Saturday, April 6, 2013

ለ3ኛ ጊዜ ህትመቱ የተቋረጠበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ” ከእንግዲህ ከጫካ መለስ ባሉ መታገያ መንገዶች በመጠቀም መብታችን እናስከብራለን” አለ

መጋቢት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይህን የተናገረው ልእልና ጋዜጣ በመንግስት ጫና እንዳድታተም ከታገደች በሁዋላ ነው። ጋዜጠኛ ተመስገን ” የንግድ ሚኒስቴር በልእልና ጋዜጣ የቀድሞ ባለቤትና በአዲሱ ባለቤት መካከል ህገወጥ የሆነ የስም ዝውውር ተደርጓል በማለት የንግድ ፈቃዱ ” እንዲሰረዝ መደረጉን ተነግሯል።

ፍትህ ጋዜጣ በህገወጥ መንገድ እንዳይታተም ከተደረገ በሁዋላ፣ ጋዜጠኛው አዲስ ታይምስ መጽሄትን ከሌላ አሳታሚ ላይ በመግዛት ለተወሰኑ ሳምንታት ሲያሳትም ቆይቷል። መጽሄቷ በተመሳሳይ መንገድ እንድትዘጋ ከተደረገ በሁዋላ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን እንደገና ልእልና ጋዜጣን ከሌላ አሳታሚ ላይ በመግዛት ስራውን ለመስራት ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጅ ከ100 ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ የገዛው ጋዜጣ ከመንግስት በተላለፈው ጫና እንዳይታተም በድጋሜ ታግዶበታል

ተመስገን በራሱ ስም ፈቃድ አውጥቶ መስራት ከተከለከለ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ስለሚኖረው አማራጭ ሲጠየቅ፣ “ያለኝ አማራጭ ከሲቪክ ተቋማት ጋር በመተባበር ፣ ከጫካ ትግል በመለስ ያሉትን የሰላማዋ ትግል አማራጮች በመጠቀም ፣ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር መብታችንን እናስከብራለን” ብሎአል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ሰሞኑን በገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ከፍተኛ ወከባ ሲደርስበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። ተመስገን፣ ከ106 ያላነሱ ክሶችም እንዳሉበት ይታወቃል።

No comments: