Friday, April 12, 2013

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት መግለጫ አነጋጋሪ ሆኗል

ሚያዚያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር የአማራ ተወላጆችን ለመመለስ የክልላቸው ካቢኔ መወሰኑን በሚመለከት በአገር ቤት ለሚታተ...ሙ ጋዜጦች እና ለኢሳት የሰጡት መግለጫ በተለይ በአዲስአበባ ከተማ አነጋጋሪነቱን ቀጥሎአል፡፡

 “የተፈጠረ ስህተት አምኖ ይቅርታ በመጠየቅ ለማረም መንቀሳቀስ ተገቢ እርምጃ ነው” በሚል ሒደቱን አንዳንድ ምሁራን ያደነቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ “እርምጃው የጭንቅት ውጤት ነው” በማለት አጣጥለውታል፡፡

 እነዚሁ ምሁራን ለአዲስ አበባው ዘጋቢ እንደተናገሩት “በሕገወጥ መንገድ ሰፍረዋል፣ደን ጨፍጭፈዋል” በሚል ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የአንድ ብሔር ተወላጆች ብቻ ተመርጠው እንዲባረሩ የሚደረግበት መንገድ ከአፓርታይድ የዘር መድልኦ ተለይቶ የማይታይና አደገኛ ጅምር መሆኑን ጠቁመው ይህን ሁኔታ የመንግስት አመራሮች ተረድተው ስህተቱን አምነው ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት ማሳየታቸው በበጎ መልኩ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡

 በጅማ ዪኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው መንግስት የእሳት ማጥፋት ስራ በማከናወን ችግሩን ከመሰረቱ መፍታት እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ዋናው ነገር ከላይ እስከታች ያለው አመራር የፌዴሬሽን አወቃቀር ጉዳይ አጣሞ በመረዳት አንድ ክልል በራሱ ተወላጆች ብቻ መያዝ አለበት የሚል የተሳሳተ አመለካከት በሰረጸበት ሁኔታ ነገሩ ዓለም አቀፍ ቁጣ በማስከተሉ ብቻ “የተባረሩት ይመለሱ” ማለት ችግሩን ከመሰረቱ የሚፈታ እርምጃ አይሆንም ብለዋል፡፡

 በአንድ በኩል ሰዎቹን ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናቸው እየተባለ በሌላ በኩል ስህተት ተሰርቶአል ይመለሱ ማለት እርስበርሱ የተምታታና ጭንቀት የወለደው ምላሽ ይመስላል ሲሉ
አስረድተዋል፡፡

 አይይዘውም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ከደቡብ ክልል፣ከሶማሌ ክልል አማሮች እየተመረጡ ተባረዋል ያሉት ምሁሩ በነዚያ ጥፋቶች ምንም የማስተካከያ እርምጃ ሳይወሰድ ዛሬ ብድግ ተብሎ ስህተት መፈጸሙን በአደባባይ መናገሩ ብቻውን ስህተቱን አያርመውም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

 በግሌ የቤንሻንጉሉ ፕሬዚዳንት መግለጫ አሳዝኖኛል ያሉት ምሁሩ “እንዲመለሱ ተፈቅዶአል፣ተወስኗል፣…ከአማራ ክልል ጋር ተስማምተናል፣ተፈራርመናል..”ሲሉ ምን ማለታቸው ነው፡፡የሰዎችን ተዘዋውሮ የመስራት መብት በኢትዮጵያ ሕገመንግስት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጭምር ተቀባይነት ያገኘ ሆኖ ሳለ እነሱን ማን ፈቃጅ ፣ማን ከልካይ እንዳደረጋቸው የሚያስገርም ነው፡፡ አንድ በአዲስአበባ የሚኖር ዜጋ ብድግ ብሎ በቤንሻንጉል ለመኖር ቢወስን ቤንሻንጉሎች ከሰውየው ብሔር ክልል ጋር ተነጋግረው መስማማት አለባቸው እያሉን ነውን?…ትልልቆቹ አመራሮች ነገሮችን በዚህ ደረጃ የሚገነዘቡ መሆናቸው በራሱ አስደንጋጭ ነው ብለዋል፡፡

 መንግስት ከደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር የተባረሩትን የአማራ ተወላጆች በተመሳሳይ ሁኔታ ወደተፈናቀሉበት በመመለስ መልሶ የማቋቋም ተግባር መስራት ካልቻለና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮቹ ስለፌዴራሊዝም ጽንሰ ኀሳብ ማስተማር እስካልቻለ ድረስ አሁንም በዘላቂነት ችግሩ ይፈታል ብለው እንደማያምኑ የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለተፈናቀሉት ሰዎች ምንም አለማለቱ እንዳስገረው ገልጿል። “ይህ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ነው፤ ይህ ካልተዘገበ ሌላ ምን ሊዘገብ ነው?’ በማለት አክሏል።
ወጣቱ ፖለቲከኛ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ በበኩሉ የሰዎቹ መመለስ ተገቢ ቢሆንም የደረሰው ቀውስ ግን በምንም ነገር የሚተካ አለመሆኑን ገልጿል።

 “እንኳንስ ቤትን የሚያክል ነገር ቀርቶ አንድ ሰው ጓዳውንና ምኝታ ቤቱን ለመቀየር ቢነሳ ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል ” በማለት የተናገረው ኢንጂነር ዘለቀ፣ ሰዎቹ ያጡት ነገር ብዙ በመሆኑ ቢመለሱም እንኳን የደረሰባቸውን ቀውስ በቀላሉ ለመተካት አይቻልም ብሎአል።

 የፌደራል መንግስቱን ከተጠያቂነት ለማዳን የሚደረገው ጥረት ተገቢ አለመሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር በአማራ ተወላጆች ላይ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የፈጸሙት የወረዳ ባለስልጣናት ናቸው በማለት የክልሉን ባለስልጣናት እና የፌደራል መንግስቱን ከተጠያቂነት ለማዳን ያደረጉት ሙከራ በማስረጃ ላይ ያልተደገፈ ነው በማለት አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የህግ ባለሙያ ተናግረዋል።

 ባለሙያው ” በሚያዚያ ወር ውስጥ በ 2004 ዓም ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የሚፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ በወቅቱ ጠ/ሚ ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት፣ አቶ መለስ ዜናዊ የሰጡት መልስ የፌደራል መንግስት እጅ እንዳለበት የሚያመለክት ነው ብለዋል።

 የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ጉዳዩ የክልሉ ችግር ነው በማለት የሚሰጡት መልስ ተገቢ አይደለም የሚሉት ባላሙያው፣ ምናልባትም ዋናው ተጠያቂ የፌደራል መንግስቱ ሊሆን ይችላል ሲሉ አክለዋል።

No comments: