Monday, November 25, 2013

ተዋርደን አንቀርም!!!

November 25/201
ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡

በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን፡፡
ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው“ብለዋል፡፡መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡
ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡በቃለ-መጠይቁ ሰላማው ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍጹም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን?ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?
ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው፣የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ሽማግሌወችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር፡፡ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው፡፡ከፖለቲካ ልዩነትም፣ከአምባገነንነትም በላይ ሰወቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፣ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የስልጣን ጥም የተጣባቸው፣ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው፡፡ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለው የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለው፡፡በአባላቶቻችን ላይ ክፍኛ ድብደባ ተፈጽሟል፣እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፣የሚያነክሱ ሰዎች አሉ፡፡እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው፡፡አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሶስት መደብደብን ከዚህ በተሸለ ልገልጸው አልችልም፡፡
አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ዋነው ጉዳይ የዜጎቹ ህጋዊነት ወይም ህጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፣ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፣ወይም ከህጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም፣ስለ ህግም ከተወራ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ጭፍጨፋው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል፡፡
ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት አገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም፡፡መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ከመንግስታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከዎን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግስት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም፡፡ስለ ኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ወገን ከምንለው የማህበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል፡፡
ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ህገ ውጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው?ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው፡፡
ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው?ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግስት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል?
እውነተኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰአታት ውስጥ ማባረር፣ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር፡፡የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣የድፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣አፈነን፡፡በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ህይዎት መደራደርን መርጠዋል፡፡
ስነ ልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግስት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል?እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነጻነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!::
እንዴት!
በዜጎች ህይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም፡፡የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና፡፡ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ጸብም እናውቃለን፣ሳውዲወችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም፡፡በዚህ ክፉ ጊዜ ስለስብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ እድል ይሰጠናል፡፡
መንግስት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብየ አላስብም፡፡በዚህ ሰአት ርዕሰ-መንግስት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቸን ማስወጣትን አስቀድም ነበር፡፡ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም፡፡የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው ሙሉ ሀይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡
እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ጩኸቱ ግን ይቀጥላል……ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን፡፡
አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልእክት አስተላልፏል፣ይህን መልእክት እንዲያስትላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡የሳውዲ መንግስት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣የአጥቂወቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል፡፡
ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው፡፡እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም፡፡ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም፡፡እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሀት ነው፤ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም፡፡ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ቸልታንም አስበለጡ፡፡በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም፡፡
(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሄት ተስተናግዷል፣ነገር ግን መጽሄቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ፡፡)

No comments: