Tuesday, April 16, 2013

ገዢው ፓርቲ ያልጠበቀውን የምር ጫ ውጤት አገኘ

ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ያለምንም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባደረገው ምርጫ ያልጠበቀውን ውጤት ማግኘቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሰባሰብናቸው መረጃዎች አመለከቱ።

ምንም እንኳ ኢህአዴግ ምርጫውን ከ99 እስከ 100 ፐርሰንት እንደሚያሸንፍ ቢጠበቅም ህዝቡ በምርጫ ካርዶች ላይ ያሰ...ፈረው መልእክት ግን ገዢው ፓርቲ ያልጠበቀውና ያለሰበው ነበር እንደ ታዛቢዎች አገላለጽ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የቀበሌ እና የወረዳ ሹሞች የምርጫ ታዛቢዎች እና የድምጽ ቆጣሪዎች የተመለከቱዋቸውን ነገሮች በሚስጢር እንዲጠብቁ ሲያግባቡዋቸው መታየታቸውን ተዛቢዎች ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ከገቡት የምርጫ ወረቀቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ባዶ ነጭ ወረቀት፣ ሌሎቹ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ ነበሩ። የሀይማኖት ነጻነታችን ይከበር፣ የታሰሩ መሪዎች ይፈቱ፣ የኑሮ ውድነቱ አስመርሮናል፣ ኢህአዴግ በቃህ ውረድ፣ ለውጥ እንፈልጋለን የሚሉት ጽሁፎች በዚህ የምርጫ ጣቢያ በብዛት ከተላለፉት መልእከቶች መካከል ይጠቀሳሉ እንደ አይን እማኞች አገላለጽ።

በሰሜን ሸዋ አጣየ ከተማ በሚገኝ አንድ ጣቢያ ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ምንም ምልክት ሳያደርግ ነጭ ወረቀት ብቻ ማስገባቱን አንድ ታዛቢ ተናግረዋል::

በአዲስ አበባ አንድ የምርጫ ጣቢያ ደግሞ ጥቂት መራጮች ብቻ ድምጽ የሰጡ ሲሆን፣ ሌሎች መራጮች ገዢውን ፓርቲ የሚሰድቡ እና ለውጥን የሚጠይቁ መልእክቶችን ማስገባታቸውን በቦታው የነበረው ታዛቢ ገልጿል::

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለከተማ ዋልያ ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረው ምርጫ ደግሞ አስመራጮች ሰው በማጣታቸውን ቁርስ እንብላ በማለት የምርጫ ጣቢያውን ዘግተው መሄዳቸውን ተከትሎ፣ በግዳጅ ለመምረት እንዲወጡ የተገደዱት ሰዎች፣ ጣቢያው ተዘግቶ በማየታቸው ወደ የቤታቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ጉዳዩን ሰምተው የመጡት የኢህአዴግ ካድሬዎች ከአስመራጮች ጋር አምባጋሮ ፈጥረው ነበር።

በአዋሳ ከተማ ደግሞ ምርጫው ከመካሄዱ ከአንድ ቀን በፊት የኢህአዴግ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የምርጫ ካርድ ያካሂዱ ነበር። በጎንደር ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ እና አደባባይ ኢየሱስ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ካርድ ሲሰጥ መዋሉን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዛሬ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

ምርጫ ቦርድ በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ 954 ወረዳዎች ፣ በተዘጋጁ 44 ሺ 509 የምርጫ ጣቢያዎች ፥ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን እጩዎችም ለውድድር ቀርበው 90 በመቶው ድምጹን መስጠቱን ገልጿል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ህብረተሰቡ በምርጫው ያሳየው ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ገልጸው ተሳትፎው ህዝቡ ስለምርጫና ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለው ግንዛቤ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳየበት ነበር ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የወጡ የምርጫ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ከ99 እስከ 100 በመቶ አሸንፎአል። በዚህ ምርጫ ገዢው ፓርቲ በ2002 ዓም ይዞት የነበረውን የ99 ነጥብ ስድስት በመቶ ውጤት ረከርድ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የተገኘውን ሪከርድ ሁሉ የሚያሻሽልና ለዘመናትም ሳይሰበር እንደሚቆይ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።



 



No comments: