Tuesday, April 2, 2013

ለዜጎች መሞት፣ መፈናቀልና መሰደድ ተጠያቂው መንግስት ነው!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን
በተደጋጋሚ ፓርቲያችን እንደሚገልፀው አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የሚከተለው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝምና የስርዓቱ አራማጆች ካላቸው የስልጣን እድሜን የማራዘም ጉጉት ተደማምረው ለሃገራችን እንዲሁም ተቻችሎ፣ ተዋልዶ፣ ተዛምዶና ተዋድዶ ለዘመናት ይኖር ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅና አስፈሪ አደጋ ወደ መሆን እንደደረሱ በግላጭ እየታየ ነው፡፡ለዜጎች መሞት፣ መፈናቀልና መሰደድ ተጠያቂው መንግስት ነው!!!
ያ ለዘመናት አብሮን የቆየው በጋራ የመኖር ዕሴት እየተደመሰሰ በምትኩ የሚያጋጩ ስልቶች እየተፈጠሩና እየተተገበሩ ወደ ሰቆቃ ተለውጠው ይገኛሉ፡፡ የዜጎች ሰዋዊና ህጋዊ መብት እየተጣሰም ነው፡፡ በኢትዮጵያችን ውስጥ አብሮ የመኖር፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና በፈለጉት ቦታ ሃብት የማፍራት ህልውና እያከተመ መጥቷል፡፡ ለዚህ ክፉ ድርጊት ተጠያቂ የሚሆነው ደግሞ የዜጎችን መዘዋወር መብትና ሃብት የማፍራት መብት ማረጋገጥ የተሳነው መንግስትና መንግስት ብቻ ነው፡፡
የከዚህ በፊቱን የማፈናቀል ግፍ ትተን በቅርቡ እንኳ በጉረፈርዳና በሌሎች አካባቢዎች በቀጥታ በክልሉ ባለስልጣናት በተፃፈ ደብዳቤ ይሄ ሀገራችሁ አይደለም ተብለው፣ ሃብትና ንብረታቸው ተዘርፎ፣ የወለዱ አራሶች እንኳን የማገገሚያ ጊዜ ሳይሰጣቸው ደማቸውን እያዘሩ ሲባረሩ ከመንግስት የተሰጠው ምላሽ ‹‹ሞፈር ዘመቶች ናቸው (ማረሻውን ብቻ ተሸክሞ ወደ ሌላ ሀገር የሚሰደድ ለማለት ይመስለናል)›› የሚል ነበር፡፡ ይሄም ቢሆን የማንኛውም ዜጋ መብት ነው፡፡ መንግስት እነዚህ ዜጎች ‹‹ሃገራችን የት ነው?›› በማለት ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ የለውም፡፡
ገዥው ፓርቲ ሃላፊነትን መዘንጋትንና ስህተትን በማረም ፈንታ አፋፍሞ በመቀጠል ዜጎች ሃብትና ንብረታቸው እየተዘረፈ መባረራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህም በጋምቤላና ቤኒሻንጉል በከፋ መልኩ ቀጥሏል፡፡ በተለይ ከቤኒሻንጉል ክልል የአማራ ተወላጅ የሆኑትን ዜጎች የዘመናችን ሹመኞች ከኢ-ሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ ከእቃ ለሚሰጥ ክብር ባነሰ ሁኔታ ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ በጅምላ እየተጫኑ መጣላቸውን ቀጥለዋል፡፡ በርካታ ህፃናትም የዚህ ግፍ ሰለባ ሆነዋል፤ እየታፈኑ የሚሞቱትም ቁጥራቸው በርካታ ነው፤ በጣም የሚያሳቅቀው ደግሞ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት 59 ሰዎች ሞት ጉዳይ ነው፡፡ ካላግባብ በጭካኔ ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት፣ ከወለዱበትና ከከበዱበት ስፍራ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአንድ መኪና እየታጨቁ እንዲወጡ በማድረግ ገደል ውስጥ ገብተው እንዲሞቱ የተፈረደባቸው ዜጎችን ህይወት እንዲቀጠፍ ያደረገውም በቸልታ እየገዛ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡ መንግስት በነዚህ ዜጎች ላይ ለደረሰው ኢ- ሰብዓዊ ድርጊትና ህይወት ማጣት ተጠያቂ ነው በማለት ፓርቲያችን ያምናል፡፡
ፓርቲያችን አንድነትም ጥያቄ ያነሳል፡፡ ለውጭ ዜጎች እንዲበለፅጉበት በትንሽ ሳንቲም፤ ግልፅነት በጎደለውና በሙስና በተተበተበ አሰራር ለቻይና ኩባንያዎች፣ ለህንድ ኩባንያዎች፣ ለሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች ወዘተ ለዜጎቻቸው ቀለብ እንዲያመርቱበት በገመድ እየተለካ የሚሰጠው የአዲስ አበባን ስፋት አምስት ጊዜ የሚበልጥ መሬት እንዴት ለዜጎቹ ይነፈጋል? ለምንስ ኢትዮጵያውያን ተዘዋውረው በኩርማን መሬት ላይ ሃብት የማፍራት መብታቸውን ተነፈጉ? ይህንን ኢሰብኣዊነት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲያውቁት እንፈልጋለን፡፡ ኢህአዴግንንና በእሱ የሚመራውን መንግስት ታሪክና ሕዝብ ይፋረደዋል፡፡ ይህንንም በደል እያዩና እየሰሙ ዝም ማለት የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ዛሬውኑ ተቃውሞአችንን፣ ጩኸታችንን እናሰማ፤ በደል ሰቆቃ በቃ እንላለን፡፡

No comments: