Friday, January 31, 2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት መተማ አካባቢ ጥቃት ፈጸምኩ አለ

January 31/2014

(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የአገራችን ኢትዮጵያን ዳር ድንባር ለሱዳን ለማስረከብ ሽር ጉድ እያለ የሚገኘውን የወያኔን አገዛዝ ጸረ-አገርና ጸረ-ህዝብ እንቅስቃሴ በመቃወም በመተማ አካባቢ ልዩ ስሙ ዘባጭ ባህር በተባለ ቦታ ከወያኔው 24ኛ ክፍለ- ጦር ጋር በጥር 21- 2006 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሠዓት ላይ ባደረገው ውጊያ 14(አስራ አራት) ገድሎ 12(አስራ ሁለት) ማቁሰሉን አርበኛ ኑርጀባ ለዘ-ሐበሻ በላከው መረጃ አስታውቋል::

“በመተማና አካባቢው በተደጋጋሚ በአርበኛው ጥቃት እየተፈፀመበት የሚገኘው የወያኔው ቅጥረኛ ሠራዊት ህይወቱን ለማትረፍ እግሩ ወደመራው እየፈረጠጠ መሆኑ ሲታወቅ በደረሰበትም ጉዳት ማካካሻ ይሆነው ዘንድ ሰላማዊውን ነዋሪ በእናንተ ምሽግነት ነው እየተመታን ያለነው በሚል እንግልት እያደረሱበት መሆኑ ታውቋል።” የሚለው የአርበኛ ኑርጀባ ዘገባ “በተያያዘ ዜናም በጭልጋ ወረዳ ጫቁ የተባለ አካባቢ ነዋሪዎች ከብት፣በግና ፍየል በአካባቢው የወያኔ ታጣቂዎች እየታረደ እየተበላባቸው መሆኑ ታውቋል” ብሏል።

አርበኛ ኑርጀባ ዘገባውን ቀጥሎ “በዚሁ አካባቢና አጎራባች ወረዳዎች የወያኔው ተላላኪዎች ተደጋጋሚ ንብረትን የመዝረፍ ሂደት የተቆጣው ነዋሪ ለምንድን ነው ንብረታችንን የምትዘረፉት ምን አደረግናችሁ ብለው ሲጠይቁ እናንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ፣መንገድ መሪዎች እንዲሁም ስንቅ አቀባዮች ናችሁ የሚል ምክንያት ሰጥጧቸዋል። ሕዝቡም እኛ የአርበኛው አባልም ደጋፊም አይደለንም ከፈለጋችሁ እነሱን ተከታትላችሁ መዋጋት ትችላላችሁ እኛን ምን አድርጉ ነው የምትሉ? ሲሉ ምሬታቸውን ቢገልፁም እንግልቱ እንዳላበራ” ከአርበኛ ኑርጀባ መረጃ መረዳት ተችሏል።

ዘገባው ቀጥሎም “የወያኔው ተላላኪዎች በሕዝቡ ላይ እያደረሱ ያለው እንግልት ያስቆጣቸው ብዛት ያላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኛች ግንባር ሠራዊትን እየተቀላቀሉ መሆኑን አስታውቋል።” ብሏል።

“በሌላ ዜና የአማራ ክልል ፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ የሆነው ሙሉጌታ ወርቁ የተባለው ግለሰብ በክልላችን ቢሮዎች በሙሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰዎች ተሰግስገዋል በሚል ምክንያት ሰሞኑን በየወረዳው ፅ/ቤት የማፅዳት ዘመቻ በሚል ከፍተኛ ስብሰባ እያደረገ ነው” ሲል አርበኞች ግንባር አስታወቀ። ግንባሩ ለዘ-ሐበሻ በላከው ዜና ” የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ተደጋጋሚ ጥቃት እያሰጋው የመጣው ሆድ አደሩ የአማራው ክልል ባልስልጣናት ሕዝቡን በተለያየ ምክንያት ማሰቃየቱ ሳያንሰው የራሱ ታማኝ የሆኑ ቅጥረኞቹ ላይ እምነት በማጣት የሚያደርገውም የጠፋበት መሆኑ ግልፅ እየሆነ መምጣቱን አመላካች እንደሆነ የዚሁ ችግር ሰለባ ልንሆን እንችላለን ያሉ ወገኖች ጠቁመዋል። በይበልጥ አማራዉን በማይወክሉት የወያኔ አገልጋዮች እየተሰቃየው ያለው ሕዝቡ ሲሆን ፣ እነሱም ሕዝቡ ከጎናችው አለመኖሩን በመረዳታቸው የተፈጠረው ክፍተት በፈጠረባቸው ጭንቀት የመንግስት ሠራተኛውንም ሆነ ነጋዴውን ማመሱን እንደቀጠሉበት ለማወቅ ተችሏል።” በማለት ዘግቧል:፡

የአርበኞች ግንባር ሰራዊት በመተማ አካባቢ አደረስኩት ስላለው ጥቃት ከመንግስት በኩል የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ መረጃ የለም።

No comments: