Wednesday, April 3, 2013

አንድነት በህሊና እስረኞች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊጀምር ነው

 

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባል የሆነው አቶ ናትናኤል መኮንን ከአንድ ሳምንት በላይ በርሀብ አድማ ላይ እንደሚገኝ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፁ፡፡

በቂሊንጦ ወህኒ ቤት በቅርቡ በተደረገ ስብሰባ ላይ አልሳተፍም በማለቱ ብቻ ለአንድ ወር ከቤተሰቦቹ ጋር እንዳይገናኝ የተከለከለው አቶ ናትናኤል የወህኒ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ከአንድ ሳምንት በላይ በርሀብ አድማ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ናትናኤል መኮንን ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ መደረጉን በመቃወም የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ወህኒ ቤት በማምራት ማብራሪያ እንደሚጠይቁና ምክንያቱን እንደሚያጣሩ ፓርቲው ለፍኖተ ነፃነት አስታውቋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ለፍኖተ ነፃነት እንደተናገሩት አንባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ዜጎችን ማሰሩ ሳያንስ በወህኒ ቤት ውስጥ የሚያደርሰውን ኢሰብአዊ ድርጊት ፓርቲው ያወግዘዋል፡፡ በተለይም በህሊና እስረኞች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም ሊወስድ ላሰበው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መረጃ ለማሰባሰብ ይረዳው ዘንድ የፓርቲውን ሊቀመንበርና ሁለት ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ ቡድን አቋቁሟል፡፡ ቡድኑ ከወህኒ ቤቱ የሚያገኙትን መልስ መሰረት አድርጎ ፓርቲው የራሱን እርምጃ ይወስዳል፡፡

በፍኖተ ነፃነት አቶ ናትናኤል ስላሉበት ሁኔታ እንዲያስረዱ የተጠየቁት ባለቤታቸው ወ/ሮ ፍቅርተ…. ከአንድ ሳምንት በላይ አቶ ናትናኤልን እንዳላያቸው ገልፀው፤ “ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሚላክለትን ምግብ አልተቀበለም፤ ያለበት ሁኔታም አሳስቦኛል” ብለዋል፡፡

No comments: