Monday, January 20, 2014

ግብጾች አንድ ሲሆኑ ኢትዮጵያዉያን በአባይ አንድ መሆን እንዳለባቸው አቶ ግርማ ሰይፉ ገለጹ (አቡጊዳ)

January20/2014
በሱዳን፣ ግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረዉ የሶስትዮች ንግግር መበተኑን አስመልክቶ ፣ የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት እንዲሁም የፓርላማ አባል፣ የግብጽን አቋም «የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ» እንደሆነ በመግልጽ፣ መንግስት የወሰደዉን አቋም ደገፉ።
በአባይ ግድብ ዙሪያ እንኳን የተቀረዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፓርላማ አባል የሆኑት እርሳቸዉም በቂ መረጃ እንደሌላቸዉ የገለጹት አቶ ግርማ፣ «የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ከዚህ አንፃር በጭፍን የአባይን ግድብ እንዲደግፉ እንጂ መረጃን መሰረት አድርገው ትንተና እንዲሰሩ እና የራሳቸውን ምክረ ሃሳብ እንዲሰጡ እድል የላቸውም፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚፈለጉት ልማታዊ የሚባሉት ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው እነርሱም መንግሰት የሚለውን እንደ በቀቀን መድገም ነው የሚጠበቅባቸው፡» ሲሉ በመንግስት ሜዲያዎች የሚነዙ ፕሮፖጋንዳዎችን አማረዋል።
የሰባአዊ መብት ከተከበረ፣ በአባይ ፕሮጀክት ዙሪያ የተሸፋፈነዉን የተደባበቀ ገሃድ ወጥቶ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ከተዘረጋ፣ ግብጾችን ከመለማመጥ በዉጭ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ግድቡን ሊገነቡት እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ግርማ አገዛዙ በዉጭ ያሉት ለማቀፍ እምሰረታዊ ለዎጦች እንዲያደርግ አሳሰበዉል።
«በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህን ግድብ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሊገነቡት የሚችሉበት አቅም እንዳለ ተገንዝቦ ግብፅን አንገት የሚያስደፋ መንገድ ከመቀየስ ይልቅ አሁንም በውጭ የሚገኙትን ዜጎች መከፋፈል ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለኝ» ሲሉ ነበር አቶ ግርማ የጻፉት።
«የመንግሰት ሹማምንት የአባይ ግድብን ያህል ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው ተቃዋሚና ገዢ ፓርቲ የሚል ክፍተት መፍጠር እንደሌለባቸው ሲነገራቸው፣ በተግባር የሚሰሩትን ሀቅ ወደ ጎን ትተው ጉዳዩን በሙሉ ፕሮፓጋንዳ ያደርጉታል» ያሉት አቶ ግርማ፣ የኢሕአዴግን አግላይ ተቃዋሚዎችን የመግፋት ኃላ ቀር ባህሪን ለማሳየት ሞክረዋል።
«ግብፆች የአባይ ጉዳይ ሲነሳ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ትተው እንደ ግብፅ ሲያስቡ እኛን መለያየት ለምን ያስፈልጋል? የአባይ ግድብ ፕሮጀክት በተግባር የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮጅክት አንዲሆን የፖለቲካ ድባቡ ላይ ያጠላው የፕሮፓጋንዳ አዚም ሊገፈፍ ይገባል፡፡ አንድነት ፓርቲ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን መጠቀም ተፍጥሯዊ መብቷ ነው ይላል፡፡ ይህ የማይገሰስ መብት ላይ ምን ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል ? የዛሬው መልዕክቴ ዋና ማጠንጠኛ በሀገር ጉዳይ እንዳንግባባ አዚም ያደረገብን ማን ነው? የዚህ አዚም መፍቻ ቁልፍ መተማመን እና ሀገራዊ ዕርቅ ይመስለኛል» ሲሉም በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲክ ልዩነቶች ሳይኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአንድ ላይ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

No comments: