Monday, November 18, 2013

የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኛ እንጂ ህገወጥ/ወንጀለኛ ዜጋ የለንም:

November 18/2013

- ይህ በአለም ላይ የማይካድ እውነት ነው :: ምንም ከሃገሩ ካለምክንያት አይሰደድም የአንድን ሃገር ድንበርም ጥሶ ካለምክንያት አይዘልቅም :: ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ወደ አረብ አገራት ገብተዋል :: የይልፍ ወረቀት ገዝተው በአየር የወጡትን ጉዳይ ለጊዜው ተወት እናድርገው እና ​​በዛሬው ወቅት ህገወጥ እየተባሉ በአረቦቹ እና በስርኣቱ መሪዎች ስለሚወነጀሉት ኢትዮጵያውያን አጠር ያለ ነገር እናንብብ ::

ወደ አረብ አገራት የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን በሁለት ይከፈላሉ እነዚህ ስደተኞች አብዛኛዎቹ በባህር አቋርጠው እና አስቸጋሪ ፈተናዎችን አልፈው በሰላም ወደ ፈለጉበት የደረሱ የሸሹ የተደበቁ እጅግ አሳዛኝ ዜጎች ናቸው :: በሁለት ከፍለን ስናያቸው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኞች ብለን እናስቀምጣቸዋለን : ; እነዚህ የሁለት ፈርቅ ስደተኞች በጅቡቲ እና በሱማሌላንድ ወደቦች በጀልባዎች ተጭነው የተረፈ ተርፎ የገባ ገብቶ አሁን ላሉበት ሁኔታ ደርሰዋል :: እስኪ ከፍለን እንመልከታቸው

የፖለቲካ ስደተኞች
እንዚ የፖለቲካ ስደተኞች በብዛት የተሰደዱት ከኦሮሚያ ክልል ሲሆን እነዚህ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች በተለያየ ጊዜ የእነግ አባላት ናችሁ የኦነግ ጦር ረዳቶች ናችሁ ኦነግን ትደግፋላችሁ በሚል የተለያዩ ችግሮች እና መከራዎች ሲደርሱባቸው ድብደባ እና እስር ሲፈጸምባቸው ይህንን በመሸሽ እንዲሁም የቤተሰቦቻቸውን እና የራሳቸውን የእርሻ መሬት ሲነጠቁ የስራ እድላቸው በፖለቲካ እምነታቸው ሲጋረድባቸው ስርኣቱ በፈጠረው የፖለቲካ ጫና ቤተሰብ ማስተዳደር ሲሳናቸው ወደ የመን ሳኡድ አረቢያ ደቡብ አፍሪካ እና የተለያዩ አገሮች በምድር ጉዞ ይሰደዳሉ : ; እንዲሁም ሴት ልጆች በቤተሰባቸው ላይ ፖለቲካው የፈጠረን ጫና ለማሸነፍ ሲሉ እንዲሁ ይሰደዳል :: እንዚህ የፖለቲካ ስደተኞች ራሳቸውን ለማሸነፍ ሲፍጨረጨሩ ህገወጥ ወይንም ወንጀለኛ አድርጎ ማየት ሃላፊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው ::

የኢኮኖሚ ስደተኞች
በሃገሪቱ የተንሰራፋው የዘረኝነት ጁንታ አብዛኛው ህብረተሰብ እንዳይሰራ ግሬጣ ከመሆኑም በላይ የፖለቲካው አናት የንግድ ድርጅቶቹን በማስፋፋት በሃገሪቱ አንጡረ ሃብት እየተጫወታ ዜጎችን ለድህነት አገሪቱንም ለድቀት ዳርጓል :: የሃገሪቱ የትምህርት ጥራት ትውልድ እንዳያፈራ ተደርጎ አመድ ከተለወሰ በኋላ የስራ አጥ ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል :: የምእራባውያኑ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካን እድገት ስለማይፈልጉ አምባገነንነትን በማበረታታት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ :: እንዲሁም እንደ ቻይና የመሳሰሉት አገራት ከቀን ሰራተኛ ጀምሮ በተለያዩ ለውጪ ዜጎች በማይፈቀድ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው የአገሪቱን ወጣት በስራ አጥነት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ አድርገውታል :: ይህ አይነቱ መንግስት ባለስልጣናት ነጋዴነት ሙሰኝነት የውጪ ዜጎች ካለደረጃቸው ዝቅ ብለው የሚበጠብጡት የስራ እድል አሻሚነት ተደማምሮ በአመት ከ 800,000 በላይ ስራ አጥ ስለሚፈጠር የስደት መንስኤ ሊሆን ችሏል :: ወደ አረብ አገራትም የሚሰደዱ ዜጎች የዚህ እና የተያያዥ የኢኮኖሚ ችግሮች ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ ይህ ደግሞ የስርኣቱ ለዜጎች የኑሮ እድገት ግዴለሽነት ያመለክታል ::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሄራዊ እፍረት መንስኤ የሆነው ስርኣት በሚከተለው የፖለቲካ እና የእኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ዜጎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እና ለሞት ለእስር ለስቃይ እና ለመንገላታት እንዲዳረጉ ሚናውን ተጫውቷል :: ይህንን መፍትሄ ለማምጣት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገናል በጋራ አገር ላይ በጋር እንድንሰራ እኛ እናውቅላቹዋለን የሚል ስርኣት ከነአካቴው ሊቆም እና ሃይ ሊባል ይገባዋል : ኢትዮጵያውያን በአረብ አገራት እየደረሰ ያለው መከራ የምን ውጤት ነው መፍትሄውስ ምንድነው ብለን ቆም ብለን የምናስብበት ጊዜ ነው :: ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር ስርኣቱ አሁንም ካለው እኩይ አድራጎቱ ሊቆጠብ ስለማይችል ነገ በሌላም አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ችግሮች ቢደርሱብን የገዛ ዜጎቼ ሳይሆን የሚለው አብሮ ህገወጥ እና ወንጀለኛ ብሎ በመፈረጅ ለሞት እና ለስቃይ ከመዳለግ ወደኋላ ስለማይል የትግል አድማሳችንን በማስፋት ወንጀለኛው ህገወጡ በሃገሪቱ የተንሰራፋው ስርኣት መሆኑን የማጋለጥ ግዴታ አለብን ; ጎን ለጎንም የመፍትሄ ሰዎች እየሆንን ባለው ስርኣት ላይ ጫና በማሳደር መትጋት ድርሻችን ነው ::
ምንሊክ ሳልሳዊ 






No comments: