Saturday, November 30, 2013

ጀኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ እና የአየር ሀይሉ አዛዥ ጄኔራል አበበ ተ/ሀይማኖት ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ መጻፋቸውን በመዘገቤ ክስ ተመሰረተብኝ

November 30/2013

ሞኑን መቼም ተወጥረናል በጭንቅ አምጠናል ገናም እያማጥን ነው…..በዚህ መሀል ወዳጄ የሆነ ጋዜጠኛ ለጃኖ መጸሔት ቃለ-ምልልስ እናድርግ አለኝ፡፡ መቼም መጠየቅ ነበር የለመድኩት አሁን አሁን እኔው ተጠያቂ ሆኛለሁ እና እሺታዬን በእሺታ አጽንቼ ጀመርን፡፡ ልጁ በዋዛ የሚለቀኝ አልሆነም እና ረዘም አድርገን እሱ ጥያቄውን ወርወር ያደርጋል እኔ ለመልሱ ስንጣጣ እውላልሁ..ነካክቶ እያናገረኝ ነው ተከታተሉት….

ጃኖ፡-ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ኃይማኖት በመጀመሪያ በስደት ካለህበት ሃገር ካለህ የተጣበበ ጊዜ ቀንሰህ ይህን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆንህ በሞያ አገሮችህና በአንባብያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ግሩም ተሀይማኖት፡-በእርግጥ እኔም ላመሰግናችሁ ይገባኛል፡፡ ያውም በብዙ ምክንያት…አንደኛ ልገልጸው የሚገባኝን ሀሳብ እንድገልጽ ስታደርጉኝ ሁለተኛ፡-ነፃ ፕሬሱ መንምኖ ጥቂቶች ብቅ ባሉበት ሁኔታ በርትታችሁ ለሁሉም ሰው ነጸ መድረክ በመሆናችሁ አመሰግናለሁ፡፡ እኔም ለሰዎች ቃለ-መጠይቅ ማቅረብ እንጂ መጠየቅ ስላለመድኩ እንድለምድም እድሉን ሰጣችሁኝ ደግሜ አመሰግናሁ፡፡

ጃኖ፡-በሀገር ውስጥ በስራ ከነበርክባቸው እንጀምርና የትኞቹ ፕሬሶች ላይ ሰርተሃል? በግልህ አሳታሚ ነበርክ?

ግሩም ተሀይማኖት፡- ሀገር ውስጥ እያለሁ በጣም በርካታ መጸሔቶችና ጋዜጦች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ገና ተማሪ እያለሁ አዲስ ዘመን ላይ ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት አድማስ አምድን በሚሰራበት ሰዓት ጽሁፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አወጣልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እስካሁን ለቁጥር በሚታክት ሁኔታ ሰርቻለሁ፡፡ ምኒልክ እና ዜጋ መጸሔቶች ዳግማዊ፣ ትውስታ፣ መብረቅ፣ ዳግማዊ ወንጭፍ፣ ቅይጥ፣ ክብሪት፣ የፍቅር ሕይወት፣ ገመና፣ አስኳል ሳተናው፣ ምኒልክ….የመሳሰሉትን ጋዜጦች ሰርቻለሁ፡፡ ግል ሚዲያው ላይ ከአስራአንድ አመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህን ጊዜ ውስጥ በ1990 ዓ.ም ላይ በምዝግባ ቁጥር 02764/90 የሆነ ንግድ ፍቃድ አውጥቼ ‹‹ገመና›› የሚል ጋዜጣ አሳትሜም ነበር ፡፡

ጃኖ፡-እንዴት ነበር በወቅቱ የነበረው የስራ ሁኔታ?

ግሩም ተሀይማኖት፡- በወቅቱ የነበረው በጣም አስፈሪ እና በስጋት የተሞላ በሙሉ ፍላጎት የሚሰራ እና ብዙ መሰዋዕትነት የተከፈለበት ሁኔተ ነበር፡፡ የያኔውን የስራ ሁኔታ ለማስታወስ አሁን ላይ ሆኜ የትዝታ መነጽሬን ስከፍተው ብዙ አሳዛኝ እና ጥቂት ደስ የሚል ነገር አስታውሳለሁ፡፡ ነፃ-ፕሬሱ ብዙ መሰዋዕትነቶች ተከፍለውበታል፡፡ ታስረናል፣ ተደብድበናል፣ ተገርፈናል..በእርግጥ የጓደኞቼን አልኩ እንጂ ከመታሰርና ከመደብደብ አልፎ መገረፍ ላይ አልደረስኩም፡፡ በርካታዎች ግን ተገርፈዋል፡፡ መታሰር ግን እስክጠግብ አይቼዋለሁ፡፡ ታፍነን ታስረናል፡፡ በስልክ እየተጠራን ማዕካላዊ ወንጀል ምርመራን ለበርካታ ጊዜ ጎብኝተናል(የምንጠራበት ጊዜ ከመብዛቱ የተነሳ ጉብኝት ተጠርቻለሁ እንባባል ነበር) ከምንም በላይ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እኔና ጓደኛዮ ዳንኤል ገዛኸኝ ታስረን የገጠመን ሁኔታ ምን ጊዜም ስለ ፕሬሱ ሲነሳ ትውስ ይለኛል፡፡ ሰው ላይ ሊፈጸም የማይገባው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞብናል፡፡እራቴን አራት ኪሎ ዘውዲቱ ሆቴል እየበላሁ በሲቪል ለባሾች ተያዝኩኝ፡፡ ሌሊቱን ስደበደብ አደርኩ፡፡ ለሽንት ስሄድ በውሻ ሁሉ አስነክሰውኝ ለዛውም ከእስረኛ ጋር ሳይሆን ጊቢው ውስጥ ከኢህአፓ ጊዜ ጀምሮ የቆሙ ሽንት ሲሸናበቸው የነበሩ ውስጣቸው አይጥ የሚርመሰመስባቸው ቮክስዋገን መኪና ውስጥ ነው ለአንድ ሳምንት የታሰርኩት፡፡

ማንም ሊያስበው የሚገባው በኢንፎርሜሽን፣ በግንኙነት ዘመን የገዛ ሃሳብህን አትግለጽ፣ የገዛ ጽሁፍህን አትጫር ትባላለህ፣ ትባየለሽ እንባለለን፡፡እነሱ ያሰቡትን ፣የጻፉትን ግን እንድትቃወም እንኳን ላይፈቀድልህ ሁላ ይችላል፡፡ ደግሞም አሁንም ቢሆን አይፈቀድም፡፡ ተናገር ተብለህ ንግግርህ ተመዝኖ፣ ብዕርህ ተገድቦ፣ ልሳንህ ተመርምሮ በመናገር፣ በመጻፍ መብትህ ተወንጅለህ ትታሰራለህ፡፡ እንታሰራለን፡፡ ስንቶች ታሰረዋል? ስንቶች ተሰደናል? ማንስ ይህን ያህል ማለት ይችላል?

ጃኖ፡-አሁን ካለው ሁኔታ በግል ፕሬስ ለመሰማራትና ፈቃድ ለማውጣት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው አንተ ሃገር ውስጥ በነበርክበት ጊዜ እንዴት ነበር? ማስታወሻ፡- አሁን ፈቃድ ለማውጣት ካፒታል፣ ምሩቅ የሆነ ባለሙያ፣ ኃላፊዎች መጥተው የሚያዩት በቂ ቢሮ፣ ኮፒውተር፣ ፕሪንተር፣ መቅረፅ ድምፅ፣ ዲጂታል የፎቶ ካሜራ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን በግድ ማሟላት ያስፈልጋል አንተ ከነበርክበት ጊዜ ጋር አነፃፅረህ ንገረኝ?

ግሩም ተሀይማኖት፡- አሁን ሱሪ በአንገት አውጣ አይነት ትዕዛዝ ነው፡፡ ነጻ ፕሬስ ክፍት ነው፣ የመናገር ነጻነት አለ ለማለት ያህል ነው፡፡ ግን ወደዛ እንዳትገባ ነገሮቹን ያከፉት አጣብቂኙን በደንብ ያጠበቡት፡፡ ለፕሬስ ስራ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ቢሆንም ከዚህ የበለጠም የምታሟላው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ፍቃድ ባወጠሁበት ጊዜ ይሄ ሁሉ ጣጣ የለም ነበር፡፡ አሁን እኮ ሁሉን ነገር አሟልተህ ፍቃዱን አውጥተህ ስትሰራ ደስ ባላቸው ጊዜ ሊያቆሙህ ይችላሉ፡፡ የአንተ መስራትም ሆነ ማናገር በእነሱ ቸርነት ላይ ተመስርቶ የተንጠለጠለ ነው፡፡

ጃኖ፡-በወቅቱ የታሰርክበት፣ የተከሰስክበት፣ በፓሊስ (በደህንነት) የተሳደድክበት በዚህ ዙሪያ የገጠመህ ነገሮች ነበሩ?

ግሩም ተሀይማኖት፡- መታሰር፣ መከሰስ…መሳደድን ካነህማ ትዝታውን ሁሉ ባነሳው ይሄ መድረክ ላይበቃ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰስኩት በዳግማዊ ጋዜጣ ነው፡፡ ከዛ በኋለ በራሴ የህትመት ድርጅት ስር አሳትመው በነበረው ገመነ ጋዜጣ የተከሰስኩት ነው ሰቅጣጭ የነበረው፡፡ የተከሰስንበትን ዜና ሙሉ መረጃ አቅርበን ነበር፡፡

በዜናው የዳሰስነው…ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በጦርነቱ ለተጎዱ ቤተክርስቲያናት ማደሻ ከጎንደር አገረ ስብከት ጽ/ቤት ጥያቄ ቀረበ፡፡ በወቅቱ ጠ/ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ነበር ጥያቄው የቀረበው፡፡ ምንም አይነት ባጀት የለንም 10 ቶን ቡና ተፈቅዶላችኋል እሱን ወስዳችሁ ሽጡና በትርፉ የተወሰኑትን አድሱ ተባለ፡፡ ይሄን ቡና ወስዶ የመሸጡን ሀላፊነት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አንድ ዲያቆን ወከሉ፡፡ ቡናው ተሸጦ ግን ለቤተክርስቲያኗ ማደሻ ሳይሆን ለአፍ ማሰሻ፣ ለኪስ ማደለቢያ ነው የሆነው፡፡

ቢታይ ቢታይ ሁሉም ዝም..ሆነ፡፡ ቄሱም ዝም መጽሀፉም ዝም እንደሚባለው ዝም ሆነ፡፡ ነገሩ የከነከናቸው አንዳንድ ካህናት ቤተክህነት ድረስ ለክስ ከጎንደር መጡ፡፡ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ተባሉ፡፡ መፍትሄም ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ማስፈራሪያ ሁሉ ታከለላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ አሳትም ነበረ እና ሙሉ መረጃውን ሰጡኝ፡፡ አጣርቼ ትክክለኛ ማስረጃ በመሆኑ ለህዝብ አቀረብኩት፡፡ የመረጃውንም ኮፒ ጋዜጣው ላይ አተምኩ፡፡ ወዲያው በብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ክስ ተከፈተብኝ፡፡ የክሳቸው ፍሬ ሀሳብ ትክክለኛ እና መጠየቅ ያለበትን ነው የጠየቁት፡፡ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ ያወጣውን ዘገባ አይተን ሁኔታውን ለማጣራት ሞክረናል፡፡ የተጠቀሱት ግለስብ የቀረበብኝ ማስረጃ ፎርጅድ ነው እኔ ስለሁኔታው አላውቅም ስላሉ ጋዜጠኛው ላይ ክስ ተመስርቶ ያለው ማስረጃ እንዲረጋገጥ፡፡ ትክክለኛ ከሆነ የጉዳዩ ባለቤቶች እንዲጠየቁ፡፡ ያቀረበው ማስረጃ ትክክለኛ ካልሆነ እና ፎርጅድ ከሆነ የእምነታችንን ክብር የሚያወርድ ነገር በሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረቡ እንዲጠየቅ..ይላል፡፡ በዚህ ክስ ቅሬታ የለኝም፡፡

ለመርማሪ ፖሊሱ ግን ገንዘብ ሰጥተው ትንሽ ቅጣትም ያሰፈልጋቸዋል፡፡ በደንብ መርምርልኝ ማለታቸው ከሀይማኖት አባት የሚጠበቅ ይሆን? እኔ አልጠብቀውም ነበር፡፡ በማወቅም ባለማወቅም በድለውኛል፡፡ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀምብኝ አድርገዋል፡፡ ዛሬ እሳቸው እውነቱ ቦታ ሄደዋል፡፡ ነፍሳቸውን ይማር ለበደሉኝ ሁሉ ይቅር ይበላቸው፡፡ እኔ ይቅር ብያቸዋለሁ፡፡

ክትትል ሲደረግብኝ ቆይቶ ዘውዲቱ ሆቴል ራት እየበላሁ ሳለ ተያዝኩ፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ ገና ከመግባቴ ጀምሮ ዱላ ተቀበለኝ፡፡ ውብሸት የሚባል መርማሪ ወዲያው ስልክ ደውሎ መያዜን ሲናገር ከቢሮው ውጭ ብቀመጥም እየሰማሁት ነው፡፡ ቃል ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኔ ሶስት ፖሊሶችን ጠርቶ ከራሱ ጋር አራት ሆነው ሰማይ ምድሩ እስኪዞርብኝ አዞሩኝ፣ ቀጠቀጡኝ፡፡ በግድ ግን ቃሌን ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆንኩም፡፡ መረጃው አለህ? ያለህ መረጃ ፎርጅድ ነው ተብሏል፡፡ እላዩ ላይ ያለው ማህተም የጎንደር የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አይደለም አለኝ፡፡ /አንድ ወረቀት ላይ ያረፈ ማህተም እያሳየኝ/ የእሳቸው ማህተም ይሄ ነው ..›› ሲለኝ ግን እልህ ያዘኝ፡፡ ማህተሙን ከዚህ ወረቀት በኋላ መቀየራቸውን የሚያረጋግጥ ትንሳዔ ዘ ጉባኤ ማተሚያ ቤት ማህተም ያስቀረጹበት ማስረጃ እንዳለኝ ጭምር ቃል ሰጠሁ፡፡ ይህንን የሰጠሁትን ቃል ግን ወዲያውኑ ደውሎ የነገራቸው ፊቴ ነው፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ተከሳሽ የሆነው ዲያቆን ጉዳዩን እንዲከታተል በብጹዕ አቡነ ጳውሎስ ትዕዛዝ ተላከ፡፡ በዛው ማታ ሲበር መጣ፡፡ ይሄኔ ነገሮች ሁሉ ጎረበጡኝ፡፡ በጣም ተጠራጠርኩ፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ቤቴ ሄደን መረጃውን እንድናመጣ ፈለጉ፡፡ ግደሉኝ እንጂ አልሄድም እናቴ በዚህ ሰዓት እንድትደነግጥ አልፈልግም አልኩ፡፡ ሰበቤ በእናቴ ሆነ እንጂ እሳቸውስ መረጃው እንዲጠፋ ካልፈለጉ እንዴት ብሩን ያጨበረበረውን ሰው ይልካሉ? ለምንስ እሰኪነጋ መጠበቅ ሳይፈልግ ዲያቆኑ መጣ? ፍርድ ቤት ስቀርብ ካልሆነ ላለማቅረብ ወሰንኩ፡፡ ዳግም ዱላ ተጀመረ፡፡ እነሱ ሳይበቃቸው እኔ ተዝለፍልፌ ስለወደኩኝ መሰለኝ ድብደባው የተጠናቀቀው፡፡ ራሴን ስለሳትኩ እንዴት እንደነበር ብዙም አላውቅም፡፡ ራሴን ሳውቅ ግን ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል፡፡

ሽንቴ ስለመጣ ካጋደሙኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ቀና ብዬ ሽንት ቤቱ የቱ ጋር እንደሆነ ተረኛውን ፖሊስ ጠየኩት፡፡ አሳየኝ እና ተነስቼ ስሄድ ውሻዋን ጃስ..ጃስ..ብሎ ሲያደፋፍራት እግሬን ዘነጠለችን፡ ወይም ዘነጠለኝ፡፡ የውሻውን ፆታ ስለማላውቅ ነው ሁለቱንም የተጠቀምኩት፡፡ እየተሳሳቁ ደግፈው አንስተውኝ ጊቢው ውስጥ ቆማ የበሰበሰች እና ሽንት የሚሸናባት አይጥ የሚርመሰመስባት አሮጌ መኪና ውስጥ ከተቱኝ፡፡ በማግስቱ ጓደኛዬ ዳንኤል የጋዜጣዬ ዋና አዘጋጅ ስለሆነ መታሰሬን ሰምቶ ፖሊስ ጣቢያ መጣ፡፡ ሳምንት ሙሉ እዛች የሚሸናባት መኪና ውስጥ አሳለፍን፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተነስቶ በመላ ሀገሪቱ ያዳረሰው የተመሪዎች አመጽ ረቡዕ ሚያዚያ 10/ 1993 ቀን በአሳዘኝ ሁኔታ የተጠናቀቀው የነበረውን ሁኔታ ከጠዋት ጀምሮ ያነዊነ ሁኔታ በመዘገቤ ከማስፈረሪያ ጀምሮ ክስ ድረስ ደርሸለሁ፡፡ አርብ ሚያዚያ 12 ቀን 1993 ዓ.ም የታተመው ምኒልክ ጋዜጣ ላይ ነበር ዘገባውን ያቀረብኩት፡፡ ዜናውን እንደልብ ለመዘገብ እንዲያመቸኝ ብዬ በትረካ መልክ ‹‹..ከመኖሪያ ቤቴ ፊት ለፊት ያለውን ቅ/ ማሪያም ቤት ክርስቲያ ለመሳለም ስጠጋ ጥያቄያችን ካልተመለሰ አንማርም ያሉት የዩንቨርስቲው ተማሪዎች ጊቢውን ሞልተውታል፡፡
 ምንድን ነው ብዬ ስጠይቅ ካተማራችሁ ጊቢውን ለቃችሁ ውጡ መባለቸውን ነገሩኝ…›› በመለት ጀምሬ ሙሉ ቀን የየሁትን የሞተውን የቆሰለውን ሁሉ በዘገባዬ ገለጽኩ፡፡ ነገሩ የመጣው ከኋላ ነው፡፡ ለካ ራሴ ለይ ራሴ ጠቁሜ ነበር፡፡ ቅ/ማሪያም ጋር ያለ ጋዜጠኛ ማነው? ብዙ ሳይደክሙ አገኙኝ፡፡

በሰዓቱ እኔ አቡዋሬ አካባቢ ነበር ተከራይቼ የምኖረው እንደ አገጣሚ እናቴ ገር የደርኩ ቀን ነበር ቅ/ማርያም ውስጥ ያንን ሁኔታ ያየሁት፡፡ እነሱ ሊይዙኝ ሲመጡ ደግሞ እዛ አልነበርኩም፡፡ የተከራየሁት ቤት ነበርኩ፡፡ ወንድሜን ይዘውት ሄዱ፡፡ ወንድሜ መታሰሩን ስሰማ ሮጬ ሄድኩ፡፡
ሌላኛው እና አስቂኝ ክሴ አስኳል ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኜ ስሰራ ነው፡፡ ህወሀት ለሁለት ተከፈለ የሚለውን ዜና በቅድሚያ ለህዝብ የደረስነው እኛ ነበርን፡፡ ከዛ ሁኔታዎችን እየተከታተልን ስንሰራ ጀኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ እና የአየር ሀይሉ አዛዥ ጄኔራል አበበ ተ/ሀይማኖት ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ መጻፋቸውን ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 1993 በወጣው አስኳል ጋዜጣ ላይ አተምነው፡፡ ይህን ጋዜጣ ለስድስት አመት በዋና አዘጋጅነት የሰራሁት እኔ በመሆኔ በወቅቱም ክሱ ወደ እኔ ነው የመጣው፡፡ ግንቦት 10 ቀን 1993 ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መርማሪው ስልክ ደውሎ ጠራኝ፡፡ ቀኑ አርብ ነው በዚህ ቀን ማዕከላዊ መሄድ አደጋ አለው፡፡ ዋስ ካልተሳካ ቅዳሜ እና እሁድን እዛው መቆየት ነው፡፡ ስለዚህ ሰኞ ለመሄድ አሰብኩ፡፡ አጋጣሚ ሰኞ ደግሞ አስኳል ጋዜጣ ማክሰኞ ስለሆነ የሚወጣው ማተሚያ ቤት ስለሚገባ ስራ መሯሯጥ ነበር፡፡ ማክሰኞ እለት ስሄድ መርማሪው የለም፡፡ ማታ ላይ ኢትዮጵያ ሬድዬ በዜና እወጃው ሁለቱም ጄኔራሎች ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ዘገበ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ረቡዕ ዕለት በጠዋት ስሄድ ከመርማሪው ጋር ስንገናኝ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው እውን ከሆነ የምከሰሰው ለምንድን ነው አልኩት፡፡ እኔ ምን አውቃለሁ ብሎ ቃል ሰጠሁና የማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ አዛዡ ጋር አቀረበኝ፡፡ ለማንኛውም ዋስ ይጥራ ተብሎ አውለውኝ በዋስ ወጣሁ፡፡ ብቻ ብዙ ክስ አለብኝ፡፡
ጃኖ፡-አጠቃላይ በሀገር ውስጥ ከመቼ እስከ መቼ ዓ.ም በስራ ላይ ቆይህ?

ግሩም ተሀይማኖት፡- የእኔ የስራ ዘመን የሚጀመረው ከልጅነቴ ነው፡፡ ጋዜጣ አዙሬ ሸጬ ከሁሉም አንዳንድ ትርፌን ይዤ እገባና ማታ ማታ አነበለሁ እጽፋለሁ፡፡ በፖስታም ሆነ በአካል ሄጄ እሰጣቸዋለሁ፡፡ በደንብ የጀመርኩት ግን በ1986 ነው፡፡ ሀገሬን ለቅቄ እስከወጠሁበት 1997 መጨረሻ ድረስም ሰርቻለሁ፡፡

ጃኖ፡-ከዚያስ ምን ተፈጠረ (ለስደት ያበቃህ) ምንድን ነበር?

ግሩም ተሀይማኖት፡- አስኳል ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት ለስድስት አመት ሰርቻለሁ ብዬሀለሁ፡፡ በዛን ወቅት ‹‹ወግድ ይሁዳ›› በሚል ርዕስ ታዲዮስ ታንቱ ተከታታይ ጽሁፍ ይጽፍ ነበር፡፡ ይህ ጽሁፍ ዝም ብሎ የተጻፈ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች ከመጀመሪያው ስላላዩት በስሜታዊነት፣ በጥላቻ የተጻፈ ነው የሚመስላቸው፡፡ ግን አይደለም፡፡ አቶ በላይ ግደይ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ እና..›› የሚል መጽሀፍ አሳትመው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ሁሉ ጠቅልለው የትግራይ አድርገውታል፡፡ ለዛ ምላሽ ነው ታደዲዮስ ታንቱ ‹‹ወግድ የይሁዳ›› ብሎ ምላሽ የሰጠው፡፡ በእሱ ምክንያት 22 የትግራይ ባለስልጣናት ተፈራርመው ከሰሱን፡፡ ከዚህ ክስ በኋላ መግቢያ መውጫ ጠፋ በኋላ ነገሩ ክፋ ብዙ ዛሬ ልገልጽ የማልችለው ነገር ተከሰተ ሀገሬን ጥዬ ወጣሁ፡

No comments: