Thursday, August 21, 2014

ዳኞች ካድሬ ሲሆኑ እንደማየት የመሰለ የአገር ዉድቀት የለም – ግርማ ካሳ

August21/2014
አገሩን እና ሕዝቡን የሚወድ ። እንደ ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን፣ ኢትዮጵያ ከግፍ አገዛዝ ተላቃ ዜጎች መብታቸዉና ነጻነታቸው ተጠበቆ፣ ተከባብረዉ በስላም የሚኖሩባት አገር እንድትሆን፣ የሚያደርጉትን ትግል የተቀላቀለ ነው። ወጣት ነው። ጉልበትና አቅም አለው። እንደ አንዳንዶች በጥቅም ተታሎ አደርባይነትን መምረጥ ይችል ነበር። ነገር ግን አላደረገዉም። «ሰዉ ያለ ነጻነቱ ምንድን ነው ? » ብሎ ለነጻነቱ ቆመ። የባለ ራእዩ ወጣቶች ማህብርን ከዚያም የአንድነት ፓርቲን ተቀላቀለ። በአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ መዋቅር የቦሌ ወረዳ አመራር አባል ሆኖ ይሰራ ነበር። በሶሻል ሜዲያዉም ብዙ ጊዜ ድምጹን ያሰማል። አይፈራም። ወኔ አለው።
ጥላዬ
በቅርቡ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ እየተደረገ በነበረዉ፣ ዉህዱን ፓርቲ ለመምራት በተደረገው የምርጫ ፉክክር «አዲስ አመራር ያስፈልጋል» በሚል ለአቶ በላይ ፍቃደ ይቀሰቅስ ነበር። ለዉጥ ፈላጊ ነው።
ነሐሴ 4 ቀን 2006 ዓ.ም ፣ ዜጎችን ማሰርና ማሰቃየት የለመደባቸው የአገዛዙ ታጣቂዎች ከየአቅጣጫው ተረባረቡበት። ምክንያቱ ለጊዘው ባልታወቀ ሁኔታ ወደ ወህኒ ወረወሩት። ይህ ወጣት ፣ ብዙዎች የማያወቁት፣ የማደንቀዉን የማከብረው ጥላዬ ታረቀኝ ይባላል።
ፖሊሲ ፍርድ ቤት ይዞት በቀረበ ጊዜ፣ «በሰው ላይ ጉዳት አድርሷል» የሚል ክስ ነበር ያቀረበበት። ፖሊሲ በሰው ላይ ጉዳት አደረሰ የሚል ክስ አቅርቦ ጉዳት ደረሰበትን የተባለው ግለሰብ ግን ለማቅረብ አልቻለም። «ጉዳይ ደረሰበት የተባለውን ሰው ማግኘት አልቻልኩም» ብሎ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጊዜ እንዲሰጠው ጠየቀ። ወጣት ጥላዬ ግን ለፍርድ ቤቱ ፣ «የያዙኝ ደህንነቶች እየመጡ ከእኛ ጋር ለመስራት ፈቃደኛ እስካልሆንክና የምንሰጥህን ተልዕኮ እስካልፈፀምክ እዚህ ትበሰብሳለህ እንጂ አትወጣም» እያሉ እንደሚዝቱበት አስረዳ። ዳኛው ግን መረጃ ባልቀረበበት እና በወጣት ጥላዬ ላይ በፖሊሶች ዛቻና ማስፈራሪያ እየተሰጠ ባለበት ሁኔታ፣ በዋስ እንዲፈታ ሳይፈቅ ቀረ። ለነሐሴ 12 ፖሊሲ መረጃዎቹን አጠናቆ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጠ።
ጉዳት ደረሰ የተባለው ከሁለት ወራት በፊት፣ በሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ነው። በቀጠሮዉ ቀን፣ ፍርድ ቤቱ «ሁለት ወራት ሙሉ የት ነበራችሁ? ለምንስ ጉዳት የደረሰበት ሰው አላቀረባችሁም ? » ሲል ጠየቀ። ፖሊሶች «ጉዳይ የደረሰበትን ሰው ልናገኘው አልቻልንም። የሕክምና ማስረጃ እንድናቀርብ ይፈቀድልን» ብለው ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ወጣት ጥላዬ «የአንድነት ፓርቲ አባል በመሆኔ፣ ባለኝ የፖለቲካ አመለካከት ጫና ለማሳደር የተወጠነ ውጥን» ነው ሲል ከፍርድ ቤቱ ፍትህን ጠየቀ።ፍርድ ቤቱ ግን አሁን ለሰላማዊ ዜጎች ፍትህን ነፈገ። ወጣት ጥላዬ በወህኒ እንዲቆይ ተደርጎ ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ተሰጠ።
አስቡት፣ የሕክምና መረጃ ያለ ባሌበቱ ሆስፒታሎች መስጠት የለባቸውም። (የአገር ደህንነትን የሚነካ ካልሆነ በቀር)። አሁን፣ ፖሊስ እያለ ያለው፣ ታከመ የተባለው ሰው ፍቃድ ሳይጠየቅ፣ የህክማን ማስረጃ ከሃኪም ቤቶች እንደሚያቀርብ ነው። ለነገሩማ የሆስፒታል አስተዳዳሪዎች ዉሸትን ጨማምረው፣ ያለዉን እንደሌለ፣ የሌለዉን እንዳለ አድርገው መረጃ መስጠታቸው አይቀርም። በተለያዩ ጊዜያት በሌሊት የሚገደሉ፣ በረሃብና በጠኔ የሚሞቱ ብዙ ናቸው። በአገር ቤት ችግር እንደሌለ የዉሸት ገጽታ ለማቅረብ የሚፈልገው አገዛዙ፣ ሆስፒታሎች የዉሸት አታብሲ (የሞት ይሕክምና ማረጋገጫ) እንዲጽፉ እንደሚያደርጓቸውም ያው አገር ሁሉ የሚያወቀው ሐቅ ነው።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ሁለት ትላልቅ ነጥቦች አሉ።
1. ብዙዎቻችን በጣም የሚታወቁ ግለሰቦች ሲታሰሩ ነው የአገዛዙ ዜጎችን የማሸበርና የማወክ ተግባር የሚታየን። ነገር ግን በአገራችን እየተደረገ ላለው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ብዙ የማናውቃቸው ወገኖቻችን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው። ከነዚህም አንዱ ወጣት ጥላዬ ታረቀኝ ነው።
2. በኢትዮጵያ አገራችን ባሉ ፍርድ ቤቶች እየታየ ያለው፣ ፍትህን የማስከበር ሥራ ሳይሆን፣ ፍጹም አሳፋሪ፣ ኋላ ቀርና አሳዛኝ የፍርድ መዛባት እንደሆነ ነው። ፖሊስ ዜጎችን እንደፈለገ ሲያስርና ሲያሸብር፣ በፈለገ ጊዜ ተጨማሪ ቀጠሮ ሲጠይቅ፣ ዳኞች ቅንጣት እንኳን የሕግ ባለሞያዎች የስነ-ምግባር ኮድ (ኤቲክስ) ሕሊናቸውን ወቅሷቸው፣ ትክክለኛ ነገር ሲሰሩ እንደማይታዩ ነው። ዳኞች ካድሬ ሲሆኑ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለአገር ዉድቀት የለም።
ገዢዎች ይኸው ስልጣን ከያዙ ጀመሮ እንደገደሉና እንዳሰሩ ናቸው። ሕግን መቀለጃ እያደረጉ ናቸው። ነገር ግን በዱላ፣ በጠመንጃ፣ በማስፈራራት፣ በዛቻ ኢትዮጵያዉያን ለመብታቸው፣ ለነጻነታቸውና ለአንድነታቸው የሚያደርጉት ትግል ሊገቱ አይችሉም። እሳት የለበሱ፣ በወኔ የተሞሉ፣ የስለጠነ ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቷ የሚኖሩ፣ አገዛዙ ከዘረጋዉን የጎሳ ድንበር አልፈው በሰብእናና በኢትዮጵያዊነት የተሳሰሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደ ጥላዬ ታረቀኝ ኢትዮጵያ አፍርታለች።

No comments: