Sunday, January 5, 2014

“መሪዎቻችን ነጻ ናቸው! ፍትህ ለወኪሎቻችን! እያልን ትግላችንን እንቀጥላለን” – ከድምጻችን ይሰማ የተላለፈ ወቅታዊ ጽሑፍ

January5/2013

ባለፉት ሁለት አመታት ያሳለፍነው የትግል ወቅት በፍሬዎቹም ሆነ በመስዋእትነቶቹ ብዙ ያሳየን ክስተት አለ፡፡ ከነዚህ አንዱ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ወኪሎቼ›› ብሎ ሊተማመንባቸው የሚችላቸውን ሰዎች በአንድ ድምጽ መርጦ ወደመንግስት ዘንድ መላኩ ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ገና ተቃውሞውን ማሰማት በጀመረ በሳምንታት እድሜ ውስጥ ይህን መሰል ውክልና እውን ማድረጉ አስገራሚም አስደናቂም ሆኖ አልፏል፡፡


‹‹ኮሚቴዎቻችን ወኪሎቻችን ናቸው!›› የሚለው ቃል መፈክር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም መሬት ላይ የወረደና የብዙሀኑን ሙስሊም ህይወት የሚነካ ተግባራዊ ትርጉም አለው፡፡ እንዲሁ ከሜዳ የተገኘ ውክልናም አይደለም፡፡ ይልቁንም የኮሚቴዎቻችን ውክልና ባህላዊውን አካሄድም፣ ብቃትንም፣ ህጋዊነትንም፣ ሃይማኖትንም ሆነ ህብረ ብሄራዊ ስብጥርን ያገናዘበና የሁሉንም መስፈርት ያሟላ ድንቅ የህዝባዊ ድምጽ ውጤት ነው፡፡
ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ ሲኖረው ችግሩን ለመንገር፣ ብሶቱን ለማሰማትና መፍትሄ ለመፈለግ ከመካከሉ መልካም የሚላቸውን ሰዎች መምረጡ ለዘመናት የቆየ አገራዊ ባህላችን ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሰዉን ብሶት ለማሰማት ባለስልጣናት ጋር የሚሄድ አካልን ማክበርም እንዲሁ ከማህበረሰባዊ እሴቶቻችን አንዱ ነው፡፡ እንኳንስ የራስ ህዝብ ወኪል ይቅርና የጠላት ሀይል መልእክተኛ እንኳን ሰብአዊ በሆኑ ማህበረሰባት ዘንድ ሁሉ ይከበራል፡
፡ ኮሚቴዎቻችን የተወከሉበት ስርአት ከግምት ካስገባቸው ነጥቦች አንዱ ደግሞ ይኸው ድምጽን በወኪሎች የማሰማት የዘመናት ልማድ ነበር፡፡ አዎን! የኮሚቴዎቻችን ህዝባዊ ውክልና ከሚጸናባቸውና ተቀባይነት ካስገኙለት መሰረቶች አንዱ ይኸው ነው፡፡ ህዝቡ ብሶቱን ለመግለጽ ተሰበሰበ፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ ተነጋገረ፡፡ ‹‹መንግስትን ማናገር አለብን›› የሚል ውሳኔ ላይ ሲደርስ አፍ ሆነው ችግሩን ሊያስረዱለት የሚችሉ ሰዎችን መረጦ ሀላፊነት አሸከመ፡፡ ሲመርጥ ዝም ብሎ አልነበረም፤ እንደህዝብ የውክልናቸው ቅቡልነት መሰረት የሆኑ ነጥቦችን አገናዝቦ እንጂ!

ከቅቡልነታቸው መሰረቶች አንዱ የኮሚቴዎቻችን ብቃት ነበር፡፡ ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ያውቃቸዋል፡፡ በተሰማሩባቸው ዲናዊ ዘርፎች የነበራቸውን አስተዋጽኦ፣ የማስተባበር ብቃት፣ የንግግር ተሰጥኦና የዳበረ እውቀት በሚገባ ያውቃል፡፡ ድምጽ ሊሆኑለት ዘንድ ምሉእ ብቃትን የተላበሱና የዘመኑንም ቋንቋ መናገር የሚችሉ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ በመሆኑም በፊርማው ወክሎ ሲልካቸው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚችሉ በመተማመን ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ተግባራቸውም ታሪክ ሆኖ መስክሯል፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ባልታወቀ ሁኔታ ህዝቡን ሰላማዊ፣ ጽኑና የሰለጠነ ትግል እንዲያደርግ ማስቻላቸውንና አገራዊ መነቃቃት መፍጠራቸውን ያልታዘበ የለም፡፡

ሃይማኖት ሌላው የቅቡልነት መስፈርት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ይከበራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ አገራችን ህዝቡ ሃይማኖተኛ በሆነበት አገር ደግሞ ለሃይማኖት አባቶች የሚሰጠው ማህበራዊ ክብር የበለጠ ይገዝፋል፡፡ ከትናንሽ የቤተሰብና የትዳር ጸብ አንስቶ እስከትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ድረስ የሃይማኖት አባቶች የሽምግልናም የገሳጭም ሚና አላቸው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በህገ ወጡ መጅሊስና መንግስት ጋብቻ የሚደርስበትን ችግር ለመፍታት ሃይማኖት አባቶችን መምረጡ በእርግጥም ተገቢ ነበር፡፡ ኮሚቴዎቻችን ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ ሰባክያንና ምሁራን ነበሩ፡፡ ይህን እንከን የለሽ ውክልና እንደምን መካድ ይቻላል?

ህጋዊነት ሌላው የውክልናቸው ቅቡልነት መስፈርት ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በአወሊያ መስጊድ ተሰባስቦ ለሁሉም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተመርጠዋል፡፡ የምርጫ ሂደቱ እንከን የለሽ የነበረ ቢሆንም በርሱ ብቻም አልተብቃቁም፡፡ የሁሉም ስም ዝርዝር ተጽፎ በሰፈረበት ወረቀት ላይ እያንዳንዱ ፔቲሽን ፈራሚ ስሙንና አድራሻውን እያስገባ ሶስቱን ጥያቄዎች መንግስት ዘንድ እንዲያደርሱለት ወክሏቸዋል፡፡ ፔቲሽኑ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ከመላው አገሪቱ ከ800 ሺህ በላይ ሙስሊሞች ፈርመው ውክልናቸውን አጽድቀዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የክልል ሙስሊሞችም አወሊያ መስጊድ ድረስ የጁምአ ተቃውሞዎች ላይ በአካል በመገኘት ህዝባዊውን ጥያቄ ለማድረስ የወከሏቸው መሆኑን በይፋ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ድብቅ ታሪክ ሳይሆን በቪዲዮ ጭምር የተቀረጸና የመንግስት አይኖችና ጆሮዎች ባሉበት በግላጭ የተፈጸመ ነው፡፡ ታዲያ ይህን እንከን የለሽ ውክልና እንደምን መካድ ይቻላል?

ኮሚቴዎቻችን ታስረው ክስ እስከተመሰረተባቸው ጊዜ ድረስ በመንግስትም ዘንድ ውክልናቸው ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ መሆኑ የማንዘነጋው ትውስታ ነው፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ባለስልጣናት የካቲት 26/2004 ከኮሚቴዎቻችን ጋር በይፋ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ኮሚቴዎቻችን የተወከሉበትን ፔቲሽን በእለቱ ያቀረቡ ሲሆን ባለስልጣናቱም ውክልናቸውን አጽድቀውና መጅሊሱ ኮሚቴዎቹን ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መፈረጁን ኮንነው፣ ይልቁንም ተቃውሞውን ሰላማዊነቱን አስጠብቀው በማቆየታቸው አመስግነው ነበር፤ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ያልሰጡ ቢሆንም! ‹‹እናንተን አሸባሪ ማለት አብሯችሁ የተወያየውን መንግስት በአሸባሪነት መፈረጅ ነው›› እስከማለትም ደርሰው ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ ውክልናቸውን ቢክዱት ከቶ ምን ይፈይዳል?

መንግስት የኮሚቴዎቻችንን ውክልና ንዶ በአሸባሪነት መኮነኑ በህዝብም ሆነ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አንዳችም ድጋፍ አላገኘም፡፡ ‹‹የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ሳይሆን አሸባሪዎች ናቸው›› ይላል መንግስት፤ ይህን ሲል ግን ብቻውን ነው፡፡ ሳር ቅጠሉ ይቃወመዋል፡፡ ህዝቡ ይቃወመዋል፡፡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቃወመዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ይቃወሙታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በግትርነት መግፋቱን ቀጥሏል… መንግስት ባንድ በኩል…. ቀሪው ሁሉ ደግሞ በሌላ በኩል!!!

መንግስት ያንንም አለ ይሄንን እኛ ወኪሎቻችንን እናውቃቸዋለን! ድምጾቻችንን እንለያቸዋለን! እስከመጨረሻም ከጎናቸው አንለይም! ‹‹መሪዎቻችን ነጻ ናቸው! ፍትህ ለወኪሎቻችን!›› እያልን ትግላችንን እንቀጥላለን …. እስከድሉ ደጃፍ ድረስ!

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

No comments: