Wednesday, January 22, 2014

አዲሱ የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሹመት በግል ጋዜጦች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ አመላካች ነው ተባለ

January21/2014

ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት የቀድሞ የህወሃት ታጋይ አቶ ዘርዓይ አስገዶምየኢትዮጵኢያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን መሾማቸው መንግስት ከምርጫ 2007 በፊት በፕሬሱ ላይ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ጠንካራ አስፈጻሚ በማስፈለጉ ሊሆን እንደሚችል ኢቲቪን የለቀቁ አንዳንድ ጋዜጠኞች ተናገሩ።


የአቶ ዘርዓይ ከቴሌቪዥን ዳይሬክተርነት መነሳት በአቶ በረከት ስምኦን ምትክ የድርጅቱ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ከወራት በፊት ከተሾሙት አቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር አንዳንድ ወገኞች እያገናኙት መሆኑ ስህሀት ነው ይላሉ ጋዜጠኞቹ።  በተለይ በቀጣዩ አንድ ዓመት በአስተዳደራዊ መልኩ ከሕትመት እንዲወጡ ለማድረግ የታሰቡ ጋዜጦችና መጽሄቶችን ጉዳይ ለማሳካት ቁርጠኝነት እንዳላቸው በመገመት አቶ ዘርአይ መሾማቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ዘርዓይ በባህርያቸው ግትርና አምባገነን መሆናቸውን ያስታወሱት ጋዜጠኞች፣ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በዴሞክራሲ ተቋማት ጉዳይ ላይ ያደረጉት ውይይት ከዕውቅናየ ውጪ እንዲቆራረጥ ተደርጓል በሚል በአንድ የግል ጋዜጣ ተቃውሞ ያቀረበውን አንድ ጋዜጠኛ ያለምንም ማንገራገር ከድርጅቱ እንዲሰናበት ማድረጋቸው የአምባገነንነታቸው አንድ መገለጫ ነው ሲሉ ጋዜጠኞቹ ያወሳሉ።

የኢቴቪ ባልደረባ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ ለአዲስ አበባው ዘጋቢ እንደተናገረው አቶ ዘርዓይን እንደዋና ስራ አስኪያጅ በቀላሉአግኝቶ ማነጋገር፣ችግርን ማስረዳት ለሰራተኞች እንኩዋን የሚቻል አለመሆኑን በመጥቀስ ወደእሳቸው ቢሮ ከመግባትጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መግባት ይቀል ነበር ብሎአል፡፡

በእሳቸው አመራር ዘመን በድርጅቱ ጋዜጠኞችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ሳይቀር የኪራይሰብሳቢነት ዝንባሌ ገዝፎ መታየቱን፣ በተለይ የእሳቸው ተከታይ የሆኑ  ጋዜጠኞች ቢያጠፉ እንኩዋን አይቶ ዝም ከማለት ያለፈ እርምጃ አይወስዱም ነበር ብለዋል፡፡
አቶ በረከት ስምኦን የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ዓመታት ከአቶ ዘርዓይ ጋር መግባባት እንዳልነበራቸውና ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አቶ ዘርዓይ ታዛዥነታቸው ከማንም ይልቅ ለህወሃት ሰዎች ብቻ በመሆኑ ነው ሲሉ ጋዜጠኞች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አቶ በረከት አዛዡን ማንሳትም፣ መቃወምም ተቸግረው መቆየታቸውን ጋዜጠኛው ተናግሯል።

የአቶ ደስታው ከብሮድካስት ባለስልጣን ዳሬክተርነት ሲነሱ ምናልባት በራሱ የሚተማመን ፣ሕግና ስርዓትን ብቻ አክብሮ የሚሰራ ተሹዋሚ ሊመጣ ይችላል የሚለውን ጭላንጭል ተስፋ የአቶ ዘርዓይ ሹመት እንደሻረው ጋዜጠኛው አክሎ ተናግሯል።

No comments: