Monday, April 15, 2013

በብሄር ከፍፈሎ መግዛት የዛገ ፖሊሲ ነዉ! ግንቦት 7

Ginbot 7 weekly editorialበሀገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች የመዘዋወር፣ ንብረትን የማፍራት፣ የመኖር፣ የመናገር፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብቶች የሚወሰነው በጥቂት የህወሃትና ጀሌ ባለስልጣኖች መልካም ፈቃድ እንጅ በመሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ድንጋጌ አይደለም።

በሩዋንዳ የተፈጸመው የሰውልጅን ዘር የማጥፋት ድርጊት፣ በሀገራችንም ኢትዮጵያ በህወሃት ኢህአዴግ አማካኝነት እየታየ ነው። ዜጎች በማንነነታቸው ከየት አካባቢ/ ብሄር/ ዘር ማንዘር ነው የመጣኸው/ሽው? እዚህ ለመኖር፣ ለመስራት፣ ንብረት ለማፍራትና ለመሳሰሉት የመኖሪያ ፈቃድ አለህ/ሽ ወይ? በሚል ብሄርን ከፋፍሎ መለያ በመስጠት ተከባብሮ የኖረን ህዝብ በትውልድ ሀገሩ እርስ በርሱ ለማጋጨት እየተደረገ ያለው የዛገ የፖለቲካ ፖሊሲ የሀገራችንን ህልውና እየተፈታተነ ነው።

በብሔር ብሔረሰብ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ዘርን በማጥፋት ፖለቲካ የተጠመዱት ወያኔዎች፣ እንደ ሰደድ እሳት በአገራችን ዜጎች ላይ ያላቸውን ጥላቻ ከወዲያ ወዲህ እየሄዱ ያሳዩናል። በተለይም በአማራው የተጀመረው የበቀል ርምጃ ቀጥሎና ተባብሶ የጥፋት በትራቸው የገረፋቸው የኦጋዴን፤ የጋምቤላ፤ የደቡብ ክልል፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የዋልድባ አባቶች የቅርብ ግዜ በደሎች ሳይረሱ ከበደል ላይ በደል፣ ከጩኸት ላይ ጩኸት እየጨመረ በማን አለብኝነት የጀመረውን ዘርን የማጥፋት አባዜ ቀጥሎበታል።

የዜጎችን ሰዋዊ መብት ወያኔ በጠበንጃ ሃይል ጉልበት በመተማመን ንብረትን ቀምቶ፤ ነፍሰጡርንና አራስን አፈናቅሎ፣ ህጻናትን ሜዳ ላይ በትኖ ማባረር፣ የድብደባና የግድያ ወንጀሎች በአማራው ሕዝብ ላይ መፈጸሙ አዲስ ያልሆነና ከበፊቱም የነበረውን የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ የዛገ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረጉት እንደሆነ ያሳየ ምልክት ነው። ይህ ዓይነቱ ዘግናኝ ወንጀል በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች በተለይም በኦጋዴን፣ በአኝዋክ፣ በኦሮሞ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በሙርሲ እና በሌሎችም የማህበረሰባችን ክፍል ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጽሟል። አሁንም እየተፈጸመ ነው።

ህወሃት/ኢህአዴግ ይህንን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመበት ዋናው ምክንያት የአንድን ዘር የፓለቲካ፣ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነቱን ለማስጠበቅ ስለሆነ፤ ለዚህ እኩይ ዓላማው መሳካት እንቅፋት ናቸው ብሎ በሚገምታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ወደፊትም ተመሳሳይ እርምጃ ከመፈጸም እንደማይቆጠብ እየነገረን ነው።
ይሁን እንጅ ወያኔና አበሮቹ ይህ ዘርን የማጥራት (Ethinc Cleansing) ወንጀል ሲፈጽሙ በየትኛውም ግዜና ዘመን ከተጠያቂነት ወይም በወንጀል ከመፈለግ እንደማይድኑ የተረዱ አልመሰለንም።

የወያኔን የዘር ማጥራት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቃወመዉ እና በተለይም አማራዉ ከትውልድ ቀዪው በግዳጅ ተባሮ ለጎዳና ተዳዳሪነት ሲዳረግ የተመለከተ የአካባቢዉ ነዋሪ ህዝብ በፍጹም ወያኔን ያልደገፈና ያልተባበረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ማፈናቀሉን ተቃዉሞ ተፈናቃዮቹን እንባ እያፈሰሰ፣ ለስደት ጉዟቸው ይሆን ዘንድ ራሱ አማራው አርሶና ቆፍሮ እሸት ካፈራበት ማእድ ወይም የዛሬ የበይ ተመልካች ከሆነበት ማሳ ስንቅ እየቋጠረ ነበር የሸኛቸው።

ለብዙ አመታት አብረዉ ከመኖራቸዉ የተነሳ የአብሮ መኖር ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የገነቡና በጋብቻና በማህበራዊ ኑሮ የተሳሰሩ ዜጎች በወያኔ ፖሊሲ ምክንያት ሳይፈልጉ ሲለያዩ ማየት ምን ያህል አሳዛኝ መሆንን የኢትዮጵያ ህዝብ ይረዳል።
በሌሎች አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የስደት ሀገር የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት በፍርድ ቤት እና በተለያዩ ሚዲያዎች የመኖር መብታቸው ይከበር ዘንድ ሲከራከሩ፤ እኒህ ምስኪን የሀገራችን ዜጎች ግን በትውልድ ሀገራቸው፣ መንደራቸው የመኖሪያ ፈቃድ ተነፍጓቸው፣ ይህንንም እንዳይጠይቁ ሆነው ይባረራሉ።

ታዲያ ይህንና ሌሎች በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደሎች በጋራ ሆነን ለመታገል እንዲሁም ለአለም ድምጻችን ለማሰማት ኢትዮጵያዉያን ለብዙ ግዜ በትላልቆቹ የአገራችን ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አቅቶን ብዙ ዘመን ቆይተናል:: አሁን ግን ሌላ ቢቀር ከምን ግዜም በተሻለ ሁኔታ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በኢትዮጵያ አንድነትና በዚህ አንድነት ዉስጥ መመስረት ሳለለበት የዲሞክረሲ ስርአት የጋራ አመካከት መጥቷል።

ይህንን ኢትዮጵያዊ አንድነት የጋራ ትግልና የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት የማስጠበቅ የነጻነት ትግልን ትብብር እውን እንዲሆን ባለፈው ግዜ በከማል ገልቹ የሚመራዉ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ከሁለት አመት በፊት የወሰደዉ የአቋም ለዉጥ እና በቅርቡ ደግሞ በኦነግ ታሪክ ዉስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸዉ ሰዎች የወሰዱት ተመሳሳይ አቋም የሚያሳየዉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን በብሄር ከፋፍለህ ቅጣዉ ፖሊሲ ከኢትዮጵያ መወገድ እንዳለበት እና በሁሉም ወገናችን የሚደርሰው በደል ሰቆቃና ስደት የሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ መሆኑንና በጋራ ሆነን የዛገን የወያኔን የዘር ማጥራት ፖሊሲ የምናስቆበት፣ ለአንዴ ለመጨረሻ ግዜ ታግለን የምናስወግድበት ሰአት ላይ ነን።

በተጨማሪ ወያኔ አገራችንን በብሄር መነጽር ብቻ የሚመለከትበትን መንገድና የሚሸርበዉ ሴራ በብሄር የተደራጁ ድርጅቶችንም እያንገሸገሻቸዉ መምጣቱን፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ወያኔን የማስወገድ እና ኢትዮጵያን የማዳን የትግል ደወል ጥሪ ላይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።

ስለሆነም ግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ነጻነት ንቅናቄ በህዝባችን እየደረሰ ያለውን መፈናቀልና እልቂት ለማስቆም የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል። የዲሞክራሲ ሃይላት ድርጅቶችም ሆነ የሀገራችን ወጣቶች፤ የአማራውና የተቀረው ህዝባችን ጮኸትና ዋይታ በደልና ሰቆቃ በሁሉም የሀገራችን ህዝቦች እየደረሰ ያለ ጥቃት ነውና ለጥሪያቸው የማያዳግም መልስ ለመስጠት ትግሉን ትቀላቀሉ ዘንድ ጥሪያችን ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments: