Wednesday, August 27, 2014

የኢቲቪ “ያልተገሩ ብዕሮች” ዘጋቢ ፊልምና ያልተገራው አቀራረብ

August27/2014
d3

ከሁለት ሰአቱ የኢቲቪ ዜና አወጃ ተከትሎ የቀረበውን “ያልተገሩ ብዕሮች” ዶክመንተሪ በደረቁ ሌሊት ድጋሜ ስርጭቱ ተከታትየ ጨረስኩት … ላፍታ እንደተጠናቀቀ ዝም፣ ጭጭ አልኩና በሃሳቤ በህዝብ ገንዘብ ከፍተኛ ወጭ እየተደረገባቸው የሚሰራጩትን የመንግስት የህትመት ጽሁፍና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን አሰብኳቸው … በምናብ ብዙ ርቄ ሔጀ በዶለደመ፣ ባልተገራ እና በተባውና  በተገራው ብዕር ውስጥ ራሴን አትኩሮት ሰጥቸ የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች በሃሳብ ተመላለስኩባች! ሰፊ ሽፋን ያለውን ኢቲቪና ራዲዮኑን፣ በየቀኑ እየታተሙ የሚወጡትን እነ አዲስ ዘመንን ጋዜጣንና የመሳሰሉት እሰብኳቸው  … አስቤ አሰላስየ ወደ ደረስኩበት ድምዳሜ ከማቅናቴ በፊት ግን በ”ያልተገሩ ብዕሮች” ዘጋቢ ፊልም ዙሪያ የታዘብኩትን ቀዳሚ አድርጌ የተሰማኝን ላካፍልዎ ወድጃለሁ…
“ያልተገሩ ብዕሮች” …
d1… ስለ ጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ከባለሙያዎች የቀረበው መግለጫ ዘጋቢ ፊልሙ የተነሳበትን አላማ በሚያሳካ መልኩ የተጠናቀረ ስለሚሸት፣ ስለሚመስል አልተመቸኝም። ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወገኖች የሰጡት አስተያየት የግል አመለካከታቸው ነውና ብዘለውም ባዕድ በሆኑት ሙያ የሰጡት ግምገማ  አልተዋጠልኝም።  “ፍየል ወዲህ  ቅዝምዝም ወዲያ ” ሆኖብኝ ልቀበለው አልተቻለኝም፣ አልወደድኩትም! ምስክርነት ግምገማቸውን ያለወደድኩት “የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች አያጠፉም!” ከሚል እሳቤ ተንደርድሬ ሳይሆን ላጠፉት ጥፋት ቅጣት መቅጫ ወፈር ያለ ህግ ተቀምጦ በህግ መጠየቅ ሲገባ ጅምላ ነቀፋን ማቅረብ ባልተገባቸውን ነበር በሚል ነው። የመንግስት ሃላፊዎች የሰጡት ገለጻና ማብራሪያም የተጻፈውን ህገ ደንብ ከማብራራት አልፎ ጥፋት እየተካሔደ  በሆደ ሰፊ መታለፉንና አሁን ግን መንግስት ማምረሩን የሚያስረዳ ከመሆን ያለፈ ፍሬ ነገር የለውም።
ብቻ … ገና ከጅምሩ ዘገቢ ፊልሙ ድምጻቸው በሚስብ ጋዜጠኞችና በምስል ቅንብር ደምቆ፣ መልዕክቱ ግን በህግ በተያዙና በሚፈለጉ ተጠርጣሪ የመገናኛ ባለሙያዎች ላይ ከፍርድ በፊት ጥፋተኝነትን የሚለድፍ ሆኖ ታይቶኛል።  ሳጠቃልለው የ “ያልተገሩ ብዕሮች” ዘጋቢ ፊልም ፍርድ ቤት ገና እያየው ባለውና ባልወሰነባቸው በጦማሪ ጸሃፍት፣ በአምደኞች እና በነጻው መገናኛ ብዙሃን የሚቀርበውን ክስ ለማጠናከር የተሰራ መሆኑ ያሳብቃል፣ ወንጀሉን ለማጠናከርም ለውንጀላው ምስክሮች በመንግስት ቴሌቪዥን የሰማሁትን ያህል ተሰማኝ!
ከዘመነ ጃንሆይ ፣ ዘመነ ደርግና ዘመነ ኢህአዴግ የመንግስትን አቋም እያራመዱ በጣም በወረደ ዋጋ ለነዋሪው በየቀኑ እየታተሙ ይቀርባሉ። ዳሩ ግን ትናንትም ሆነ  ሃገር ምድሩን በሚሞላ ቁጥር የመታተማቸውን ያህል ቁም ነገር አላቸው የሚባሉት ገጾች የስራ ፈላጊዎችን ቀልብ የሚስቡት ማስታወቂያዎችና የጨረታ ማስታወቂያዎች ብቻ መሆናቸውን ቢያንስ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን አውቃለሁ።  ብዙሃኑን ነዋሪ እውነትንና ጠቃሚ መረጃን ቢይዙ አንኳ አጓጉተውት አይገዛቸውም! d4
ወደ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ መስኩም ስናመራ የምናየው እውነታ ተመሳሳይ ነው።  ዘመኑ የመረጃ ነው፣ ዘመነኛ የመገናኛ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ያንጠለጠለው የታደለው ቀርቶ በስማ በለው ከሚነገሩት መስማት የሚናፍቀው የሃገሬ ሰው ቁጥር የትየለሌ ነው። ጭብጥን መረጃ ከሃላፊት ጋር  ይዘው ፈርጀ ብዙ በሆነ መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎችን በፍቅር የሚከታተለው ወገን መረጃ እንደ እለታዊ ፍጆታው የቆጠረው ይመስላል። ዛሬ ዛሬ ከስልጡን ለውጥ ፈላጊ እስከ መደዴው የኔ ቢጤ ያለ መረጃ መተንፈስ አይቻለውም።
አትኩሮት ሰጥቶ ከሚከታተለው የራዲዮ፣ ቲቪ መርጦ ጀሮውን ይሰጣል። ለህትመት ውጤት ለሆኑት ጋዜጣና መጽሄቶችን ያለው እየተጋፋ ገዝቶ፣ የሌላው እየተከራየ መረጃን ይመገባል። ያሻውን ይመርጣል፣ ያሻውን አንቅሮ የመትፋት ያህል አይቀርባቸውም!
በ “ባልተገሩ ብዕሮች ” የቀረቡት ባለሙያዎች ያልመረምሩት እውነታ ይህ ነው። በጥናታዊው ዘገባ የቀረቡት ባለሙያዎች  በዋናነት የህዝቡን ነጻ መረጃ የማግኘት መብት አክብረው ሙያዊ “የተገራ   ያልተገራ ብዕር” ግምገማ አድገው አላሳዩንም።
d2ይልቁንም ቀርበው የደሰኮሩበት የህዝብን ገንዘብ መሰረት አድርጎ ከሚንቀሳቀው ኢቲቪ ይልቅ እየፈራ እየተባም ቢሆን ከጽፈኛ ተቃዋሚዎች ልሳንነት የሚደበውን ኢሳትን ይከታተላል፣  በመንግስት ደጋፊነት የሚፈረጀውን ኢቢኤስን ደረቱን ገልብጦ ማየት ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ራዲዮን ትቶ ጀርመን እና አሜሪካን ብሎም በሃገር ቤት የመንግስት እጅ የለባቸውም የሞላቸውን  የተመረጡ የኤፍ ኤም አዳዲስ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ያምናል ፣ ማየትና መስማትን ይመርጣል። የዚህ ሁሉ የነዋሪው ግልጽ ሽሽት ምን ይሆን የሚለው ዳሰሳ መላ ምት ውጤት በዘገባ በቀረቡት ባለሙያዎች ቢነገረን ያምር ነበር። “ነበር ባይሰበር “…
ይህ የሆነው ለምን ይሆን?  ብዙሃን ነዋሪ ምርጫ እንዲህ የሆነው ምን ቢሆን ነው? እውን ውስጣቸው ባልተገራ ብዕር የታጨቁ መረጃዎች ስለተሞላ ነው ማለት ይቻል ይሆን?  አይመስለኝም በሚል የሚሸፈን ሳይሆን  ህዝቡ የፈለገውን ማየት መስማት አይሻምና ነው ባይ ነኝ! … “ያልተገሩ ብዕሮች” ምንጭ እያስተዋለ መርጧልና ያለተገራው ብዕር በሰፊው ያለበትን ቦታ አሳምሮ ተረድቶታል…! እናም የማይፈልገውን አይቀርበውም ኩሩው ህዝብ እንዲህ ነው!
አይ “ያልተገሩ ብዕሮች!” ? ጊዜ ደጉ፣ መስማት፣ ማየት፣ መናገር መልካም!
ሰላም ለሁላችሁ!

No comments: