት ቢቀድሱ ከመዕመናን ጆሮ ላይደርሱ ቢደርሱም እንደሳቸው ተደናግረው ሊያደናግሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ነፃነት፣ መብትና ፍትህን መፈለግ የፖለቲካ ጠበብትነትን አይሻም፣ ሰው መሆንን ብቻ እንጂ። በተለያየ ሙያ ከሰለጠኑ ምሁራንም በትንሹ የሚጠበቀው ለመብትና ለነፃነት ቀናዒ እንዲሆኑ ነው።

ለመጻፍ መነሳሳቴን የፈጠረው ዛሬ ያነበብኩት በኢያሱ ለበኑ የተጻፈው Ethiopia: The Tale of Two Minister D’états የሚለው ጽሁፍ ነው። ይህ በእንግሊዝኛ የተጻፈው ጦማር ሁለት የአባትና የልጅ ያህል ልዩነት ያላቸውን ሚኒስትር ደኤታዎችን የሚያነጻጽርና አንደኛው በጣም የተማሩና አዛውንቱ ዶር ተቀዳ አለሙ ከሁሉም አገዛዞች ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሄዱ ለሁሉም አገልጋይ ስለመሆናቸውና ሌላኛው ኤርምያስ (ወያኔ ሲገባ እድሜው ሃያ ያልገባ) ከመንግስት ጋር ሆኜ አገር መግደልና ሕዝብ መበደል ይብቃኝ ብለው አለቃቸውን ስለነበረን ጊዜ አመሰግናለሁ በሚል ደብዳቤ ወደ እውነት ለመጠጋት ምቾትንና ስልጣንን ጥለው ስለሄዱት ግለሰብ የሚመለከተው ነው። ወያኔ ሲገባ የነበረው ሞቅ ሞቅና በደርግ ላይ የነበረው አፍላ ጥላቻ የልጅነት መልቀቂያ ፈተና ተቀብሎ ወደ ጉርምስና የሚሸጋገር እንደ ኤርምያስ ላለ ወጣት የሚመርጠውን መንገድ መሞገት አሰቸጋሪ ነው። ወደ ጉልምስና ሲሻገር ግን እውነት ማየት ከተሳነው ችግር እንዳለ ያመለክታልና ኤርምያስም እውነትን አሻግሬ ተመለከትኩ ያለሁበትንም ጠላሁ ብለው የራሣቸውን እድል በራሳቸው ወሰኑ። ዶክተሩ ደግሞ ወደ አዲስ የመንግስት የስልጣን ግምጃ ቤት እየተቀዱና በቀላሉ እየተደባለቁ ስለመኖራቸው የሚያነጻጽረው ጦማር ጊዜያችንን ገላጭና ጥያቄ አጫሪም ነው።

የኢያሱ ለበኑ ጦማር በኦሪየንታሊዝም ጽሁፉና በሌሎችም ስራዎቹ ታዋቂ የሆነው ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሰይድን (1935 – 2003) ሃሳብ የሚጋራ ይመስለኛል። ፕሮፌሰሩ በአንድ ጽሁፉ …

“Nothing in my view is more reprehensible than those habits of mind in the intellectual that induce avoidance, that characteristic turning away from a difficult and principled position which you know to be the right one, but which you decide not to take. You do not want to appear too political; you are afraid of seeming controversial; you need the approval of a boss or an authority figure; you want to keep a reputation for being balanced, objective, moderate; your hope is to be asked back, to consult, to be on a board or prestigious committee, and so to remain within the responsible mainstream; someday you hope to get an honorary degree, a big prize, perhaps even an ambassadorship. For an intellectual these habits of mind are corrupting par excellence. If anything can denature, neutralize, and finally kill a passionate intellectual life it is the internalization of such habits.” (Edward Said, 1994, Representations of the Intellectual, pp.100-101)

ሃሳቡ ወደ አማርኛ ሲመለስ “… እንደ እኔ አመለካከት በመርህ ላይ የተመሰረተ አስቸጋሪ ግን ትክክለኛ አቋም ከመያዝ ሆን ብለው የሚሸሹ ምሁራንን ያህል አሳፋሪ ነገር የለም። ፖለቲከኛ ላለመምሰል ተሟጋችና አስቸጋሪ ላለመባል የአለቃን ወይም የበላይን መልካም ፈቃድ ብቻ በመጠበቅ ሚዛናዊና ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘቡ ናቸው በመባል በትላልቅ ስፍራ ለመጋበዝ አማካሪ ለመሆን የከፍተኛ ኮሚቴዎች አባል ለመሆንና በትላልቅ የቦርድ ስብሰባዎች ለመገኘት፣  ከሃላፊዎች ተርታ ለመቆም እናም አንድ ቀን የክብር ዲግሪ ለማግኘት፣ ትላልቅ ሽልማቶች ለመሸለም ምናልባትም አምባሰደር ለመሆን ይጥራሉ። ይህ አይነቱ ባህርይ ምሁርን ከምንም ነገር በላይ የሚያረክስና እርባናቢስ አድርጎ የሚያከሽፍ ልማድ ነው…”

በርካቶቻችን በዘልማድ ለዚህ አይነት ሰዎች ሞገስና ክብር መስጠታችን ደግሞ እጅጉን ጎድቶናል። ስለ ጨዋነትና ጥሩ ሰውነት መገለጫው ዝምተኛነትና ዳተኛነት ነው። ‘እሳቸው ዝም ነው… አይቶ እንዳላየ ናቸው… ሰው ቀና ብለው አያዩም… ከሁሉም ጋር አብረው ይሄዳሉ…. ምንም ውስጥ የሉበትም.. ኑሮአቸውን ብቻ ነው የሚኖሩት…ወዘተ። በሚሉ አባባሎች ውስጥ መልካም ነገሮች ቢኖሩም አንኳ እነዚሀ የባህርይ መገለጫዎች ለመብትና ነፃነት ተቆርቋሪ የሆኑትን ፍትህ ፈላጊዎች አሳናሽ ናቸው። ስለዚህ የመብት ታጋዮችን ‘ነገረኞች’ “አሳዳሚዎች’ ያስብላል። በነኚህ ‘ነገረኞችና አሳዳሚዎች’ ጥንካሬና ትግል ሳቢያ የሚመጣውን ጥቅም ግን ቀድመው የሚቋደሱት ምንም ውስጥ የሌሉበት ‘ጨዋዎቹ’ ናቸው። ጉዳት ቢኖረው መስቀል ተሸካሚዎቹ ‘ነገረኞቹና’ ‘አሳዳሚዎቹ’ ይሆኑና “ሳይቸግራቸው… አርፈው ቢቀመጡ ኖሮ” ተብለው ይወገዛሉ።

ለዚህም ይሆናል ዛሬ በሀገርቤትም ይሁን በውጪው አለም በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ‘ምሁራን’ በደልንና መብት ረገጣን አይቶ እንዳላየ ሲያልፉ የምንመለከተው። ከዚያ የሚብሰው ደግሞ የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ እንደ ክህሎታቸው የሚሞክሩትን ሁሉ ማብጠልጠል ማዋረድና መመፃደቅን እንደ ትልቅ ነገር በመቁጠር ሲኮፈሱ የምናያቸውም የበዙበት ምክንያትም ይህ ዳተኝነት ምንም ዋጋ ስለማያስከፍልም ነው። ከዚህ አይነት ስነምግባር በመቆጠብ እውቀታቸውን ቢፈትሹና የሚተርፋቸውን ቢያካፍሉ ከሌሎች ጋርም ቢመክሩ በስሜትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በእውቀት፣ በአመክንዮና በብልህነት ወደፊት እንድንገሰግስ እገዛቸውን ቢለግሱ የተሻለ ይሆናል። መድረክ ላይ ወጥቶ መናገር ወይም ጽሁፍ መጻፍ ብቻ ሳይሆን ተቋማትን ማጠናከር፣ አዳዲስና ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን መፍጠር፣ የተራራቀው እንዲቀራረብ የከረረው እንዲረግብ ማድረግ፣ የእውቀት ፍላጎትን በማሳደግ የመረጃ ተፋሰስን በማስፋት ምሁራዊ አስተዋጽኦ የሚደረግባቸውን መንገዶች መፈለግና ሃሳብ ማቅረብ ድርሻቸው ነው እንዲያውም የዜግነት ግዴታቸው ጭምር ነው። ምሁራን የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን አንደጠላትነት ሲመለከቱ ክርክራቸውን ወደ ተራ ስድብነት ሲቀይሩት ቂመኝነት የዛሬውን አይናቸውን ሲጋርደው ግን የጥፋት ጥፋት ይሆናል። ሃሳቤን በዚሁ የሃርቫርድ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሰይድ ጽሁፍ ላጠቃልለው ፈቀድኩ እንዲህ ይላል…

“And finally a word about the mode of intellectual intervention. The intellectual does not climb a mountain or pulpit and declaim from the heights. Obviously you want to speak your piece where it can be heard best; and also you want it represented in such a way as to influence with an ongoing and actual process, for instance, the cause of peace and justice. Yes, the intellectual’s voice is lonely, but it has resonance only because it associates itself freely with the reality of a movement, the aspirations of a people, and the common pursuit of a shared ideal.”

ወደ አማርኛ ሲመለስ “በመጨረሻም ስለምሁራን አስተዋጽኦ እንዲህ እላለሁ። ምሁር ከተራራው ጫፍ ወጥቶ ወይም ከመድረክ ላይ ቆሞ ድል አድርጌአለሁ አይልም። ይልቁንም ሃሳብህን አድማጮችህን በሚገባ ልትደርስበት በምትችለው መንገድ ተናገር። ንግግርህም እየሆነ ባለ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ይሁን ለምሳሌ ስለ ሰላምና ፍትህ። አዎ የምሁር ድምጽ ብቸኛ ሊሆን ቢችልም እንኳ ስለ ሕዝቡ ፍላጎት ስለ ትግሉ ስለጋራ ግብና የጋራ ስምምነት እስከሆነ ድረስ እንደ ገደልማሚቶ ያስተጋባል።” ይለናል።

ምሁራን እውቀትና ብልህነታቸውን፤ የሕዝባቸውን የነጻነትና የፍትህ ጥማት አገናዝበው ከያሉበት የሚያሰሙት ድምፅ የሚያንኳኩት በር እንደ ገደልማሚቶ እያስተጋባ የሚያስተባብረን ወደ ነጻነትና አንድነት የምናደርገውን ጎዳና የሚያሳምርልን በፍጥነትም የሚያደርሰን ይሆናልና ለዚህ ቢተጉልን በልባችን ውስጥ ሀውልት እንሰራላቸው ዘንድ እውነት ነው። ጠብታ ተጠራቅሞ ጎርፍ ጎርፍም ጎልብቶ ወንዝ እንዲሆን ሁሉ ከያላችሁበት ድምጻችሁ ይሰማ ክፋትን ጠራርጎ የሚወስድ ሕዝባዊ አመጽም ይወለዳል።

ነፃነትና ሰላም ፍትህና ብልጽግና ለኢትዮጵያችን ይሁን
biyadegelgne@hotmail.com

No comments: