Wednesday, April 10, 2013

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ውይይት ተጀመረ

ሚድያ የመሪነቱን ሚና እንዲጫወት ተጠየቀ
በድንበር ግጭቱ ምክንያት የሁለቱም አገሮች መንግሥታት ግንኙነት እስካሁን ሰላምም ሆነ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ያሉ ቢሆንም፣ ከመንግሥታቱ ውጪ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ለማደስ ይፋዊ ውይይት ተጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ባለፈው ቅዳሜ በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው ስብሰባ ስድስት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በስደት ላይ የሚገኙና በአብዛኛው በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ዕድል ያገኙ የኤርትራ ወጣቶች፣ እንዲሁም ደግሞ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተወከሉ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል፡፡

በተለይ ኤርትራውያን ወጣቶች በኤርትራ መንግሥት ሚዲያ ሲነገራቸው የቆየው ፀረ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ በስንት መከራ ተሻግረው በስደት የሚገኙት ግን ከየትኛውም አገር ከሚገኙት ኤርትራውያን የተሻለ መሆኑንና በሁለተኛ ቤታቸው ያሉ መስሎ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡ በኤርትራ መንግሥት ሲነገራቸው የቆየው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ውሸት መሆኑን፣ በኤርትራም ሆነ በሌላ አካባቢ ያሉ ኤርትራውያን ዜጎችን በማስገንዘብ ላይ እንደሚገኙ አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲሳካ በኤርትራ ላሉት ዜጎችስ ምን ሊፈይድ ይችላል?›› በሚል ጥያቄ ያቀረቡም ነበሩ፡፡

ከሁለቱም ወገኖች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዴት መጠናከር እንዳለበት ሐሳቦች ቀርበው፣ የመድረኩ መሪ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አምባሳደር ብርሃነ ደሬሳ፣ በተለያዩ አገሮች ከኢትዮጵያና ከኤርትራ በባሰ ሁኔታ በደም የተቃቡ ሕዝቦች ይቅር ተባብለው ተቀራርበው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማደስ የመንግሥትም የግሉ ሚዲያም ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ወጣት ሰለሃዲን እሸቱ ስለ ወጣቶች ዕይታ፣ አቶ ፀጋልዑል ወልደ ኪዳን የሕይወት ተሞክሮአቸውን፣ ወጣት መርከብ ነጋሽ (ከጅማ ዩኒቨርሲቲ) ስለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ምንነት ጥናት ሲያቀርቡ፣ በኤርትራ በኩል በአዲስ አበባ የኤርትራ ስደተኞች ተወካይ ወ/ሮ ሳሊሃ ኢብራሒም የሕይወት ተሞክሯቸውን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳምሶን ይሳክ የኤርትራ ወጣቶች ዕይታን በተመለከተ ጥናት አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም የሪፖርተር ጋዜጣ የፖለቲካ ዓምድ ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ የኢትዮ ኤርትራ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማደስ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን መሆን እንዳለበት በተመለከተ ጥናት አቅርቧል፡፡

No comments: