Monday, January 20, 2014

“የአፄ ምኒልክ ወታደሮች በአያቴ ላይ ብዙ በደል አድርሰዋል” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ቃለምልልስ)

January20/2014

“በኢህአዴግ በኩል የአፄ ምኒልክ ሐውልት ይፍረስ የሚል እንቅስቃሴ አልነበረም”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ቃለምልልስ)

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለ3 አመት የመሩትን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ለኢ/ር ግዛቸው አስረክበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በፓርቲ ፖለቲካ እንደማይታቀፉ ከተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር በፓርቲ ቆይታቸው፤ በቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው፣ በአፄ ምኒልክ፣ በደቡብ ሱዳን በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ዙሪያ ከ“ሎሚ” መፅሔት ም/አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡




ሎሚ፡- ያለፉት 3 ዓመታት የአንድነት ፓርቲ ቆይታዎ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከጤንነትም ከቴክኒክ ሁኔታ (ለምሳሌ መኪና የለኝም)፤ ከዚህ ከዚህ አኳያ የመንቀሳቀስ ብቃቴ የተገደበ ነበር፡፡ ይሔ መገደቡ ደግሞ ለፓርቲው አይጠቅምም፡፡ ብዙ መሠራት ያለበትን ነገር ያለመስራት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ በኩል እኔ ስመረጥ በስራው ላይ እኔ የፈተንኳቸውን ሰዎች አይደለም በካቢኔው ውስጥ ያስገባሁት፡፡ በተለያዩ ሠዎች ሃሣብና አስተያየት ይሄ ይሻልሃል በሚል ነው የመረጥኳቸው፡፡ ካቢኔውን የሚያቋቁመው ሊቀመንበሩ ነው፡፡ በዛ መሠረት ነው ያቋቋምኩት፡፡ ወደ ስራ ከገባን በኋላ ስትፈትናቸው፣ ስታያቸው አንዳንድ ወደ ፅንፍ የሚሄዱ አብረን መስራት ያልቻልናቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ በተግባርም ላይ ሌሎችም ድክመቶች ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ ሙሉ ጊዜያቸውን ያለመስጠት ፍላጐት ሣይሆን ስራ ስላለባቸው ነው፡፡ የራሳቸውን ስራ እየሠሩ ኑሯቸውን እየኖሩ በትርፍ ጊዜያቸው መጥተው ነው የድርጅቱን ስራ የሚሠሩት፡፡ ማስገደድ አትችልም፤ ስለዚህ ማስገደድ በማትችልበት ሁኔታ ብዙ ለመስራት ያስቸግራል፡፡ ይህ ደግሞ በስራ አስፈፃሚው ላይ ድክመት እንዲታይ አድርጓል፡፡

ሌላው ደግሞ የግል አመራርና የጋራ አመራር የሚባል ነገር አለ፡፡ እኛ በጋራ አመራር ላይ ነው የተመሰረትነው፡፡ በአንድ በኩል ለሊቀመንበሩ ስልጣን ይሰጣል፤ በሌላ በኩል የጋራ አመራር በሚባልበት ጊዜ ስራ አስፈፃሚው መግባባት አለበት፡፡ በአቋምም የጋራ አመራር ስለሆነ አመራር ሲሰጥ የአቋም መለያየት ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ መካከል አብሮ በትክክል ያለመስራት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህ፣ እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም በሌላ በኩል ጥሩ ነው፡፡ ድርጅቱ ሣይከፋፈል መቆየቱ እንደገና ደግሞ ሁሉንም ያሰብናቸውን ነገሮች ባናከናውንም፤ አንዳንድ ስራዎች ተሠርተዋል፡፡ በህዝብ ግንኙነት በኩል ውይይቶች መካሄድ፣ እንደገና የሚሊየኖች ድምፅ ለነፃነት የሚለውን ሠላማዊ ሠልፍ ማከናወንን የመሳሰሉ፣ በተጨማሪም ምንም እንኳን ችግር ቢኖርበትም በ34 አካባቢዎች በቅርንጫፍ ቢሯችን መስራት የምንችለውን ሰርተናል፡፡ እነዚህ እነዚህ ጥሩ ነበሩ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ከሁሉም አባላት ጋር ከስራ አስፈፃሚ፣ ከብሄራዊ ምክር ቤት ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ያለፉት ሶስት አመታትም ይሄን ይመስላል፡፡

ሎሚ፡- ጊዜዎት ደርሶ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ለቀዋል፤ ከፖለቲካው ለመራቅ መወሰንዎም እየተነገረ ነው፤ ይሄ ነገር ምን ያህል እውነት ነው? 
እንዴት እዚህ ውሳኔ ላይ ደረሱ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አንደኛው እውነት በፓርቲ አመራር ውስጥ አልገባሁም፤ ይሔ ተርሜ (የሊቀመንበርነት ጊዜዬ) ስላለቀ የወሰንኩት አይደለም፡፡ ብዙ ሠዎች ለምን አትቀጥልበትም ብለው ጠይቀውኛል፡፡ ብቀጥል ደስ ይላቸው ነበር፡፡ ከአራት ወር በፊት ተግባራዊ ያደረግነው አካሄድ አለ፡፡ ለሊቀመንበርነት፣ ለብሄራዊ ምክር ቤት ለመወዳደር የሚፈልጉ ሠዎች ማመልከቻ አቅርቡ ተብሎ መስፈርቶች ተዘጋጅተው በዛ መሠረት ማመልከት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ እኔ ግን ለሊቀመንበርነትም ሆነ ለብሄራዊ ምክር ቤት ማመልከቻ ለማቅረብ አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም በአመራር ቦታ ላይ ለመስራትም ሆነ ለመቀጠል ስላልፈለኩ ነው፡፡ ሁለተኛው አንተ እንዳልከው ከፖለቲካ መራቅ ሣይሆን የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኜ ለዛ ወገንተኛ ሆኜ በዛ ፕሮግራም፣ በዛ ህገ ደንብ ተገዝቼ እቀጥላለሁ እንጂ የአመራር ፖለቲካ እንቅስቃሴ አቆምኩ ማለት ነው እንጂ ፖለቲካውን ከነጭራሹ ለቀኩ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሠዎች የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ካልሆንክ፣ ፖለቲካ ውስጥ የለህም ብለው ያስባሉ፡፡ ሠው እስከሆንክ ድረስ ፖለቲካ ነው የምትሠራው፡፡ ዝም ማለትም ፖለቲካ ነው፤ ገለልተኛ መሆንም ፖለቲካ ነው፡፡ እኔ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ማለቴ ነው እንጂ ከፖለቲካ እርቃለሁ ማለት አይደለም፡፡ ከፖለቲካ የማልርቅበት ምክንያት ደግሞ የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ አሁን ካንተ ጋር ስነጋገር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ የፖለቲካ አስተያየት ነው የምሠጠው፡፡ ገለፃ ማድረግ አለ፤ አርቲክሎች መፃፍ አለ፤ መፅሐፍ ማሣተም አለ፤ ምክር የመስጠት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ወጣሁ ማለት አይደለም፡፡

ሎሚ፡- ከሠሞኑ አፄ ምኒልክን የተመለከቱ ፅሁፎች በተለያየ መገናኛ ብዙኃን እየተንፀባረቁ ነው፤ የገዢው ፓርቲ ብሎገሮች ይህንን በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ፤ መነሻው ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የአፄ ምኒልክ 100ኛ የሙት አመታቸው ሲከበር እርሳቸውን ደግፈው የሠሯቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች የሚያጎሉ ጽሑፎችን ነው ያነበብኩት እንጂ በተቃራኒው መጥፎ ስራቸውን በሚመለከት የተፃፈ ነገር አልተመለከትኩም፡፡

ሎሚ፡- አይ እኔ የጠየቅኩት በብሎገሮች ላይ የወጡትን ነው፤..

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ ብሎገሮችን አላነበብኩም፡፡ ሆኖም ግን የማያቸው ሚዲያዎች የእርሳቸውን ጥሩ ጥሩ ጐን ብቻ አጉልተው የፃፉ ናቸው፡፡ የፖለቲካ አቋማቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ አቋም ያላቸው ደግሞ የተደረጉ ጥፋቶች አሉ፡፡ የተሠሩ ስህተቶች አሉ፡፡ እነርሱ ጐልተው አልታዩም፤ የአንድ ወገን አስተያየት ብቻ ነው ያየሁት፡፡ ሁለቱንም ሚዛናዊ ያደረገና ያመጣጠነ መጥፎ ተሰርቶ ከሆነ መጥፎ፣ ጥሩውም በጥሩ ታይቶ መሠራት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ሎሚ፡- ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላይ በወጣ ሠሞን የተጀመረው “የምኒልክ ኃውልት ይፍረስ” ተቃውሞ አሁንም የቀጠለ ይመስላል፤ ገዢው ፓርቲ አፄ ምኒልክን በተመለከተ ያለውን አቋም እንዴት ይገልፁታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ያን ጊዜም ሆነ አሁንም በኢህአዴግ በኩል የምኒልክ ኃውልት ይፍረስ የሚል እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ አሁንም ያለ አይመስለኝም፤ ከየት እንዳመጣችሁ አላውቅም፡፡ ይሄንን ነው የማስታውሰው፡፡

ሎሚ፡- በዛን ሠሞን በገዢው ፓርቲ አማካይነት ሠልፍ የወጣ አልነበረም ነው የሚሉት?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ኦህዴድ ለምሣሌ አንስቶ ነበር፡፡

ሎሚ፡- እርስዎ ኦህዴድ ነበሩ፤ ተሰልፈው ወጥተዋል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ! ወጥቻለሁ፡፡

ሎሚ፡- ኦህዴድ የኢህአዴግ አጋር ድርጅት ነው፤ የኦህዴድ አቋም በኢህአዴግ ሊንፀባረቅ አይችልም ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ቢንፀባረቅ ኖሮ ያን ጊዜ ይነሣ ነበራ፡፡ እነ አቶ ተፈራ ዋልዋ ከንቲባ ነበሩ፤ የዛን ጊዜ ኦህዴድ ጫና ቢፈጥር በእርሳቸው ላይ ይንፀባረቅ ነበር፤ በኢህአዴግም ላይ ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ኢህአዴግ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ኃውልት አንስቷል፤ የሌኒንን አንስቷል፡፡ እንጂ የምኒልክን ለማንሣት የተደረገ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ኦህዴድ ደግሞ ተፅዕኖ ቢያሳድር ኖሮ እናይ ነበር፤ አላደረገውም፡፡

ሎሚ፡- እርሶ በግል አፄ ምኒልክን እንዴት ይገልፁቸዋል? ንጉስ ነገስቱ በሃገር ውስጥ ፈፅመውታል የሚባለው መጥፎና መልካም ጐናቸውን ቢጠቅሱልን? የአሁኑዋን ኢትዮጵያ በመፍጠሩ ረገድ የነበራቸውን ሚና እንዴት ይገልፁታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ቀደም ብዬ ገልጬዋለሁ፤ በግል ከነጋሶ ታሪክ ነው የምነሣው፡፡ የአፄ ምኒልክ ወታደሮች መጥተው አያቴን በሠንሠለት አስረው እህል አስፈጭተዋቸዋል፡፡ እንዳያመልጡ ተብሎ ይህ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ሌላ ለ6 ሠዓት ያህል ረጅም መንገድ እህል አሸክመው ወስደዋቸዋል፡፡ እና ይህንን ለመርሳት አልችልም፡፡ የተገደሉ ሠዎች አሉ፤ በባርነት የተሸጡ ሠዎች አሉ፡፡ አስገድዶ የማስገበር ሁኔታም ነበር፡፡ የሆነውንና የተፈፀመውን ጥፋት መርሣት አይቻልም፡፡ ይሔ እንዳለ ሆኖ የተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ሚዛኑ ይሄ ይደፋል፡፡ “ይደፋል” የሚባል ነገር ውስጥ ሳንገባ፡፡ ለምሣሌ ዘመናዊ ነገሮችን ወደ ሃገሪቱ የማስገባት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በነዚህ ላይ ብቻ አተኩሮ ሌላውን መርሳት አንችልም፡፡ ያኔ ያጡትን የራስን መብት በራስ የመወሰን መብት ያጡ ህዝብች አሁንም መብታቸው አልተከበረም፡፡ እስካሁን ድረስ የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ በዚህ ምክንያት አገርን አንድ አደረጉ፣ የኢትዮጵያን ነፃነት አስጠበቁ፤ ምናምን የሚል ነገር አለ፡፡ ግን ደግሞ መጥፎውንም መርሣት የለብንም፡፡

ሎሚ፡- ምኒልክ በኦሮሞ ተወላጅ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጉዳት አድርሰዋል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ አላልኩም፤ ለምን እንደዚህ እንደሚባልም፣ ለምን እንደዚህ ብለህ እንደምትጠይቀኝም አላውቅም፡፡ በአንድ በኩል የደቡብ አካባቢን ካየህ ከኡጋዴን እስከ ቤንሻንጉል ድረስ፤ ከቦረና እስከ ሠሜን ሸዋ ድረስ በምኒልክ ተበድሏል፡፡ ስለዚህ ይሄ ጉዳይ በኦሮሞ ብሔር ላይ ብቻ የደረሰ በደል አይደለም፡፡

ሎሚ፡- የአፄ ምኒልክም ሆነ የቀረው የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን ልዩነት በመዘላለፍ ከመግለፅ ይልቅ በሰለጠነ አካሄድ እና በሰከነ ሁኔታ ለመነጋገር ምን መደረግ ይኖርበታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ምኑ ነው ስልጡኑ? እውነት መናገሩ ነው ስልጡን አለመሆኑ? መጥፎም የሚናገር አለ፤ ጥሩም የሚናገር አለ፡፡ ስልጡን የሚሆነው መደማመጡ ነው፡፡ ማንም ሠው የፈለገውን ይናገር፤ የፈለገው ደግሞ ይስማ፡፡ ሁሉም ሠምቶ በጠላትነት ባይተያይ ጥሩ ነው፤ እርሱ ነው ዋናው ቁም ነገሩ፡፡

ሎሚ፡- የሕወሓት ነባር ታጋይ የሆኑት አቶ ብስራት አማረ “ፍኖተ ገድል” በተሰኘው መፅሃፋቸው “የምኒልክ የስልጣን ጥማት ለትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ የነበረውን ከባድ ጥላቻ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ እንዳመራ ይታመናል” ይላል፤ እርሶ ይሄን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አላነበብኩትም፤ አንደኛ እርሱ የግሉ አቋም ነው፡፡ የእኔ አቋም ግን ቀድሞ የገልፅኳቸው ናቸው፡፡

ሎሚ፡- ሠማያዊ ፓርቲ በአፄ ምኒልክ 100ኛ አመት የሙት ዝክር ዝግጅት ወቅት የክብር እንግዳ የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም “አፄ ምኒልክ ከአሁን በኋላ ታላቁ አፄ ምኒልክ” ተብለው እንዲጠሩ ሃሣብ አቅርበዋል፤ ይሄን እንዴት አዩት?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የራሳቸው አመለካከት ነው፤ ሌላው ደግሞ እንደዛ ላይል ይችላል፤ በአንድነት የሻማ ምሽት ላይ የቀበና አደባባይ የአንዱዓለም አደባባይ እንዲሆን ሲሉ ሠምቻቸዋለሁ፤ ይሄ የራሳቸው አመለካከት ነው፡፡

ሎሚ፡- ገዢው ፓርቲ ያለበትን የችግር አቅጣጫ ለማስቀየር ይህን ጉዳይ ተጠቅሞበታል የሚሉ አስተያየቶች አሉ፤
ዶ/ር ነጋሶ፡- በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተከታተልኩት ወይም ትኩረት የሰጠሁት ነገር የለም፤ ኢህአዴግ አደረገ ወይም አላደረገም ለማለት መከታተል አለብኝ፡፡

ሎሚ፡- ባለፈው የመፅሔታችን ዕትም አቶ በቀለ ድሪባ ካባ የተባሉ የቀድሞ የፓርላማ አባል “የምኒልክን ስህተቶች” ከዘረዘሩ በኋላ እንደ ራስ ጐበና ደጩ የመሠሉ የምኒልክ ባለሟሎች “የምንሸማቀቅበት ታሪክ አጉዳፊ ግለሰብ ናቸው” ብለዋል፡፡ ይህን መሠሉ አቋም ምን ያህል የኦሮሞ ተወላጆችን አቋም ይወክላል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ይሔንን ቅድም ካልኳቸው ጉዳዮች ጋር ልታስታርቅ ወይም ልዩነታችንን ልታስተውል ትችላለህ፡፡ ሁሉም ኦሮሞ እንደ እኔ ያስባል ወይስ እንደሳቸው የሚለውን ለመደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሎሚ፡- ቴዲ አፍሮ ከሠሞኑ ለአፄ ሚኒልክ አድናቆቱን ገልጽዋል፤ ለኮንሠርቱ ስፖንሰር የሆነውን በደሌ ቢራ ላለመጠጣት አድማ እንዲደረግ ጥያቄ ቀርቧል፤ የደቹ ሄኒከን በትዊተርና ፌስቡክ ከ18ሺህ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች “ምኒልክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችን” የጨፈጨፉ ኢትዮጵያዊ ሂትለር ናቸው” የሚል የተቃውሞ መልዕክት እንደደረሰው ገልጿል፡፡ አፄ ምኒልክን ኢትዮጵያዊ ሂትለር የሚለው ቃል ይመጥናቸዋል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በዛን ጊዜ በነበረው ሁኔታ ምክንያት አፄ ምኒልክ ላይ ስሞታ የሚያነሱ ሠዎች አሉ፡፡ የሚደግፏቸውም አሉ፤ የሁሉም መብት ነው፤ ከሂትለር ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? በምን ዓይነት መንገድ? በኢኮኖሚው ነው? የዛኔ የኢኮኖሚ ኢንዳስትሪ አልነበረም፤ ፋሽስት ነበር፤ ፋሺዝም ደግሞ የሚመጣው ከኢንዱስትሪው ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ አፄ ምኒሊክ ፊውዳል ነበሩ፤ ታዲያ እንዴት አድርገህ ነው ከናዚ መሪ ጋር የምታመሳስላቸው?'

ሎሚ፡- ምኒልክን የሚመለከቷቸው እንደ “ተበዳይ ተበዳይ ባይ ነኝ ሰው” ነው? ወይስ እንደ ሆደ ሰፊ ፖለቲከኛ?'
ዶ/ር ነጋሶ፡- ኦሮሞ ስለሆንኩ ነው እንደዚህ የምጠየቀው? ትኩረት ያልሠጠሁትን ጉዳይ ለምን ትኩረት እንድሰጠው ይደረጋል?

ሎሚ፡- ለወደፊቷ የጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ ጉዳዮችን ለማስታረቅና ለመቀየር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አሁን ካነሣሃቸው አንደኛውን እና የፈለከውን ልታሳካ ትችላለህ፤ እኔም የፈለኩትን ሃሣብ ላነሣና ልከተል እችላለሁ፡፡ እኔ መብትህን እንደማከብርልህ አንተም መብቴን ታከብርልኛለህ፡፡ ሰብዓዊ መብትን፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር እንደገና የህዝቦች የራሳቸውን መብት በራሳቸው እንዲወስኑ መፍቀድ ሲቻል ነው ኢትዮጵያ በሰላም ልትኖር የምትችለው፡፡

ሎሚ፡- አንድነት በወጣት ፖለቲከኞች ያምናል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ!

ሎሚ፡- በወጣት የሚያምን ከሆነ የአመራር ቦታዎችን ለወጣቶች ለምን ለመስጠት አልፈለገም? ወይም ሙከራውን አላሣየም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እንዴት?

ሎሚ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በወጣት የሚያምን ከሆነ የኢ/ር ግዛቸው ወደ አመራር መምጣት እንዴት ተፈጠረ?'

ዶ/ር ነጋሶ፡- የእኛ አሠራር ይሔ ወጣት ነውና ይህንን ቦታ ይያዝ፤ ይሄ ይሻላልና ይሄ ዞር ይበል አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ሠዎቹ ታውቀው “እችላለሁ እመራለሁ” ብለው ማመልከቻ ካቀረቡ በኋላ በማመልከቻው መሠረት መስፈርት ተቀምጦ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሠዎች፣ ለምርጫ ይቀርባሉ፡፡ በዚህ መሠረት ነው የተመራው፡፡ ለምሣሌ የብሔራዊ ም/ቤት ምርጫ በቀደም ተካሂዶ ነበር፡፡ 65 ሠዎች ናቸው ተለዋጭና ሙሉ አባል የሆኑት፡፡ ከ50 አመት በታች የሆኑ ሠዎች ምን ያህል ናቸው ብለህ ትገምታለህ?

ሎሚ፡- አላውቅም፤ ይቅርታ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከ65 ተለዋጭና ሙሉ አባላት 47ቱ ከ50 አመት በታች ናቸው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ባለበት መልኩ እንዴት ወጣቶች አልተካተቱም ይባላል? ሁለተኛ በፕሬዚዳንቶች ምርጫ ወጣቶችን ጨምሮ ኢ/ር ግዛቸውን ነው የመረጡት፡፡ ለምን ግዛቸውን መረጡ ነው? (ሣቅ…) ከ50 አመት በታች የሆኑት ተክሌና ግርማ ተወዳድረው ነበር፡፡ ቤቱ አልመረጣቸውም፡፡ እናስ ይሄ ቤቱ ወጣቶችን አይፈልግም ለማለት ነው? በነገራችን ላይ ሁለቱም ከ50 በታች ናቸው፡፡ እንደገና ደግሞ አሁን የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ከተመረጥኩኝ 65 ፐርሰንቱን የስራ አስፈፃሚ ወጣቶች አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣት ሊቀመንበር ተወዳድሮ ስላልተመረጠ ድርጅቱ ወጣቱን አይፈልግም ብሎ ማሠብ ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ነው፡፡ ፓርቲው ወጣቶችን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊትም ነበሩ፤ ነጋሶ ወደ 70 አመት ተጠግቶ በሊቀመንበርነት ስላገለገለ ይሄ ወጣቶችን አይፈልግም ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡

ሎሚ፡- ፓርቲው ቀጣዩን የ2007 ዓ.ም ምርጫን እንዴት ያየዋል? ሠልፎች፣ ስብሰባዎች እክል ይገጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል፤ ከዚህ አንፃር ምርጫውን እንዴት ያስቡታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከፓርቲው አመራር ለቅቂያለሁ፤ ሊቀመንበሩ አዲስ ናቸው፤ ስራ አስፈፃሚው የሚወስነውንና ያላቸውን አቋም አናውቅም፡፡
ሎሚ፡- የአቶ ስዬ አብርሃ ጉዳይ ግልፅ አይደለም፤ ፓርቲውን ለቀዋል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እስካሁን በፅሁፍ ያስታወቁት ነገር የለም፡፡

ሎሚ፡- በዚህ ዓይነት ርቀትና ምንም እንቅስቃሴ በማያደርጉበት ሁኔታ ከፓርቲው ጋር መስራት ይቻላል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በግል የማውቀው የሚሠሩበት ስራ የፖለቲካ አባል እንዲሆኑ የሚፈቅድላቸው አይደለም፡፡ በምን መልኩ ፓርቲውን ይረዳሉ? ምን ዓይነት ግንኙነት አላቸው? የሚለውን ውስጥ ገብቼ ለመግለፅ አልችልም፡፡ ዋናው ነገር ግን በፅሁፍ እኔ ከፓርቲው ለቀቅቄያለሁ ብለው የፃፉት ነገር የለም፡፡

ሎሚ፡- ደቡብ ሱዳን ከአንድ አመት በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ሁከት ገብታለች፡፡ የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ እንዴት ተመለከቱት? የሃገሪቱ ጉዳይስ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ጫና ምንድነው? ምንስ መደረግ ይኖርበታል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ደቡብ ሱዳንና ጐረቤት ሃገሮች ውስጥ እንዲህ ያለ ችግር በሚነሣበት ጊዜ ችግሮቹ የሚዛመቱት ወደ ጐረቤት ሀገሮች ነው፡፡ የስደተኞች ጉዳይ አለ፡፡ ያም ብቻ አይደለም፤ ኑዌር ለምሣሌ ደቡብ ሱዳንም አለ፤ ኢትዮጵያም አለ፡፡
ችግር በሚነሣበት ጊዜ ሸሽተው ወደዚህ ሊመጡ የሚችሉ ሊኖሩ ይችላል፡፡ ስደተኝነት ብቻ ሣይሆን ያም ምን ዓይነት ችግር ሊያስነሣ እንደሚችል አናውቅም፡፡ በአካባቢያችን ሠላምና ፀጥታ ከሌለ እኛም ሠላምና ፀጥታ ማግኘት አንችልም ማለት ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሦስት ሣምንት በላይ ሆኖታል፡፡ እንደማይቀጥል ተስፋ አለኝ፤ ከስምምነት ላይም እንደሚደርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሎሚ፡- የኢትዮ-ኤርትራ ፍጥጫ አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ለውጦች የሉም፤ 15 አመት ተቆጥረዋል፤ መጨረሻው ምን ይሆን?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በሪፖርቴ ላይ የገለፅኩት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በጦርነትና በሠላም መሃል ነው ያለው፡፡ ወደ ጦርነት ተገብቶ አንዱ ወገን አሸንፎ ተሸናፊው ተቀብሎት እርቅ ወርዶ አግባብ ያለው የመንግስታት ግንኙነት ተፈጥሮ አልተስካከለም፡፡ በዚህ መቀጠሉ ጥሩ አይደለም፤ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲህ ነው ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል፡፡

ሎሚ፡- በኢትዮጵያ ላይ በኢኮኖሚ ዙሪያ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በፍጥጫ ላይ የመቆየቱ ጉዳይ ሣይሆን ወደብ የለንም፤ በአሰብ ምክንያት ብዙ ገንዘብ እናወጣለን፡፡ ይሔ ብዙ የኢኮኖሚ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ይሔ ነገር አንድ እልባት ቢያገኝ ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሎሚ፡- ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና አካባቢው ያላትን የበላይነት አጥታለች የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ከኢትዮጵያ ይልቅ የዩጋንዳ ተፅዕኖ ፈጣሪነት መስፋቱ ይነገራል፤ ይሄን እንዴት ታዘቡት?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በእውነት አልገባኝም፤ በምንድነው ተፅዕኖ የፈጠረው?

ሎሚ፡- ጥሩ ምሣሌ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ወገኖች በስልጣን ላይ ያለው እና ለጉዳዩ ቅርብ የሆነው ፓርቲ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ዙሪያ ማድረግ የሚገባውን ያህል አላደረገም ይላሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ምን ማድረግ ነበረባት ኢትዮጵያ?

ሎሚ፡- ዩጋንዳ የበላይ ሆኖ ለአንድ ወገን በማገዝ የወሠዳቸው እርምጃዎች ነበሩ፤

ዶ/ር ነጋሶ፡- ይሄ ነገር የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ከዚህ በፊት በሶማሊያ ጣልቃ በመግባታችን ብዙ ችግር ተፈጥሯል፤ አሁንም እየተፈጠረ ነው፤ ለወደፊትም ብዙ ችግር ያስከትላል፤ እንደዛ ለምን አልገባችም ነው ኢትዮጵያ?

ሎሚ፡- እንደዛ አይደለም ዶክተር፤ ለምሣሌ ዩጋንዳ ጣልቃ የገባችባቸው ሱዳን ላይ ሊሆኑ የማይገባቸው ነገሮች መደረጉ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ያሉ ኑዌሮች አሉ፤ ዩጋንዳ ለሳልቫኪር በመደገፍ የአየር ጥቃት ማድረሱ ይነገራል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለምን ሆኑ ብላ ማጣራት አልነበረባትም ወይ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እያደረገች አይደል አሁን?

ሎሚ፡- በተወሰነ መልኩ የማርፈድ ሁኔታዎች አለባት፤

ዶ/ር ነጋሶ፡- እንዴት ማርፈድ?

ሎሚ፡- ለምሣሌ ኬኒያ ላይ የተደረገው ድርድር የኢጋድ ሣይሆን የዩጋንዳ ሃሣብ የተተገበረበት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ አላውቅም፤ ይሄ በኢጋድ ተዘጋጅቶ ነው የተከናወነው፡፡ ስህተት ተሰርቷል ወይስ አልተሠራም? ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢጋድን ወክላ ነው እየሠራች ያለችው ነው የሚባለው? እንደዛ ከሆነ አላውቅም፡፡

ሎሚ፡- የሃገሪቱን ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ኢኮኖሚካሊ ሙስና ሠፍኗል፤ መንግስት ራሱ የመንግስት ሌቦች የበዛበት ነው ብሎ ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል ድህነት አለ፤ እየሠፋ ነው፡፡ በፖለቲካው መታፈን አለ፤ ነፃነት የለም፤ ከድህነቷ በመነሣት ደግሞ የማህበራዊ ችግሮች አሉ፡፡

ሎሚ፡- ለነዚህ ሁሉ ጉዳዮች መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ኢህአዴግ ራሱ በሩን ክፍት ማድረግ አለበት፤ የዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡

ሎሚ፡- ዶክተር በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

No comments: