Tuesday, January 28, 2014

በልቡ የሸፈተ ህዝብ የካድሬዎች ጋጋታና ሽብር አይገታውም

January 28, 2014
በዲያስፖራ የአረና ትግራይ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑሰሞኑን በትግራይ የህወሓት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ከየመንደሩ የተውጣጡ ነብሰ ገዳይ፣ ስብሰባ በታኝና አፋኝ የዱሪየ ቡድኖችን በተለያየ መልኩ በማደራጀት በአረና ትግራይ አባላትና አመራር ላይ የከፈቱትን አዲስ የመንጥርና የድብደባ ዘመቻን አስመልክቶ

ህወሓት/ኢሕአዴግ በትረ ስልጣኑን ከተጎናፀፈና ካደላደለ ወዲህ ከሱ የተለየ አመለካከትና ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ የተለያዩ ቀለማ ቀለሞችን በመቅባት፣ የፈጠራ ስም በመለጠፍና ሰበብ አስባብ በመፈለግ በቀጥታም ሆነ በረቀቀ መንገድ የመመንጠር፣ የማፅዳት፣ የመሰወር፣ የማሰር፣ የመግደልና እርስ በርስ የማናቆር ስራ ዋነኛ የስርዓቱን ባህርይ መገለጫ ሆኖ መቆየቱ እሙን ነው። የእርምጃው ዋናው ምክንያትም እውነት ተቃዋሚዎቹ የሀገርና የህዝብ ጠላቶች ስለሆኑ አይደለም። ነገር ግን ጥያቄያቸው “ስለ ሀገራችንና ህዝባችን ጉዳይ እኛም ያገባናል!! አባቶቻችን ደም ከፍለው ያቆዩልንን ሀገር የመጠበቅ የኛም ግዴታ ነው!! ዘላቂ ልማትና ዕድገት የሚመጣው እውነተኛ ዲሞክራሲ፣ የሕግ ልዕልና፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ሰላምና አንድነት ሲረጋገጥ እንጂ በጡንቻ አይደለም!! ሕገ መንግስቱ የሰጠንን የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመንቀሳቀስ፣ የእምነት፣ የመምረጥና የመመረጥ ነፃነታችንን ይከበር!!” ብለው ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን ተከትለው በቆራጥነት ስለተንቀሳቀሱና ስለጠየቁ ብቻ መሆኑን ማንም ቅን ህሊና ያለው ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚችል ጉዳይ ነው።
ሰሞኑን የመድረክ አባል ከሆኑት የፓለቲካ ድርጅቶች አንዱ “በአረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ” አባላትና ከፍተኛ አመራር ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና አፈና ማየቱ በቂ ይመስለናል። የአረና ትግራይ ፈጣን ዕድገትና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሄድ ያስደነጋጣቸው የህወሓት ካድሬዎችና መሪዎቻቸው እንቅስቃሴውን ለመግታት የማይፈንቅሉት ድንጋይና የማይሸርቡት ተንኰል እንደሌለ በተደጋጋሚ አይተናል። ዛሬም እንደለመዱት አዲስ የማጥቃት ስልት በመቀየስ ነብሰ ገዳይ፣ በታኝና አፋኝ የዱሩየዎች ቡድን በተለያየ መልኩ በሕቡእና በግልፅ በማደረጃት በአረና አባላትና መሪዎች ላይ አዲስ የመንጥር ዘመቻና ጥቃት ጀምሯል።
የማጥቃት ዘመቻው ቀደም ብሎ በሽሬ እንዳስላሴ የተጀመረ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ በባሰ መልኩ በአዲ ግራት ከተማና በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት ቀጥሏል። በዚሁ ተከታታይ ዘመቻቸው ያነጣጠሩት አረና ትግራይ የጠራውን ስብሰባ እየተከታተሉ መበተን፣ ህዝቡን ወደ ስብሰባው እንዳይሄድ በተለያዩ ዘዴዎች ማስፈራራትና ማሰናከል፣ በታኝ የዱሩየዎች በዱን በማደራጀት ለመበጥበጥና ለማወክ ያለ የሌለ ሀይላቸውን በማንቀሳቀስ ስብሰባዎችን እንዲቋረጡ አድርጓል።
ጉዳዩን በቅርብ ተከታትለን እንዳረጋገጥነው የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ስብሰባውን መበተኑና መቋረጡ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ለመቀስቀስ በአካባቢው የተሰማሩ በሶስት ከፍተኛ የአረና ትግራይ መሪዎች በአፋኝና በታኝ ቡድን እንዲደበደቡ ማደረጋቸውና ማሰራቸው ነው። የዚሁ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ሰዎች ውስጥ አቶ አስገደ ገብረስላሴ የቀድሞ የህወሓት መስራችና አስልጣኝ የነበሩ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ፣ አቶ ዓንዶም ገብረስላሴ የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ይገኙባቸዋል።
በአንጋፋ ወንድሞቻችን ላይ የደረሰባቸው ኢ ሰብኣዊ ጥቃት እጅጉን ያስቆጣንና ያስገረመን ቢሆንም በኛ እምነት ይህ ሁሉ ግፍና መሰሪ ተግባር በድምር ሲታይ የሚከተሉትን ሓቆችንና ክስቶችን የሚያመላክቱ የስርዓቱን ባህርይ ገላጭ ናቸው ብለን እናምናለን።
1. ህወሓት ታሪክ፣ ባህልና ሕግ የማይገዛው፣ መሰረታዊ እውነታዎችንና ዲሞክራሲያዊ መርሆዎችን የሚፃረርና የህዝቡን ሉዓላዊ ህልውና የሚያፈርስ የጥፋት መንገድ እየተከተለ በመሄድ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ መሆኑን ራሱ በራሱ ጋሃድ እየሆነ መምጣቱ የሚያመላክት ነው።
2. ይህ ዓይነቱ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የሚያሳየን ህወሓት ራሱን ከመንግስትነት ወደ ተራ ዘራፊነትና ማፊያነት በመቀየር የዜጎችን ድህንነት ለመጠበቅ የማይችል ሕገ አልባና የሻገተ ስርዓት መሆኑን ራሱን በራሱ እያስመሰከረ ያለ ድርጅት መሆኑን እንገነዘባለን። አንድ መንግስት በራሱ ህዝብና በገዛ ወገኑ ላይ ነብሰ ገዳይና አፋኝ ቡድንን በማደራጀት ዜጎቹን በአደባባይ ማስደብደብ ማለት የባዕድ ወራሪ እንኳን ያላደረገው ከዚህ የባሰ ጭካኔ፣ ውድቀትና ዝቅጠት አለ ብለን አናምንም።
3. የህወሓት ፀረ ህዝብ ተግባር ለይስሙላ ስለዲሞክራሲና ስለየብዙሃን ፓርቲ ስርዓት ይናገር እንጂ በተግባር በህዝብ ፊት ቀርቦ ለመከራከርና ለመዳኘት አቅምና ሞራል የሌለው፣ በህዝቡ ዘንድ ምን ያህል የተተፋና ጊዜ የጣለው ድርጅት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ህወሓት የትግራይ ህዝብን ነፃነትና ደህንነት ጠባቂ ለመሆን ቀርቶ የነገ የሀገር ተረካቢና ተስፋ የሆነውን ወጣት በነፃነት አየር ተኰትኵቶና የወገንና የሀገሩን ፍቅር ተላብሶ እንዳያድግ ወኔን የሚያኰላሽ ትውልድ ገዳይ ድርጅት መሆኑን ከተግባሩ በላይ ሌላ ምስክር የሚያሻ አይደለም።
4. ህወሓት የትግራይ መንግስት ነኝ ይበል እንጂ ራሱ የፃፈውን ሕገ መንግስት እንኳ ጠንቅቆ የማያውቅ፣ በተግባር የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆዎችን የሚፃረር ስራ የሚሰራ አፍራሽ ድርጅት መሆኑን ራሱን በራሱ እያስመሰከረ ይገኛል። የትግራይ ህዝብ እየተዳደረ ያለው ራሱ ባፀደቀው ሕገ መንግስት መሰረት ሳይሆን ገና በበረሃ የነበረው የደደቢት የካድሬ ሕግ መሆኑን ካለው ተጨባጭ ሁኔታና ከተግባራቸው መረዳት ይቻላል።
5. ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ነኝ በማለት የትግራይ ህዝብ ነብዪ መስሎ ለመቅረብ ይሞክር እንጂ በተግባር ግን የታገለለትን አላማ የሚፃረር ስራ የሚሰራና የህዝቡን ተስፋ እያጨለመ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ራሱ በራሱ እያስመሰከረ ይገኛል።
6. የጥቃቱ መንሲኤ ካድሬዎቹ እንደሚሉት የአረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎቻቸው የህዝብ ጠላት ስለሆኑ፣ ሕግ ስለጣሱ፣ የትምክሕተኞች አመለካከት ስለሚያራምዱ ወይም የደርግ ስርዓትን ዳግም ለመመለስ የሚታገሉ ስለሆኑ አይደለም። አረና ትግራይ ሕገ መንግስቱ የሚጠይቃቸው መመዘኛዎችን አሟልቶ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ድርጅት መሆኑን ይታወቃል። ይሁን እንጂ “አያ ጅቦ ሳታማኸኝ ብላኝ” እንደሚባለው ሁሉ ከጥቃቱ በስተጀርባ ያለው ሚስጢር ግን ባንድ በኩል ገዢው ፓርቲ በሀገር ደረጃ በተለይም በትግራይ ምድር እነሱ የማይቆጣጠሩት ትርጉም ያለው ነፃ የፓለቲካ ድርጅት እንዲፈጠር ፍፁም አይፈልጉም። በሌላ በኩል ደግሞ በትግራይ ህዝብ ላይ ያላቸው ንቀትና ዝቅተኛ ግምት የሚያሳይ ነው። ሕብረተሰቡ በፓለቲካ ድርጅትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነትና ነፃነት፣ የዲሞክረሲ “ሀ ሁ”፣ ሕገ መንግስታዊ መብቱንና ታሪኩን በትንሹ ያውቃል ብለው ቢገምቱት ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ዓይን
ያወጣ አረሜናዊ ተግባር አይፈፁምም ነበር።
የተከበራችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ውድ ኢትዮጵያውያን!!
እኛ በዲያስፓራ የምንኖረው የአረና ትግራይ የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴና መላ የትግራይ ተወላጆች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በየማዕዝናቱ በተለይም በበንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በደቡብና በሌሎች ቦታዎች በወገኖቻችን ላይ የሚፈፀሙ አፈናዎችና እንግልት በቅርብ ስንከታተልና በተለያየ መልኩ ድምፃችንን ስናሰማ ቆይተናል። በቅርቡ በሳውዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የደረሰው ልብ ሰባሪ የሆነ አሳዛኝና አሳፋሪ ዜና ስንሰማም በቁጣ ስሜት በመነሳሳት በያለንበት ከሌሎች ወገኖቻችን ጎን በአደባባይ ቆመን ጭኾናል። አውግዘናልም። ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ እንደተለመደው በትግራይ በወገኖቻችን ላይ እየተካሄደ ያለው ጥቃትም ከዚሁ ተለይቶ የማይታይ ስለሆነ አሁንም የተሰማንን ቁጣና ብሶት ይህንን የጋራ መግለጫ በይፋ እንድናወጣ ተገደናል። ያልታደለች ሀገር ሁሉጊዜ መርዶ ነውና!!
ትግራይ እንደነ አሉላ አባ ነጋና ዮሐንስ የመሳሰሉ የብዙ ጀግኖች ዓፅም የተቀበረባትና አኩሪ ታሪክ ያላት ምድር ብትሆንም ዛሬ ህዝብዋ በአንድ ቤተሰባዊ ቡድን ለሚመራ ፓለቲካዊ ድርጅት በሞኖፓልና በንብረትነት ለማገልገል የተፈጠረ ህዝብ አድርገው በመቁጠር እንደ ህፃን ልጅ አፍህን ያዝ እየተባለ በካድሬ ዱላ እየተኰረኰመ ሲኖር ማየች እጅግ የሚያሳዝን የታሪክ ጠባሳ ነው። ስለሆነም ህወሓት በህዝቡም ሆነ የተለየ አመለካከት ይዘው በሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችን ላይ የሚያካሂደው የስነ ልቦናና የአክል ጥቃት የዲሞክራሲ መርህ የሚፃረር ኢ ሰብኣዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ሕገ ወጥ ተግባር ስለሆነ ድርጊቱን እናወግዛን። እንዲሁም በግፍ የታሰሩ ወገኖቻችን ከእስር እንዲፈቱና በነሱ ላይ ድብደባ ያደረሱ የማፊያና የነብሰ ገዳይ ቡድን አባላትም በአስቸኳ ለፍርድ እንዲቀርቡ አበክረን እንጠይቃለን። በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ዜጎቻችንን ለያይተህ ግዛ በሚል ፈሊጥ በየተራ እንደ ፈለገ እያጠቃን እንዲኖር ምቹ ሁኔታ የፈጠርንለት እኛው ራሳችን በተለያየ ጎራ የየራሳችን ጎጆ አበጅተን በረባም ባልረባም በመነጣጠላችን መሆኑን እሙን ነው። ህዝብ ከተባበረ ምን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል በሌሎች አጋጣሚዎች አይተናል። ስለዚህ በሀገር ቤትም በውጭም የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሀገርና ለወገን ሲባል መለስተኛ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አስነዋሪ ጥቃት በጋራ ልንቆምላቸው ይገባል። በመሆኑም ዛሬ በትግራይ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው በደል ነገ በሌሎች ክልሎችም የሚደርስ ጉዳይ ስለሚሆን ድርጊቱን በጋራ እንድናወግዘው ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ጀግናው ኩሩና ታጋሽ የትግራይ ህዝብም በአካል ይቆጣጠሩት ይሆናል እንጂ የህወሓት ካድሬዎችና መሪዎቻቸው የሚሰሩትን አስቂኝና አሳዛኝ ድራማ ይስቷል ብለን አናምንም። ማን በሙሱና ተነክሮ ጨለማ ለብሶ የሀገርና የህዝብ ሀብት እየዘረፈና ወደ ዉጭ እያሸለከ እንዳለ ማን ደግሞ ለሀገሩና ለወገኑ በፅናት እየታገለ እንዳለ በውል ይገነዘባል። ትላንት ማን ከጎኑ እንደቆመ ማን ደግሞ ለሻዕቢያ ወረራ ለጅብ አሳልፎ እንደሰጠው ስለሚያስታውስ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ልቡ ከማን ጋር እንዳለ ጠንቅቀን እናውቃለን። በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ክብሩንና ማንነቱን በሻዕቢያ በመደፈሩ፣ ለም መሬቱንና አንጡራ ሀብቱን ለባዕድ አሳልፎ በመሰጠቱ፣ ራሱ የሰራውን ቤት፣ በደሙና በአጥንቱ ራሱ የገነባትን ሀገር ፈርሶ የባሕር በር የሌላት ጎራዳና ሽባ ሀገር ይዞ በመቅረቱ ደስተኛ ነው ብለን በፍፁም አናምንም።
ስለሆነም ዛሬም ለገዢው ፓርቲ ህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ደግመን ደጋግመን ልናስገነዝባቸው የምንፈልገው ጉዳይ አንድና አንድ ብቻ ነው። በሀገራችን ፍትሕ የጠማው፣ በረሃብ አለንጋ የሚገረፍና በልቡ የሸፈተ ህዝብ እስካለ ድረስ እናንተ የምትፈፅሙትን ጊዜው ያለፈበትና አረሜናዊ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ ትግሉን የበለጠ እንዲግልና እንዲጎለብት ያደርገዋል እንጂ በፍፁም አይገታውም። እኛም የበለጠ እንድንጠነክርና ቀና ብለን በፅናት ከህዝባችን ጎን እንድንቆም ያደርገናል እንጂ አንገታችንን እንደማንደፋ ደግመን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ለዘላለም ትኑር

No comments: