Tuesday, January 14, 2014

አፈንዲ፣ ጃዋር መሐመድ እና የቴዲ አፍሮ ጉዳይ

January 14/2014

teddy and jawar



የሰሞኑ የነ ጃዋር ሲራጅ ግርግር ለኛም ስም አትርፏል፡፡ እንደፈቀደው ይሁን፡፡ እኛ ጉዳያችን ሞልቶልናል፡፡ የታቀደው የቴዲ ኮንሰርት በመሰረዙ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ በኮንሰርቱ ታክኮ ሊከሰት የሚችለው የህዝብ መተላለቅ በመቅረቱ እሰየው ነው፡፡ ብርና ዝና ብቻ እያሰቡ የህዝብ መጨራረስን ሊጋብዙ የነበሩ ሰዎች ተንኮላቸው ስለከሸፈባቸው አላህን በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡
ታዲያ ያስገረመኝ ነገር ስሜት እውነትን ለመሸፈን ምን ያህል ጉልበት እንዳለው መረዳቴ ነው፡፡ አጃኢብ ነው! ግጭትና ትርምስ ሲሰበክ የነበረው በውሸት የተፈጠረውን ወሬ እንደ ሰበብ በማድረግ ነው፡፡ ውሸቱን ለማዳመቅ በግርግሩ ውስጥ የገቡ ሀይሎች አበዛዝም ያስገርማል፡፡ ከአሜሪካ እስከ ኖርዌይ፣ ከለንደን እስከ ሸገር እየተጠራሩ ሽብሩን ለማጋጋል የተደረገው ጥረት አስደናቂ ነበር፡፡ ለወትሮው በአንድ ብሄር ላይ የሚደረግ ዘረኛ ቅስቀሳን እንቃወማለን ሲሉ የነበሩ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ከኛ ጋር ተባብረው ግጭት እንዳይከሰት ጥረት ያደርጋሉ ብለን ስንጠብቅ የኛ ተቃራኒ መሆናቸው አስገርሞናል፡፡ ለምሳሌ እነ ዳንኤል ብርሃኔ “ቀኝ አክራሪዎች እንዲህ አደረጉ” እያሉ ሲጽፉት የነበረው ነገር በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ነገሮችን በስሜት በመቀበል እውነትን ከውሸት ለመለየት ጥረት አለማድረጋቸው አስቂኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ለምሳሌ በግርግሩ መጀመሪያ ሰሞን “መጽሔቱ ቃለ-ምልልሱን አትሞ አውጥቶታል” ሲባል ከርሞ “ሁለት ዓይነት መጽሔት ነው የታተመው” የሚል ነጠላ ዜማ ተለቀቀ፡፡ ከዚያ ለጥቆም “መጽሔቱ አከራካሪውን ቃለ-ምልልስ ቆርጦ አስቀርቶታል” ተብሎ ተወራ፡፡ “የተቆረጠው ክፍልም ይኸውላችሁ” ተብሎ በአንዳንድ ዌብሳይቶች ላይ ተለጠፈ፡፡ በመጨረሻው ላይ ጭራሽ የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኦዲዮ ተቀርጾ በእጃችን ገብቷል የሚል ማስመሰያ ተፈጠረ፡፡ ይህ ሁሉ የውሸት ወሬ ነው፡፡ በግርግሩ የተሳተፉት ግን አንዱንም ለማጣራት አልሞከሩም፡፡ “ጀዋር የተናገረው ነገር ምንጊዜም እውነት ነው” የሚል መመሪያ ያላቸው ነው የሚመስለው፡፡ (ያሳቀኝ ነገር ቴዲ አፍሮ ራሱ መጽሔቱ “ቅዱስ ጦርነት” በሚለው ርዕስ አለመታተሙን ያላወቀ መሆኑ ነው፤ እንደዚያ ዓይነት ርዕስ ያለው መጽሔት በጭራሽ አልታተመም)፡፡
እኛ ለቴዲ አፍሮ አልነበረም የተከራከርነው፡፡ ቴዲ ተናገረ የተባለው ቃል ትክክል ነው ያለ ሰው የለም፡፡ በደሌ መጠጣትን አቁሙ መባሉንም የተቃወመ ሰው የለም (እኛ እንዲያውም አስካሪ መጠጥ የተባለ በሙሉ ቢወገድ ነው የምንፈልገው)፡፡ እኛ ያልነው በሀሰተኛ ወሬ ሰውን ለማጨራረስ አትሞክሩ ነው፡፡ ይህንን ሀሰተኛ ወሬ የሚያራግቡ ሀይሎች ድብቅ አጀንዳ አላቸው ነው ያልነው፡፡ ይኸው ነው መልዕክታችን፡፡
ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ቴዲ አፍሮ በትክክል “ቅዱስ ጦርነት” የሚለውን ቃል ተናግሮ ቢሆን እንኳ መደረግ የነበረበት በፍትሕ መንገድ መፋረድ ነው፡፡ ሆኖም የግርግሩ አድማቂዎች በቀጥታ ወደ ዘረኝነት ቅሰቀሳ ነው የገቡት፡፡ ያሳዝናል! የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ ይህ አልነበረም፡፡ የህዝቡ ትግልም ከስርዓቶች ጋር ነው እንጂ ከሰፊው የአማራ ህዝብ ጋር አይደለም፡፡
በኔ በኩል የምችለውን አድርጌአለሁ፡፡ በአላህ እርዳታ የምፈልገውን ውጤት አግኝቼበታለሁ፡፡ ህዝቦቻችን አልተገዳደሉም፡፡ አልተፋጁም፡፡ እነርሱ እንደተመኙት አልተጨራረሱም፡፡ ስለዚህ ባደረግኩት ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ታክል ጸጸት አይሰማኝም፡፡ ወደፊትም እንዲሁ ማድረጌን እቀጥላለሁ፡፡
===መነሻው===
ይህንን ሁሉ ትርምስምስ በአጋፋሪነት የመሩትን እናውቃቸዋለን፡፡ ሁሉም በውጪ ሀገር ተቀማጭ ሆነው ነበር እሳቱን ሲያጋግሉት የነበረው፡፡ ዓላማቸው ሰሞኑን የፈጠሩት የሰንበቴ ማህበር ግዙፍ ስኬት እያስመዘገበ እንደሆነ እንደ መጠቆሚያ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡ ህዝብ ቢጨራረስ ባይጨራረስ ጉዳያቸው አይደለም፡፡
የግርግሩ ዋና አቀናባሪ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንደ ቃል አቀባይ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ግን ጀዋር መሐመድ ነው፡፡ ጀዋር በቅድሚያ ስለጉዳዩ በኔ ኢንቦክስ ሲነግረኝ “የእንቁ መጽሔት ባለቤቶች ጎል ሊያስገቡን የውሸት ሽፋን በፎቶሾፕ ሰርተው በትነዋል” ነው ያለኝ፡፡ እናም “ይህንን መጽሔት መበቀል አለብን” በማለት ሊቀሰቅሰኝ ሞከረ፡፡ “እንቁ ማለት የማይታወቅ መጽሔት ነው፤ ነገሩን ባናጋግለው ይሻላል” አልኩት፡፡ እርሱ ግን “አይደለም! በጣም ግዙፍ የሆኑ ነፍጠኞች ናቸው በገንዘብ የሚደጉሙት” ብሎ ሊያነሳሳኝ ሞከረ፡፡ እኔ በበኩሌ የሰውዬው አጉል ብልጠት ስለሚደብረኝ ግድ አልሰጠሁትም (እርሱ የሚያወራውን ነገር ሁልጊዜ በጥርጣሬ ነው የማየው)፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱን ላለመገናኘት ስሸሸው ቆየሁ፡፡ በዚህ መሀል ቴዲ ሰጠ ስለተባለው ቃለ-ምልልስ ሐቁን ለማወቅ ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ እናም ውሸት መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡
ታህሳስ 14/2006 ከጀዋር ጋር በሌላ ጉዳይ ስንገናኝ ግን ቀደም ሲል ውሸት ነው ሲለው የነበረውን ነገር “እውነት ነው! የኦዲዮ ማስረጃ ጭምር አለን፤ የመጽሔቱ አዘጋጅ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል” የሚል ማሻሻያ ሰጥቶት ከርሱ ጋር እንድሳተፍበት ይጨቀጭቀኝ ጀመር፡፡ ነገሩ ውሸት ነው ሳልለው “ይህንን ነገር ከማጋጋል መቆጠቡ ይመረጣል” ብዬ ላቀዘቅዝ ሞከርኩ፡፡ እርሱ ግን “እምቢ! ቴዲን አፈር አባቱን ሳናበላው አንተወውም፤ አንተ ደስ ካለህ እንደ ፈለግክ ሁን” እያለ ይፎክርብኝ ገባ፡፡ ለፉከራው ግድ ባይኖረኝም ለራሱ ዝና ሲል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነት በመጠቀም ስለሜንጫው የፎከረውን ቃል ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል ብዬ ፈራሁ፡፡ እና የርሱን እንቅስቃሴ የሚያኮላሽ እርምጃ መውሰድ አለብኝ በማለት ወሰንኩኝ (በወቅቱ እኔም እንደርሱ በቢራ የምንቦጫረቅ መስሎት “በደሌ መጠጣት አቁም” ሲለኝ ለጥቂት ነበር ከመሳደብ ራሴን የተቆጣጠርኩት!)፡፡
***** ***** *****
ይህ ሰው በጣም አጭበርባሪ ነው፡፡ የውሸት ወሬ መፈብረክ ይችልበታል፡፡ ደግነቱ የሚፈበርካቸውን ወሬዎች ሀሠትነት ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ አይፈጅም፡፡ የዚህ ሰው ሌላኛው ባህሪ ደግሞ ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖችና ፓርቲዎች የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡ ሰውዬው ከላይ ሲታይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ይመስላል፡፡ ሆኖም አብዛኛው ሰው እንደሚያውቀው ከኦፒዲኦ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ አንድ ቀን ሳያስበው ይህንን ግንኙነቱን ግልጽ ያደረገበትን ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡ እኔ በሰጠሁት ምላሽ ሳስደነግጠው ትንሽ እንደማፈር ብሎ ዘጋው (በወቅቱ የጠየቀኝን ጥያቄ ሌላ ጊዜ ብነግራችሁ ይሻላል)፡፡ በርሱ ቤት ነገሩን የማላውቅ መስሎታል፡፡ ይሁንና በፌስቡክም ጭምር በሰፊው ሲባል የነበረ ነገር በመሆኑ ብዙም አልደነቀኝም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው ከኦነግ-ቀመስ ቡድኖችም ጋር በትክክል እንደሚሰራ መረጃው አለን፡፡ ከሻዕቢያ ጋር እንደሚሰራም ውስጥ ውስጡን ይወራል፡፡ እነዚህ ግንኙነቶቹ ቀደም ብዬ የሰማኋቸው በመሆኑ ብዙም አላስገረሙኝም፡፡ በጣም የተደነቅኩት ግን “ነፍጠኛ” እያለ ቀን ከሌሊት ከሚሰድባቸው ቡድኖችም ጋር የሚሰራ መሆኑን እራሱ በነገረኝ ጊዜ ነው፡፡ የዚያን ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት (ዕለቱ ህዳር 7/2006 ነው)፡፡ “ይህ ሰው ጥቅም ካገኘ ለሰይጣንም ይሰራል ማለት ነው ለካ!” በማለት ተደመምኩበት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዚህ ሰው ጋር የማደርገውን የመልዕክት ግንኙነት ገታ ማድረግ ጀመርኩ (እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ማስረጃው በእጄ ነው ያለው)፡፡
ሰውዬው ከነዚህ ሁሉ ቡድኖች ጋር የሚሰራበት ዓላማ ገንዘብና ዝና ማግኘት ይመስለኛል፡፡ በየሀገሩ እየዞረ ብር እንደሚለቅምም ይታወቃል፡፡ እኔ በበኩሌ በግርግሩና በጉዞው ብር ቢያገኝበት ጉዳይ የለኝም፡፡ ብር አገኝበታለሁ ብሎ የማይገባ ድራማ ሲጫወት ግን ዝም ብዬ ላልፈው አልፈቀድኩም፡፡ የጸረ-በደሌውን ዘመቻ በጎን በኩል የተጋፈጥኩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ አስቡት እስቲ! የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመታደም ድሬዳዋ ስቴድየም በተገኘው ህዝብና እርሱን በሚቃወመው ህዝብ መካከል ግጭት ቢፈጠር ውጤቱ ምን ሊሆን ነው? በዚያ ውጤትስ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው? አማራው ነው? ኦሮሞው ነው? ወይንስ ማን ነው? እስኪ እናንተው መልሱት፡፡ … የጃዋር የፖለቲካ ተንታኝነት ይህ ነው እንግዲህ!…(እንኳንም ኮንሰርቱ ቀረ! እሰይ!)
ከዚህ ሰው ጋር የተዋወቅኩት በኢንተርኔት ነው፡፡ የምጽፋቸውን ጽሑፎች በዌብሳይቱ ለመጠቀም በፈለገበት ጊዜ ሲያነጋግረኝ ነው ያወቅኩት፡፡ ከዚያ ውጪ ሌላ ትውውቅ የለንም፡፡ ለአንድም ቀን አይቼው አላውቅም፡፡ እኔ የጻፍኳቸውን ጽሑፎች ከኔ የፌስቡክ ፔጅ ላይ እየወሰደ ዌብሳይቱ ላይ ይለጥፋል፡፡ በቃ ይኸው ነው፡፡ ባለፈው ክረምት ደግሞ “ያንተን መጽሐፍ እናሳትማለን” የሚል ቃል ሰጠኝ፡፡ በጥቅምት ወር መጨረሻ ገደማ ግን የመጽሐፉ ጉዳይ ቀረና መጽሔት እንጀምራለን ብሎ መጣ፡፡ የመጽሐፉ ጉዳይ መቅረቱ ሆዴን እየበላኝ ብቸገርም እስቲ ትንሽ ልመርምረው ብዬ አብሬው ሰነበትኩ፡፡ ይሁንና ከህዳር ወር 10/2006 ወዲህ የመጽሔቱም ነገር የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ (የማያደርገውን ነገር በስሜት የሚያወራው እንዲህ ዓይነቱ ቀጣፊ ሰው በድሬዳዋ ልጆች ቋንቋ “ሐጂ ቅደደው” ወይንም “ሐጂ ቦንባ” ነው የሚባለው)፡፡
የሆነ ሆኖ የአሁኑ ግርግር ከዚህ ጉዳይ ጋር አይገናኝም፡፡ መጽሔት እናዘጋጃለን ብዬ የለፋሁበትን ድካም መና ስላስቀረብኝ ቂም ቋጥሬ አይደለም ልጋፈጠው የወሰንኩት፡፡ እርሱ ያመጣው ሎጂክ እጅግ አደገኛና ህዝቦችን የሚያጨራርስ በመሆኑ ነው ዝም ማለቱን ትቼ በቀጥታ የገባሁበት (መጽሔቱን በራሴ ወጪ ይፋ አደርገዋለሁ)፡፡
===ታሪክ ====
እኔ የታሪክ ምሁር አይደለሁም፡፡ ግን ስለታሪክ አንብቤአለሁ፡፡ በተለይ ስለ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ በደንብ ነው ያነበብኩት፡፡ ከሰሞኑ ግርግር ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የአጼ ምኒልክንም ታሪክ አንብቤአለሁ፡፡ ነገር ግን ግርግሩ በተጋጋለበት ወቅት ስለርሱ ትንፍሽ አላልኩም፡፡ ወደፊትም እንዲህ አይነት አደገኛ አሻጥር የተመላበት ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት ግጭትን የሚያጋግሉ ታሪኮችን አልቆሰቁስም፡፡ ግጭት ሲቀሰቀስ ተጠቃሚው ህዝብ ሳይሆን የህዝብ ጠላት ነው፡፡
አጼ ምኒልክ ደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያን ከግዛተ መንግሥታቸው ጋር ለመቀላቀል ያደረጉት ጦርነት ከፍተኛ እልቂትና ፍጅት የተፈጸመበት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሊታሰቡ የማይገባቸው አጸያፊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ህዝቦች የገዛ መሬታቸውን ተነጥቀው በትውልድ ቀዬአቸው ጭሰኛ ለመሆን ተገደዋል፡፡ ይህንን ታሪክ የምኒልክ ጸሐፊ ከነበሩት ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ-ሥላሴ ጀምሮ በርካቶች በድርሳናቸው ጽፈውታል፡፡
ታዲያ የአጼ ምኒልክ ጦር ያኔ ለፈጸመው ጥፋት የአሁኑ ትውልድ ዕዳ ከፋይ የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ዘመን ያለው ትውልድ ያለበት ሃላፊነት ከታሪክ ተምሮ የያኔው ጥፋት እንዳይደገም መከላከልና የህዝቦች የመብት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ እንዲያገኝ አብሮ መታገል ነው፡፡ ታሪክን የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ እያደረጉ እልቂትና ሁከትን መቀስቀስ የህዝቦችን ትግል ወደኋላ ማስቀረት እንጂ ለህዝቦች የመብት ጥያቄ አንዳች መፍትሄ አያመጣም፡፡
የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ስለ አጼ ምኒልክ አልጽፍም ያልኩት አንደኛ ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ነው፡፡ ስውር ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ህዝቦችን ለማጨራረስ ስለአጼ ምኒልክ በሚነዘንዙበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን መጻፍ እነርሱ በሚፈልጉት ወጥመድ ውስጥ ራስን ማስገባት ነው፡፡ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ታሪኮች በአብዛኛው የሚያወዛግቡን በመሆናቸው ታሪኮቹን በሶሻል ሚዲያ ላይ እያመጡ መለጠፍ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ታምራት ነገራ እንደጻፈው እንዲህ ዓይነት የሚያነታርኩ ታሪኮችን በፌስቡክ ላይ መለጠፍ ሌሎች ታላላቅ ህዝባዊ አጀንዳዎች እንዲረሱ መንገድ መክፈት ነው፡፡ ታሪኩን ማወቅ የሚፈልግ ሰው በታሪክ ምሁራን የተጻፉ ድርሳኖችን ቢያገላብጥ ነው የሚሻለው፡፡ ሶስተኛ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን መጻፍ እኔ ፌስቡክን ከምጠቀምበት ዓላማ ጋር በጭራሽ የማይሄድልኝ በመሆኑ ነው፡፡
===ትምህርት===
ይህ ግርግር ከተጀመረ ወዲህ ብዙ ተብዬአለሁ፡፡ በወረዱ ቃላት ተሰድቤአለሁ፡፡ አብዛኛው ተሳዳቢ የማያውቀኝ ስለሆነ ምንም አልተሰማኝም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሚንጫጩበት ግለት ግን በጣም አስደንቆኛል፡፡ ይገርማል! አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡
ወላጅ አባቴ ለኦሮሞ ህዝብ በተደጋጋሚ ጊዜአት ታስሮ፣ ተደብድቦ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረቱን አጥቷል፡፡ ትግሉ ሲጀመር ጳጉሜ 5/1966 ቀን የመጀመሪያ ሰማዕት ሆኖ የወደቀውና ሬሳው ረጅም ርቀት የተጎተተው ሰው አሕመድ ተቂ (ሁንዴ) የተሰኘው አጎቴ ነው (ጓደኛው ኤለሞ ቂልጡ በዚያው ቀን ነው የሞተው፤ ሆኖም በወቅቱ የአካባቢው ጸጥታ ሀይሎች ስላላወቁት እዚያው የወደቀበት ቦታ ላይ ትተውት ሄደዋል፤ እስከዛሬ ድረስ ያንን የመሰለ ጀግና ገበሬዎች በአንድ ገደል ጥግ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ራቅ ብሎ ተኝቷል፤ እነ ጀዋርን የመሳሰሉ ሰዎች ግን ሬሳውን እንኳ ደህና ቦታ ስለመቅበር ጉዳይ ላይ ሳይመካከሩ በየስርቻውና በየፓርቲው “ኤለሞ” እያሉ ቱሪናፋ ይነዛሉ… ሐፍረተ ቢስ! አዳማ ውስጥ ደግሞ በርሱ ስም ትልቅ ግንብ አቁመዋል፤ ሬሳውን እንቅበር ብሎ የጠየቀ ሰው ግን እስከ አሁን ድረስ የለም፤ እኛ ከጠየቅን “ሌላ ተልዕኮ አላችሁ” እንባላለን፤ ጉድ እኮ ነው)፡፡
አባቴ የታናሽ ወንድሙን ሬሳ ካየበት ደቂቃ ጀምሮ አዕምሮው ተነክቷል፡፡ ኑሮው የቀን ጭለማ ሆኖበት ከሰው ተለይቶ በራሱ መንገድ ለብቻው ነው የኖረው፡፡ ደርግ ሲወድቅ ያለ አዋጅ የተወረሰበትን አንድ ክፍል ቤቱን እንዲመልሱለት ጥረት አድርጎ ተከልክሏል፡፡ በዚያው ከተማ ውስጥ ግን እስከ አምስት ክፍል ቤት ያላቸው ሰዎች (ለዚያውም በአዋጅ የተወረሱ) ተመልሶላቸዋል፡፡ በዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ አባቴን የት ነህ ብሎ የጠየቀው ሰው የለም፡፡ ከርሱ ጋር የምንቸገረው እኛ ልጆቹ ነን፡፡ አሁንም የድሮው ግርፋት አገርሽቶ እግሩን ፓራላይዝ አድርጎት ሲያስቀምጠው ከርሱ ጋር እየተቸገሩ ያሉት ልጆቹ (በተለይ ሴት ልጁ) ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ “እናውቅሃለን፤ ዘመድህ ነን” ባይ ወገኖች “አባትህ የት ደረሰ” ብለው ጠይቀውኝ እንኳ አያውቁም፡፡ እኔም ነገ ብቸገር የሚገጥመኝ ዕድል ይኸው ነው፡፡ እነዚህ ቱሪናፋ የሚነፉት ወሽከሬዎች ጉዳይ ኖሮኝ እገዛ ብጠይቃቸው አካውንት ዲአክቲቬት እስከማድረግ ይደርሳሉ፡፡ በተለይ ዘላለም ወዬሳ የሚባለው የኦነግን ማሊያ የለበሰ የኦፒዲኦ አገልጋይ “በኦሮሞ እጅ አድገህ፣ የኦሮሞን እንጀራ በልተህ፣ የኦሮሞን ልብስ ለብሰህ፤ ዛሬ ኦሮሞን ከዳህ”… እያለ ሲዘባርቅ ከቤታቸው ኩሽና በየቀኑ እንጀራ በወጥ ሲያቀብለኝ የኖረ ነበር የሚመስለው፡፡
ምሁራን ነን ተብዬዎቹም ኤለሞ ቂልጡን ሲያወድሱት ሳት ብሎአቸው እንኳ በዚያው ቀን በዚያው ሜዳ ላይ ከኤሌሞ ቀድሞ የሞተውንና በርሱ ሰበብ መላው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር የታመሰበትን የሰማዕት አጎቴን ታሪክ በአንድም መጽሔትና መጽሐፍት ሲያነሱት አይቼ አላውቅም (እርግጥ አንድ ጊዜ የድሮው የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ገላሳ ዲልቦ ገለምሶ ከተማ መጥተው የአጎቴን ስም ሲያነሱት ሰምቻለሁ፤ ”ግዝትና ግዞት” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥም ስሙን አይቼዋለሁ፤ ቴዎድሮስ ሙላቱ በጻፈው አኬል ዳማ ውስጥም ታሪኩ በጥቂቱ ተጠቅሷል፤ ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐሰንም በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ ውስጥ አንዴ ስሙን የጠቀሰው ይመስለኛል፤ እነዚህን አራቱን ብቻ በቤተሰቤ ስም አመሰግናቸዋለሁ፤ ከዚህ የተቀረው ሁሉ አስመሳይ ነው)፡፡
ለረጅም ገዜ የዚህ አጎቴ ታሪክ መረሳት በጣም ያንገበግበኝ ነበር፡፡ እናም ታሪኩ መጻፍ አለበት ብዬ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ መለስተኛ ጽሑፍ በዊኪፒዲያ ውስጥ ያስቀመጥኩት እኔ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እርሱን ለማወቅ በሚል መጠነኛ ግርግር የተጀመረው፡፡ ከማንም በፊት አጎቴን ያስታወሰው ግን ዓሊ ቢራ ነው፡፡ ገጣሚው አቡበከር ሙሳ እና ዓሊ ቢራ በጋራ ምስጋና ሊደርሳቸው ይገባል፡፡ “ያ ሁንዴ በሬዳ” የተሰኘው ዜማ የተጻፈው ለአጎቴ ለአሕመድ ተቂ ሼኽ ሙሐመድ-ረሺድ ነው (በነገራችን ላይ ዓሊ ቢራንም ለመጀመሪያ ጊዜ በዊኪፒዲያ ያስገባሁት እኔ ነኝ፤ ዓሊ ቢራ ለአጎቴ ማስታወሻ የሰራውን ስራ ለማክበር ይሆን ዘንድ ነው ታሪኩን በዊኪፒዲያ የጻፍኩት)፡፡
ታዲያ የአጎቴ ስም አለመነሳቱ አንዳንዴ ለበጎ ነው ያሰኘኛል፡፡ በርሱ ጦስ የአባታችን ህሊና ተቃውሶ የአባት ፍቅር በደንብ ሳይገባን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ በ1975 ከእስራት ወጥቶ ከዝርፊያ የተረፈውን ገንዘብ ዝም ብሎ ሲበትን ጸባዩን ማስተው ያቃታት እናቴ እኛን ለማሳደግ ያሳለፈችው ስቃይ እስከ አሁን ድረስ ውስጤን ያነደኛል፡፡ በተገደለው አጎቴ ሰበብ ሌላኛው አጎቴም (ኢስራፊል ይባላል) አዕምሮው ተነክቷል፡፡ ሟች እናታቸው መርየም “ልጄ አህመድ ተቂ” እንዳለች ነው ህይወቷ ያለፈው፡፡ ወላጅ አባቱ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ግን የአላህ ሰው ስለሆኑ ትዕግስቱ ነበራቸው፡፡ የአጎቴ ጓደኞች የነበሩት እነ ነጃሽ ዒስማኢል፣ ሙሐመድ በከር፣ ዒስማኢል አሕመዩ፣ ሙሐመድ አብዶ (ሉንጎ) የመሳሰሉት ድንቅ ነጋዴዎች ፣ በግርፋትና ቶርች ብዛት ናላቸው ዞሮ ያለ ጊዜአቸው ከስራው ዓለም ተሰናብተው የሰው ጡረተኛ ለመሆን ተገደዋል (ሉንጎ ከድብደባ ብዛት ዐይኑን አጥቷል)፡፡ የአጎቴን ታሪክ ማንሳት የሚችሉት በርሱ ሰበብ እውነተኛውን ስቃይ ያዩት እነዚህ ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ ምድረ አጭበርባሪ መንገደኛ ሁሉ ስሙን እየጠራ መነገጃ እንዲያደርገው አንፈቅድም፡፡
የኔ አጎት የሞተው ለኦሮሞ መብትና ነጻነት ሲል ነው፡፡ አጎቴ አማራን ለመጨፍጨፍ አይደለም ጫካ የገባው፡፡ ከአማራዎች ጋር በጉርብትና ሲኖርና በጋራ ሲሰራ የነበረ ሰው ነው፡፡ እርሱ የታገለው ጨቋኙን ስርዓት ነው እንጂ የአማራ ተወላጆችን አይደለም፡፡ የርሱን ታሪክ ከበደሌ ቢራ ጋር እያገናኛችሁ ማስጠንቀቂያ ልትሰጡኝ የምትሞክሩት ሀይሎች ህልመኞች መሆናችሁን እወቁ፡፡ ለራሳችሁ ሰው የመጨፍጨፍ ዓላማ ካላችሁ በግልጽ አሳውቁን፡፡ የአጎቴን ስም ግን አለቦታው አታንሱት፡፡ እዚያው መቃብሩ ውስጥ በሰላም ይተኛበት፡፡
*****
እንግዲህ አፈንዲ ማለት ይህንን ሁሉ ታግሶ ዝም ያለ ሰው ነው፡፡ ዛሬ “አፈንዲ ጉራጌ ነው፣ አደሬ ነው፣ ጎበና ነው ጂንኒ ጀቡቲ” እያሉ የሚጯጯኹት ታሪክን መሸጥ የለመዱ አስመሳዮች ናቸው፡፡ “ህዝብን ማጋጨት አቁሙ” ማለት ጎበና ከሆነ በእርግጥም ጎበና ነኝ (አንዳንዶች ጭራሽ የጻፍኩትን ሳያገናዝቡት “አባት ማር ስለበላ የልጅ አፍ ጣፋጭ አይሆንም” እያሉ ሊተርቱ ይፈልጋሉ)፡፡
ሰማችሁ ወይ! እኔ ልረዳችሁ ብዬ ነው እንጂ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል፡፡ አንድም ነገር የመጻፍ ግዴታ የለብኝም፡፡ በአባቴ ላይ የደረሰውን ስቃይ እያየሁ ያደግኩ በመሆኔ ከርሱ ህይወት በቂ ትምህርት ወስጄአለሁ፡፡ የሚያሳዝነኝ እንዲህ የሚነገድበት ህዝብ ለሁሉም ነገር ባይተዋር መሆኑ ነው፡፡ ለሁሉም ትምህርት ወስጄበታለሁ፡፡
===የኔ ዓላማ===
ከዚህ ቀደም እንደጻፍኩት እኔ የፖለቲካ ዓላማ የለኝም፡፡ የኔ ጉዳይ ያለው ከህዝብ ዘንድ ነው፡፡ የማንኛውም ህዝብ መብትና ነጻነት እንዲከበር ጽኑ ፍላጎቴ ነው፡፡ የአንዱን ህዝብ መብት ለማስከበር ሌላውን መንካት ትክክለኛ ነገር አይደለም፡፡ እኔ የወጣሁበት የኦሮሞ ህዝብ መብት የሚከበረው የአማራን ህዝብ በመጨቆን አይደለም፡፡ የአማራውንም መብት ማስከበር የሚቻለው ኦሮሞን በመጨቆን አይደለም፡፡ የጭቆናው ደረጃና ስልት ቢለያይም ሁሉም ህዝብ መብቱን ፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ለህዝቦች መብት የሚታገሉ ወገኖችና ቡድኖች ይኑሩ፡፡ እኛ ደግሞ ይህ የመብት ትግልና በርሱ ምክንያት ከሌላ አቅጣጫ የሚሰነዘረው ግብረ-መልስ ውላቸውን ስተው ሌላ አቧራ እንዳይቀሰቅሱ የመከላከሉን ስራ እንስራ፡፡ በህዝቦች መካከል ፍቅርና ወንድማማችነትን እናጎልብት፡፡
የኔ የምንጊዜም ፍላጎትና ዓላማ ይህ ነው፡፡ ከተወለድኩበት የኦሮሞ ህዝብ በፊት በሀረሪ ህዝብ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ የጻፍኩት በዚህ መንፈስ ነው፡፡ ከገለምሶ የተገኙትን የመምሬ ሙላቱ እና የሼኽ ዑመር ገለምሲይ አስደሳች ታሪኮችን ጽፌ በፌስቡክ እና በድረ-ገጾች ላይ የለጠፍኩት ለዓላማችን መሳካት ያግዘናል በሚል ነው፡፡ ሰዎች የፖለቲካ ታጋይ መስዬአቸው በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዱኝ በሚል ልዩ ልዩ ማስታወሻዎችን ለጥፌ ያስነበብኩት “ፖለቲካው አይመለከተኝም” ብዬ ሳይሆን በዚህ ገጽ ላይ ፖለቲካ እንደማላካሄድ ለማሳወቅ በሚል ነው፡፡
አፈንዲ ሙተቂ
አፈንዲ ሙተቂ
ወደፊት በዚህ ገጽ ከኔ ጋር መማማር የሚፈልግ ሰው በዚሁ መንገድ ከኔ ጋር ሊቀጥል ይችላል፡፡ ለኔ የሚከፍል ይመስል እየተሳደበ፣ ቡራ ከረዩ እያለ፤ እየተራገመ ወደርሱ መንገድ እንድገባለት የሚሻ ሰው ካለ ግን በሰላም ወደመጣበት ቢሄድልን እንመርጣለን፡፡ እኛ ለፈጣሪ እንጂ ለሌላ ሀይል አጎብድደን የማናውቅ ሰዎች ነው፡፡ ህሊናችንንም ለገንዘብ ቸብችበን አናድርም፡፡
===ያክብርልኝ===
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በገጠምኩት ሙግት ብዙዎች (65 %) የሚሆኑት ከኔ ሃሳብ ጋር ተግባብተዋል፡፡ ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡ በተለይ ግን መንሱር አሊዩ፣ ጃዕፈር ሰይፊ (ጃፈር አሕመድ)፣ ፊርዶስ ሐሶ፣ ዑስማን አሕመድ፣ ያሕያ ሙሐመድ፣ ጀሚል ይርጋ፣ ፍጹም ታዬ፣ ታጠቅ ወንድሙ፣ ተካበ መኮንን፣ የሚባሉ ጓደኞቼን በጣም አመሰግናቸዋለሁ (ምክንያቱን ወደፊት ብነግራችሁ ይሻላል)፡፡
——–
ሰላም
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 26/ 2006
Afendi Muteki is a researcher and author of ethnography, history and art with special focus on Eastern Ethiopia.

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ 

No comments: