Thursday, November 14, 2013

መምህር አበበ አካሉ በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ስለደረሰባቸው ጉዳት ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ ፡፡ ሙሉ ቃለ-ምልልሱን ያገኙታል

November 14/2013

መምህር አበበ አካሉ የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት አባልና በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡ መምህሩ አንድነት ፓርቲ በሚያደርጋቸው እንቅስቀሴዎች ላይ በመሳተፍ በተለያይ የሀገራችን ክፍሎች ተዟዙረዋል ነው፡፡ ፍኖተ ነፃነት በቅርቡ በፖለቲካ አቋማቸው የተነሳ ስለደረሰባቸው አደጋና  አሳሳቢ ስለሆነው የሀገራችን የትምህርት ጥራት ሁኔታ አነጋግራቸዋለች፤ መልካም ንባብ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በመጀመሪያ ስለራስዎ ቢያስተዋውቁን?

አቶ አበበ፡- አበበ አካሉ እባላለሁ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን የያስኩት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛና ስነ ፅሁፍ ነው ፡፡ መምህር ነኝ፡፡ ላለፉት 29 አመታት በመምህርነት ሙያዬ አገልግያለሁ፡፡
 
ፍኖተ ነፃነት፡- በቅርቡ በፖለቲካ አቋምህ የተነሳ በመንግስት ኃይሎች ጉዳት ደርሶብዎ ነበር፤ መነሻ ምክንያቱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? አሁንስ በምን ደረጃ ነው የሚገኙት?

አቶ አበበ፡- ማስጠንቀቂያዎች የደረሱኝ ፍኖተ ነፃነት ላይ በጣፎ ጉዳይ ብዙ ነገር ማጋለጥ ከጀመርን በኋላ ነው፡፡ በዚያ የተነሳ የከተማው ወጣቶች ይከተሉኝ ጀመር፡፡ ቤቴ ድረስ እየመጡ የሚያስፈራሩኝ በዚህ ነው፡፡ ተናገርክብን፣ አጋለጥከን ነው የሚሉት፡፡ ዋናው መነሻ ግን በሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ወቅት በደሴ፣በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በፊቼና በአዳማ ቅስቀሳዎችንና ሰልፎችን በመምራቴ ነው፡፡
የሚገርመው ባህር ዳር ለሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ለመሄድ ስሰናዳ ለባለቤቴ እርምጃ እንደሚወሰድብኝ መረጃ ደረሳት፡፡ ጠዋት ልወጣ ሲል ውዝግብ ውስጥ ገባን፡፡ “ሻንጣዬን ብቻ ስጪኝ፣ ይኸው ቤቱ፣ ደሞዜንም ሙሉ እሰጣዋለሁ እንጂ ማስፈራሪያ መጣ ብዬ በህገ መንግስታዊ መብቴ አልተውም አልኳት፡፡ ትንሹ ልጄም ህገ መንግስት ይዞ መጣ፡፡ በዚህ በዚህ አንቀፅ የተነሳ በማንኛውም ህጋዊ ተቋም ውስጥ የመሳተፍ፣ ሀሳቡን የመፃፍ … መብት አለው ሲል አሳመነ፡፡ በርግጥ “በትግሉ ከገፋ በወጣበት እናስቀረዋለን” ስላሏት እንጂ እሷም መብቴን ታከብራለች፡፡
 
ፍኖተ ነፃነት፡- ስትደበደብ ምን አሉህ?

አቶ አበበ፡- ከፖለቲካ አቋሜ አንስተው በሰላማዊ ሰልፉ ጉዳይ ላይ አተኮሩ ከዚያም ስለ ለገ ጣፎ ጉዳይ አነሱልኝ፡፡ “ጣፎ ላይ የተለየ አብዮት መፍጠር ትመኛለህ” አሉኝ፡፡ “እንዲያውም ጣፎ የሊብያዋ ቤንጋዚ ናት እያላችሁ ነው” ሁሉ ሲሉ ነበር፡፡ በርግጥ ጣፎ ላይ መንግስትን ሳይሆን ሙስናውን ነበር የምንዋጋው፡፡

ስለድብደባው ደግሜ መስታወስ አልፈልግም፡፡ እጄ ሰባራ ነበር፡፡ እንደ ሸንበቆ ሲያንቋቁት ምንም አይሰማቸውም ነበር፡፡ ያጠጡኝ ነገር ዶክተሩ “Absolute” አልኮል ነው ቢሎኛል፡፡ ጨጓራዬ ላይ ከባድ ችግርም አድርሶብኛል፡፡ እሽት አድርገው ከደበደቡኝ በኋላ ነው ያጋቱኝ፡፡ ሽታው አያስጠጋም ነበር፡፡ በዚያ ላይ አልኮል አልጠቀምም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በኢሳት ላይ “ሌላ የደረሰብኝ ጉዳት አለ እሱን በቅርቡ ይፋ አደርገዋለሁ” ብለው ነበር፤ ምን አይነት ጉዳት ነበር የደረሰባዎት?  

አንዳንዶች ትንሽ ጥግ ድረስ እየወሰዱ ስለፃፉት ልንገርህ፡፡ ያደረጉት በሆነ ጠንካራ ነገር ፍንጢጣዬን ወግተውኛል ፡፡ በዚያ በኩል ሱሪዬም ተቀዷል፡፡ ሁለት ቦታ የመሰንጠቅ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ ዶክተሬ በዛገ ብረት ጉዳቱን እንዳደረሱብኝ ነግሮኛል፡፡ አስቸጋሪ ነው፤ እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ቦታ ስለሆነ ተከታታይ ህክምና እየተከታተልኩ ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በጉዳትህ ወቅት አብረውህ የነበሩ ልታመሰግናቸው የምትፈልጋቸው ካሉ?

አቶ አበበ፡- በቅድሚያ ቤተሰቦቼን እንዲሁም የአንድነት ፓርቲንና አባላቱን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ከውጪ እስከ ሀገር ውስጥ በየደቂቃው የማስናኛ ስልክ እቀበል ነበር፡፡ እንደጉዳቴ ቢሆን ቆሜ አልሄድም ነበር፡፡ የጣፎ ልጆችንም ከማሳከም ጀምሮ እስካሁን አልተለዩኝም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እስኪ አሁን ደግሞ በመያህ ጋር የተያያ ጥያቄዎችን እናንሳ የመምህርነት ስራህን መቼ ጀመርክ?

አቶ አበበ፡- 24 ዓመታት ገጠር ነበርኩ፡፡ በ2000 ዓ.ም ነው ዝውውር አግኝጬ አዲሰ አበባ የገባሁት፡፡ ባለቤቴ እዚህ በመሆኗ ባልና ሚስት ማገናኘት በሚል ነው የተዘዋወርኩት፡፡ ሶስት ሊጆች አሉኝ፡፡
 
ፍኖተ ነፃነት፡- ሀያ ዘጠኝ አመት ያስተማረን ሰው ስለ ትምህርት ጥራት መጠየቅ አግባብ ይመስለኛል፤ ጥራቱ ወዴት  እያመራ ነው?

አቶ አበበ፡- በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ት/ቤት ገብቻለሁ፡፡ ወደ 6፡00 ሰዓት መንገድ ቤተሰቦቼ እያጓጓዙኝ ነው የተማርኩት፡፡ ተለምነንም ነበር የምንማረው፡፡ ወንድሞቼ ሲነግሩኝ ተማሪ ለመሳብ ስኳር፣ ዱቄት ወተት … ይሰጣቸው ነበር፡፡ ትምህርት መበላሸት የጀመረው በደርግ ዘመን ነው፡፡ ከማስፋፋት አንፃር ኢህአዴግ ደርግም ሚና ነበራቸው፡፡በደርግ ዘመን የትምህርት ጥራት መውደቅ የጀመረው “Direct Teaching” በሚል ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እየወሰደ እንዲያስተምሩ ሲያደርግ ነው፡፡ አስተማሪነት ስልጠና ያስፈልገዋል፡፡ ሳትሰለጥን ሀኪም እንደማትሆነው ሁሉ፡፡ ያ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ማስተማር ሙያ ነው፡፡ ያ ግን ኢህአዴግ የሚመፃደቅበትን የማስፋፋት ስራ ለመስራት ሲባል የተሰራ ስህተት ነው፡፡

እኔ ሁለተኛ ደረጃ የተማርኩት በ “TTI” መምህራን ነው፡፡ ነገር ግን ታላቅ ችሎታ ነበራቸው፡፡ አሁን ካለው ዲግሪ ጋርም አይነፃጸሩም፡፡ በክረምት ድግሪ ለመያዝ ከ10 በላይ ክረምት ይማሩ ነበር፡፡ ለረዥም አመት ማስተማር ማስተርስና ፒ.ኤች.ዲ እንደመስራት በለው፡፡ ደርግ የማስተማሪያ መሰላሉንም እያበላሸው መጣ፡፡ በንጉሱ ጊዜ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች በሆነ ርዕስ ላይ ጥሩ ድርሰት የሚፅፉ ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመን ለመምህራን የክረምት ትምህርት ዕድል እንኳ አልነበረም፡፡ አሁን የትምህርት ጥራት መዝቀጥ እንጂ እድሉ አለ፡፡ አንድ ዲፕሎም የነበረው የባዮሎጂ መምህሬ 10 ክረምት ከተማረ በኋላ አቋረጠ፡፡ ዛሬም ድግሪውን አልያዘም፡፡ ኢህአዴግ ግን በ4 ክረምት ዲግሪ ይሰጠሃል፡፡ ዕድል ቢሆንም ጥራቱን ገድሏል ነው የምልህ፡፡

በዚህ ላይ ሚዲያው ሁሉ እየጮኸ ነው፡፡ እኔም ፅፌአለሁ፡፡ ችግሩ ኢህአዴግ አይሰማህም፡፡ ፖለቲካውን ካልነካህበት ሀገር በአፍ ጢሟ ብትዘቀዘቅ ምኑም አይደለም፡፡ ትውልዱ ተዘቅዝቋል፡፡ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብትመጣ ስማቸውን በእንግሊዘኛ የማይፅፉ ተማሪዎች አሉ፡፡

የሚገርምህ ኢህአዴግ ለፓለቲካ በቀል አስተምርበት ከነበረው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ወደ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲወሰደኝ የበለጠ የትምህርት ስርአቱ እንዴት እንደዘቀጠ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡  የ7ኛ ክፍል ተማሪን እንደ ቄስ ትምህርት ቤት የፊደል ገበታ ዘርግቼ ፊደል እያስቆጠርኩ ነው፤ አስበው፡፡ ያሳፍራሉ፡፡ ነገ ሚኒስትሪ ወስደው “High school” ሊገቡ ነው፡፡
በአለም አቀፍ መለኪያዎች መሰረት 1ኛ ክፍል ያሉ ልጆች ከ1- 50 የ2ኛ ክፍሎች ከ1-100 መፃፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን 60 ተማሪ ካለበት ክፍል አንድ ወይ ሁለት ተማሪ ቢያደርገው ነው፡፡ መንግስት ግን ይሄን አይቀበልም፡፡ ይህ የጠላት ወሬ ነው ይለሃል፡፡ ባለው እውነት ግን 1ኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ላይ ያሉ ልጆች መፃፍ አይችሉም ፡፡
 
ፍኖተ ነፃነት፡- ችግሩ ምንድነው?

አቶ አበበ፡- መምህሩ በትምህርት ፖሊሲ ቀረፃው ላይ ሚና የለውም ፤ የመምህሩን ገብረ መልስ መንግስት አይቀበልም፡፡ ካሪኩለም ላይ፣ ሲለበስ ላይ መምህሩ አይሳተፍም፤ ባለቤቱ እቤት ተቀምጠህ ፖለቲከኛ ነው የሚቀርፅልህ ፤ ስትነግራቸው ጠላት ነህ፡፡ ለቀህ መውጣት አለብህ ትባላለህ፡፡

በዚያ ላይ ትምህርቱን አድምተህ አትሰራም፡፡ ርዕሰ መምህሩ በምርጫ ጉዳይ ላይ እንዲሰራ የማይሸከመው ጥራዝ ይሰጠዋል፡፡ 40 በመቶ ያስተምራል 60 በመቶው ፖለቲካቸውን እንዲያግዝ ይፈልጋሉ፡፡ በትምህርት ቤት በዚያ ነው የሚገመገመውም፡፡

ዛሬ ትምህርት ቤት ውስጥ የፓርቲ አባላት የሆኑ መምህራን “ግንባር ቀደም” የሚል መለያ ይሰጣቸዋል፡፡ ሌላው ድንጋይ ቢፈልጥ አይመሰገንም፣ አያድግም፡፡ ሙያዊ ፉክክር ሳይሆን፣ በሰራኸው መጠን ሳይሆን፣ ባጎበደድክበት መጠን ነው ከፍ የምትለው፡፡ በርግጥ እኔ የአንድነት ፓርቲ አባልም አመራርም መሆን እስከ ቻልኩ እነሱም መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ ጓዙን ጠቅልሎ ትምህርት ቤት መግባት የለበትም፡፡

እኔ ስመረቅ “ዲግሪውን ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ሰጥቼዋለሁ ብሎ” ነው የኒቨርሲቲው የሸኘን፡፡ ታዲያ ለምንድነው የፖለቲካ አቋሜ ይህንን መብቴን የሚያስነፍገኝ?

አዲስ አበባ ላይ መሰናዶ ትምህርት ቤት መግባት ያልቻሉት ኮተቤ ገብተው መምህራን ሆነው ይወጣሉ፡፡ ከሁለት አመት አገልግሎት በኋላ ሰመር ይገባና ዲግሪ ይይዛል፡፡

ሌላው አሳዛኝ ነገር የመምህሩ ደመወዝ ነው፡፡ ዳቦ የራበው ሰው እንደምን የትምህርት ጥራትን ያረጋግጣል? የተቀደደ ሱሪ፣ የተንሻፈፈ ጫማ አድርጎ በተማሪ ፊት የሚሸማቀቅ መምህር ከሀፍረት የበለጠ ምን ያስተምራል? አሁን ባለው ሁኔታ የደሞዝ ጉዳይ 400 ሺህ ለሚበልጥ መምህር ጫና ነው፡፡

No comments: