Monday, April 29, 2013

የወያኔ ፖሊሶች ከግንቦት7 ህዝባዊ ኃይል ጋር ግንኙነት አለዉ የሚሉትን ወጣት ሁሉ እየከበቡ ማሰር ጀመሩ

የዘረኛዉ ወያኔ የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች በቅርቡ እራሱን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ ካስተዋወቀዉ ከግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ጋር ግንኙነት አለዉ ብለዉ የሚጠረጥሩትን ወጣት እያደኑ ማሰር መጀመራቸዉን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ታማኝ የአገር ዉስጥ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ በዘገበዉ ዜና ገለጸ። ለኢሳት የደረሰው መረጃ መሠረት መሳሪያ አንግበዉ ከአዲስ አበባ በብዛት የተንቀሳቀሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከባህርዳር በ35 ኪሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘዉ መርአዊ የምትባል ከተማ በመሄድ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አፍነው አዲስ አበባ ዉስጥ ለግዜዉ ወዳልታወቀ ቦታ እንደወሰዷቸዉ ለማወቅ ተችሏል።

ምሽት ላይ አድፍጠዉ መርአዊ ከተማ የገቡት ፖሊሶችና የደህንነት ኃይሎች የአካባቢውን ሰዎች በማስፈራራት ተማሪዎቹን አፍነው የወሰዱዋቸው ሲሆን፣ በወቅቱ አንድ ወጣት ክፉኛ መደብደቡን ለማረጋጥ ተችሏል። አንድ የባህር ዳር ነዋሪ ለግንቦት ሰባት ዜና ዜና ዝግጅት ክፍል ስልክ ደዉለዉ የተማሪዎቹን መታሰርና መደብደብ ካወገዙ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ አንቅሮ እንደተፋዉና ስርአቱን ለመደምሰስ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የተረዳዉ ወያኔ የቀብፀ ተስፋ እርምጃ መዉሰዱ የሚገርም ባይሆንም አይኑ ያተፈበትንና ገደብ የሌለዉ እጁ የደረሰበትን ዜጋ ሁሉ እያፈሰ ማሰር መጀመሩ ህዝብ የጀመረዉን የፍትህ፤ የነጻነትና የደሞክራሲ ትግል አጠናክሮ የድሉን ግዜ ያፋጥነዋል እንጂ አያሳጥረዉም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የደህንነት ሹም በመሆን ለረጅም ጊዜ ያገለገለዉ የሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ወያኔን በመክዳት የግንቦት7 ህዝባዊ ሀይልን መቀላቀሉ ታውቋል። ሻለቃ መሳፍንት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ስላለው የዘር ችግር፣ በብአዴን ውስጥ ስለሚነሱ ቅሬታዎች እና መሰል ጉዳዮች ዛሬ ከኢሳት ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርጓል። ሙሉ ቃለምልልሱ በቅርቡ ይቀርባል።

No comments: