Tuesday, November 12, 2013

በሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ተጠያቂው ወያኔ ብቻ ነው


          
ወያኔ በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓም ጀምሮ በአገራችንና በወገኖቻችን ላይ ከፈጸማቸው በርካታ ወንጀሎች አንዱ በህጋዊ መንገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ለባርነት ወደ አረብ አገራት በመላክ የአገራችንን መልካም ዝናና የህዝባችንን ክብር ያዋረደበት ተግባር ነው::

በወያኔ ንግድ ድርጅቶች ዋና ተዋናይነት ተመልምለው ለባርነት ሥራ የሚላኩትን ዜጎች በገፍ ስትቀበል የኖረቺው ሳውድ አረቢያ የሥራ ፍቃድ ያለቀባቸውን ከአገሯ ለማባረር ሰሞኑን በወሰደቺው የማዋከብ እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን እየተደበደቡና ጎዳና ላይ እየተጎተቱ እሥር ቤት ታጉረዋል፤ ገንዘባቸውን ተዘርፈዋል፤ ከፖሊስ የሚደርስባቸውን ድብደባና እንግልት ለመቋቋም የሞከሩት በግፍ ተገድለው አስከሬናቸው ጎዳና ላይ ተጥሎሏል:: በርካታ ወጣት እህቶቻችን ደግሞ በአምስትና ስድስት የአረብ ጎረምሳ ወሲብ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ለአካልና መንፈስ ጉዳት ተዳርገዋል::

ይህ ሁሉ ሲሆን በአባይ ግድብ ግንባታ ሥም ገንዘብ ለመሰብሰብ ቦንድ ግዙ እያለ የሳውዲ ነዋሪ ሲጨቀጭቅ የኖረው በሳውዲ የወያኔ ኤምባሲም ሆነ አዲስ አበባ የሚገኙ ቅምጥል አለቆቹ ጥቃቱን ለማስቆም ድምጻቸውን ለማሰማት አለመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን ጥቃቱን ያደረሰውን የሳውዲ መንግሥት እርምጃ እውቅና የሚሰጥ መግለጫ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲህ መሰጠቱ እጅግ የሚያሳዝንና ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው::

ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው አረብ አገር በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የባርነት ስቃይ በፋሺስት ጣሊያን ዘመን በወገኖቻችን ላይ ከተፈጸመው የከፋና በተለይ በሴት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ እንደ አገርና እንደ ህዝብ የገባንበት ውድቀትና ውርደት ማሳያ ነው ብሎ ያምናል::

ስለዚህ ይህንን ውርደት ማስቆም የምንችለው ለዚህ ሁሉ መከራና ውርደት የዳረገንን የወያኔንሥርዓት ታግለን በማስወገድ በምትኩ ለአገሩና ለህዝቡ ፍቅር ያለው፤ በያንዳንዱ ዜጋ ላይ የሚደርሰው መከራና ስቃይ የሚቆረቁረው፤ አገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጥሮ ለባርነት ሥራ ወደ ውጪ የተላኩትን የሚሰበስብ መንግሥት ማቋቋም ስንችል መሆኑ ታውቆ ወያኔን ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል በተለይ ወጣቱ የህብረተሰባችን ክፍል በነቂስ እንዲቀላቀል የተቀረውም ህዝባችን አቅም የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርግ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል::

በመጨረሻም ምንም እንኳ በተለያዩ አረብ አገሮች በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ላለው መከራና ስቃይ ዋና ተጠያቂው ዜጎችን በህጋዊ መንገድ ለባርነት ከላከ ቦኋላ ጥቃት ሲፈጸምባቸው መከላከል ሳይፈልግ ዝም ብሎ እየተመለከተ ያለው የወያኔ አገዛዝ መሆኑ ባያጠያይቅም፣ የሳውዲ አረቢያም ሆነ ሌሎች አገሮች ተቆርቋሪ በለላቸው ዜጎቻችን ላይ የሚፈጽሙትን ወንጀል በአሰቸኳይ እንዲያቆሙና ተጠያቂዎቹንም ለህግ እንዲያቀርቡ ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን አቅም የፈቀደውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁሉ ወያኔን ከማስወገድ ትግል ጋር አጣምሮ እንደሚገፋ ይገልጻል::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን የህዝብ ግንኙነት

No comments: