July28/2014
በወርሃ-ግንቦት ላይ ለዘመናት የተንሰራፋውን ሀገራዊ ደዌ ይፈውሳል ብዬ ተስፋ ስለማደርግበት “የሕዳሴ አብዮት” በሶስት ተከታታይ ክፍሎች ለመዳሰስ መሞከሬ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መጪው የ “ሕዳሴ አብዮታችን” መፍትሔ ሊሰጥባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መሀል በዋነኝነት የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማሕበረሰብ እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የመብት ጥያቄን በተመለከተ በጥቅሉ ጠቃቅሼው አልፌ ነበር፡፡ ሆኖም ‘ሰፋ ብሎ ቢዳሰስ’ የሚሉ በተለያየ መንገድ የሚቀርቡ ጎትጓች ድምፆች መበራከታቸው የመነሻ ሃሳቡን ፈታ አድርጌ እንዳቀርብ አስገድዶኛል፤ እንግዲህ ይህ ጭብጥም የዛው ተከታይ መሆኑ ይሰመርልኝ፡፡
የኦሮሞ ጥያቄ'
በኢትዮጵያችን ከሚገኙ በርካታ ብሔሮች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ኦሮምኛ ተናጋሪው ቢሆንም፣ ለዘመናት ይደርሱበት ከነበሩ ሥርዓታዊ በደሎች እና የባሕል ጭፍለቃዎች ዛሬም በምልአት ነፃ እንዳልወጣ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ የአገሪቷ አደባባዮች የዘመኑን መንፈስ በተረዱ ቁጡ ወጣቶች መጥለቅለቁን ተከትሎ፣ ‹በንጉሣዊው አገዛዝ ግብዓተ-መሬት ላይ የመጨረሻዋን ድንጋይ ለማስቀመጥ› በሚል ሰበብ ቤተ-መንግስቱን መቆጣጠር የቻለው ወታደራዊው ደርግ፣ ህልቆ መሳፍርት በሌለው መስዋዕትነት የተገኘውን ወርቃማ ዕድል ከጅማሮው አጨናፍጎታል፡፡ በግልባጩ አብዮቱን ካጋሙት ገፊ-ምክንያቶች ዋንኞቹ ለሆኑት የብሔርና የሕዝባዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄዎች፣ መፍትሄ ይስጥ አይስጥ እስኪረጋገጥ ድረስ መታገስ ያልፈለገው ህወሓት፣ ጉዳዩ በደም መፋሰስ ብቻ እንደሚፈታ አውጆ ጫካ ሲገባ አዲሱ መንግስት ገና የ6 ወር ጨቅላ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ታሪክ በአስከፊ መልኩ ራሱን ሲደግም ያስተዋልነው ወታደራዊውን መንግስት መንፈቅ-ዓመት ያህል እንኳ መታገስ ያልፈቀደው ይህ ቡድን፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ሳይሰጥ ከሁለት አስርታት በላይ ያለመንግራገጭ በሥልጣን ለመቆየት ባለመቸገሩ ነው፤ ርግጥ የእኔ ትውልድም የእድሜውን እኩሌታ በትግስት መጠበቁ የአደባባይ እውነታ ቢሆንም፣ ተጨማሪ የቻይነት ዓመታት ይኖራሉ ብዬ ግን አላስብም፤ አብዮቱን ምኩንያዊ የሚያደርገውም ይህ ነው፡፡
…እነሆም ከአራት አስርታት በላይ ሲንከባለሉ የቆዩት የኦሮሞ ጥያቄዎች በ“ሕዳሴ አብዮት” ይፈቱ ዘንዳ፣ ሊተኩርባቸው የሚገቡ አንኳር አጀንዳዎችን በሁለት አውድ ከፍለን እንመለከታለን፡፡
፩
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጥያቄዎቹን ከወረቀት ድንጋጌ (ከአፋዊነት) እና ከፕሮፓጋንዳ ሽንገላ ባለፈ፣ እውነተኛ መፍትሔ በሚያስገኝ መልኩ እልባት ሊያበጅላቸው አልፈቀደም፤ ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ‹‹አነበርኩት›› የሚለው ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝም የይስሙላ ስለመሆኑ ለመገንዘብ፣ ዛሬም ከደርዝን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች የራስ አስተዳደር ጥያቄን አንግበው በትግል መድረክ መገኘታቸውን ማየቱ በቂ ነው፡፡ የክልሉ ‹‹ገዥ›› እንደሆነ የሚነገርለት ኦህዴድም ቢሆን፣ የህወሓቱ የአማርኛ ክንፍ እንደሆነው ብአዴን ሁሉ፣ የኦሮምኛ ክንፍ ከመሆን አለማለፉን፣ የብሔሩ ልሂቃንን ጨምሮ የፌደራል ሥርዓቱን አወቃቀር ያጠኑ በርካታ ምሁራን ማስረጃ እያጣቀሱ ያጋለጡት እውነታ ነው፡፡ ሕዝቡም በየጊዜውና በየአጋጣሚው የሚያነሳው ጥያቄ አሁንም ተግ አለማለቱ የልሂቃኑ ማስረጃ መሬት መርገጡን ያስረዳል፡፡ በቅርቡ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ስለሕጋዊነቱ በድፍረት የደሰኮረለት የማስተር ፕላኑ ጥያቄ በኃይል መጨፍለቅም በገዥው በኩል ሕገ-መንግስቱ አፈር ለብሶ እንዳበቃለት ተናግሮ አልፏል፡፡በተጓዳኝ የክልሉ ነዋሪ በተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ከመደረጉ ባሻገር፤ ከሕዝቡ ቁጥር ብዛት አኳያ ኦሮምኛ በሁለተኛ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋነት እንዲያገለግል ኦህዴድ ተፅእኖ የሚፈጥር አልሆነም፤ ሌላው ቀርቶ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ያነሱ ፖለቲከኞች ‹‹ኦነግ›› ተብለው የምድር ፍዳቸውን ሲቀበሉ የታደጋቸው የለም፡፡ የዚህ እኩይ ድርጊት ተጠያቂም ጉልበተኛው ህወሓት ብቻ ነው ማለት ገራገርነት ይመስለኛል፤ የገዛ ወገኑን አሳልፎ የሰጠው ኦህዴድም ጭምር የድርሻውን መውሰዱ አይቀሬ ነውና፡፡ ይህም ሆኖ ከአንዳንድ ምልክቶች በመነሳት ጥያቄዎቹ መልስ እስካላገኙ ድረስ፣ የቱንም ያህል የእስር ቤት ደጃፎች ከዚህም በላይ ቢጨናነቁ፣ የቱንም ያህል የእስረኞቹ ሰቆቃ እያደር ቢበረታ ከእንግዲህ በኦሮሚያ ምድር በፍርሃት ዝም-ጭጭ ብሎ የሚተኛ ሊኖር እንደማይችል ዛሬ ላይ ቆሞ መናገሩ ‹‹ሟርተኛ›› አያስብልም፡፡
፪
የኦሮምኛ ተናጋሪውን ያደረ ቅራኔ በመፍታት የአንድነት ዘብ ለማድረግ፣ የሀገሪቱ ታሪክ እና ባሕል በዳግም ብያኔ መታደሱ ግድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የክልሉ ማሕበረሰብ በዘመናዊው መንግስት ምስረታም ሆነ ከባእድ ወረራ መታደጉ ላይ ታላቅ አበርክቶ ቢኖረውም፣ በሀገሪቷ ታሪክ ውስጥ ሚናው ደብዝዞ መገለፁ ጎምዛዛ እውነት ነው፤ የቋንቋው ተናጋሪ ያልሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ይህንን አምኖ ሊያርመው ቀርቶ፣ እውቅና ሊሰጠው እንኳ አለመፍቀዱ፣ ጉዳዩን ወደሰሞነኛው ‹‹ውጡ ከሀገራችን›› አይነቱ አስደንጋጭ ኩነት ገፍቶታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በጥቂት የብሔሩ ልሂቃን የሚንፀባረቀው (ሀገርን ለፍርሰት ሊያጋልጥ የሚችለው) ሸውራራ የታሪክ አረዳድን እና የቅኝ አገዛዝ ትርክትን ማጥራት ሌላው ወሳኝ የቤት ሥራ ሆኗል፤ ምክንያቱም ከጥያቄው ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተቃውሞ ድምፆች ማጠንጠኛ ‹ባሳለፍነው መቶ ዓመት ለቅኝ አገዛዝ ተዳርገናል፣ ሥርዓታዊ በሆነ መዋቅር የሥልጣን ባይተዋር ሆነን ቆይተናል፣ ከሌላው ሕዝብም በተለየ መልኩ ከሰብአዊ ፍጡር በታች ተቆጠረን ተረግጠናል…› የሚል መንፈስ እንዲይዝ እየተለጠጠ ነው፡፡ ይህ የታሪክ ትንተና ስሁት መሆኑን የምንረዳው በየትኛውም መንግስታዊ ሥልጣን ጊዜ (ሀገሪቱ በጦር መሪዎችም ሆነ በነገሥታቱ ጠንካራ መዳፍ ስር በተያዘችበት ዘመን) በግንባር ቀደምትነት በመንበሩ ላይ ይፈራረቁ ከነበሩት አማርኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች የማይተናነስ እኩል ሚና እንደነበራቸው የቋንቋው ተናጋሪ ምሁራን በማስረጃ አስደግፈው ባዘጋጇቸው ድርሳኖቻቸው ያተቱትን ስናስተውል ነው፡፡
ለማሳያም ‹‹የጎንደር ዘመን›› ተብሎ ከሚጠቀሰው (እ.ኤ.አ ከ1636-1769 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው) ማዕከላዊ መንግስት ውድቀት በኋላ የተተካውና ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› እየተባለ የሚጠራው አገራዊ የአስተዳደር ዘይቤ ጠንሳሽና ተግባሪ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ የመንግስቱ መቀመጫ ከሰሜን ጎንደር ወደ ደብረታቦር የተዘዋወረ ሲሆን፣ የግዛት ወሰኑ ደግሞ ጎንደርን፣ ወሎን፣ ጎጃምን፣ ከፊል ሸዋንና ትግራይን የሚያካትት እንደነበር መዛግብቱ ያወሳሉ፡፡ በዘመኑ ሥልጣኑን የጠቀለሉትና ‹‹የጁ (ወራ-ሼክ) ስርወ-መንግስት›› በሚል ስም የሚጠሩት የአሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ የብሔሩ ምሁራን ነግረውናል፡፡ እያገባደድነው ባለው በዚህ ዓመት ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች›› በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ያሳተሙት ታቦር ዋሚ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ዘገባዎች አላግባብ ዘመነ መሳፍንት ሲባል የቆየው
የየጁ ዘመንና ታሪካዊ ሚና›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር በርካታ መጽሐፍትና የጥናት ጽሑፎችን በመጥቀስ ሥልጣኑ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እጅ እንደነበረ በስፋት አብራርተዋል፡፡ ታቦር በትርክታቸው ‹‹የጁ ከሰሜን ኢትዮጵያ የኦሮሞ ነገዶች አንዱ እንደሆነና ቀስ በቀስም ይህ ስም የጎሳው ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ የሰፈረበት አካባቢ ጭምር መጠሪያ እንደሆነ በርካታ ጸሐፍት ይመሰክራሉ›› (ገፅ 287) ሲሉ በአባሪ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ ሥርወ-መንግስቱ በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜያትንም ‹‹ከጎንደር ዘመነ-መንግስት ማብቂያ እስከ አፄ ቴዎድሮስ መነሳት ድረስ የነበሩትን ዓመታት ሁሉ ያካትታል›› (ገፅ 293) በማለት ገልፀውታል፤ ይህንን በአሃዝ እናስቀምጠው ብንል ደግሞ ወደ 86 ዓመት ገደማ ልንቆጥር እንገደዳለን፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ እሸቱ ኢረና ዲባባም መከራከሪያውን እንዲህ ሲሉ ያጠናክሩታል፡-
‹‹ጎንደር የሃበሻ መንግስት (አቢሲኒያ)ማዕከል በነበረችበት ወቅት የኦሮሞ ህዝብ በአካባቢው ሰፍሮ ይኖር እንደነበረና ወሳኝ ሚና ለረጅም ጊዜ ነበረው፤ እ.ኤ.አ. ከ1853-1854 በጎንደር በእስር ላይ የነበረው ጀርመናዊ ሰዓሊ በሰራቸው ምስሎች ኦሮሞ በወቅቱ በአካባቢው ገዢ እንደነበር እርሱም ከአካባቢው ኦሮሞ ሴት እንዳገባ፤ ምስልዋንም ሰርቶ እነዚህ የስዕል ስራዎቹ እ.ኤ.አ. በ1868 ዓ.ም በለንደን ከተማ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጥቶ ይገኛል፡፡ በአካባቢው ሰፍረው ይኖሩ ከነበሩት የኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ የቦረና ኦሮሞ አንዱ መሆኑን ኤች ሙሬይ በ1830ዎቹ ባሳተመው ጽሑፍ ውስጥ ከጠቀሰ በኋላ ኦሮሞ እንደ ሕዝብ በደንቢያ በጎጃም፣ በዳሞትና በአንጎት አካባቢዎች ሰፍሮ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡›› (ገፅ 83-84)
ራሱ የክልሉ መንግስትም፣ በባሕልና ቱሪዝም ቢሮው በኩል
‹‹የኦሮሞ ታሪክ እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ‹‹…‹ወራ- ሼክ› የሚለው የቤተሰቡ መጠሪያ በየጁ ኦሮሞዎች ዘንድ ታላቅ ዝና ከማግኘቱም በላይ በአጠቃላይ የየጁ ኦሮሞዎች ቀደምት መንግስት መነሻ ወይም አባት ተደርጎ እስከመቆጠር ደረሰ ይባላል›› (ገፅ 281) ሲል ገልጿል፡፡
በግልባጩ የአፄ ምኒሊክ ፈረስ ሐረርና አርሲ መርገጡን ‹‹የቅኝ-ግዛት ወረራ›› አድርገው የሚያቀርቡ ዘመነኛ ‹‹ፖለቲከኞች››፣ ይህ አይነቱን ጥሬ ሀቅ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት አይፈቅዱም፡፡ የጠቀስኳቸው ድርሳናትም የሚነግሩን ኦሮሞ ከሌላው ብሔር ጋር ትንቅንቅ ገጥሞ በለስ ቀንቶት ድል ባደረገ ቁጥር መንግስታዊ ሥልጣን መጠቅለሉን ብቻ አይደለም፤ በሀገሪቱ ታሪክ ጭቆና እንጂ ቅኝ አገዛዝ የሚባል ነገር አለመኖሩንም ጭምር ነው፡፡ ከኤርትራ እስከ ሞያሌ፤ ከጋምቤላ እስከ ሶማሌ በተዘረጋው ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በተደጋጋሚ ከተቃጡ የባዕዳን ወረራዎች በቀር፣ ቅኝ-ገዢም ሆነ ቅኝ-ተገዢዎች ስለመኖራቸው የሚያትት አንድም የታሪክ መረጃ ተፈልጎ ታጥቷል፡፡ መቼም ‹‹ድሮ ነፃ ሀገር ነበረን›› በሚል ዛሬ ላይ የመገንጠልን ጥያቄ ሲያነሱ፤ አሊያም አንድ ብሔርን በነፍጠኛነትና በወራሪነት ሲኮንኑ የምናደምጣቸው ጠርዘኛ ልሂቃን ‹የኦሮሚያ የግዛት ወሰን ጎንደርን እና ትግራይን ያጠቃልል ነበር› ስለማለታቸው ሰምተን አናውቅም፡፡ መቀመጫውን ደብረታቦር ላይ አድርጎ ከትግራይ እስከ ሸዋ ያስተዳድር የነበረ ሥርወ-መንግስት፣ የበለጠ ጉልበተኛ ተነስቶበት፣ በተራው ከመንበሩ በኃይል ሲገለበጥ ቅኝ-አገዛዝና ኢ-ሰብአዊ ብሎ ለመኮነን መሞከሩ ውሃ የሚያነሳ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ጋ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ፣ በተለይም ከአፄ ምኒሊክ መንገሥ ወዲህ የኦሮሞ ማሕበረሰብ ቋንቋውን ጨምሮ የባሕል እሴቶቹ ተውጠው፣ የአገሪቱ ወካይ እንዳይሆኑ መጨፍለቃቸውን ነው፤ እንደምሳሌም የገዳ ሥርዓት ምንም እንኳ ሁሉንም የቋንቋው ተናጋሪ ያቀፈ ባይሆንም (የ‹‹ጊቤ ግዛት›› ተብለው የሚታወቁት፡- ጅማ፣ ሊሙ፣ ጎማ፣ ጉማ እና ጌራ ከገዳ ይልቅ በንጉሣዊ ሥርዓት ሲተዳደሩ፤ ወለጋና ኢሊባቡርን የመሳሰሉ አካባቢዎችም በ‹‹ሞቲ›› ይመሩ ስለነበር) የአክሱም ሐውልትን ወይም የጎንደር ግንብን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቦታ አለማግኘቱ አይካድም፡፡ እንዲሁም በሌላ ቋንቋ ተናጋሪው ዘንድ ‹‹ጣኦት ማምለክ›› ተደርጎ የሚቆጠረው የኢሬቻ ክብረ-በዓል አረዳድ ስሁት ስለመሆኑ ቢረፍድም የመስከሩ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ይህ የምስጋና ሥነ-ስርዓት በአገሪቱ ታሪክ ተገቢውን የክብር ስፍራ ሳያገኝ መገፋቱን በማመን፣ ሚዛንን ማስተካከል ግድ ይላል፡፡ በጥቅሉ ምግቡ፣ አለባበሱ፣ ሙዚቃውና መሰል እሴቶቹ በትልቁ የታሪካችን ገፅ በበቂ ደረጃ አለመወከላቸውን ዛሬም ለማድበስበስ መሞከሩ መፍትሔውን ከማራቅ፤ አሊያም ልዩነትን ከማስፋት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ መቼም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ቡድኖች መኖራቸው ደብቀን የምናስቀረው ሚስጥር አይደለም፤ ከኦሮሚያ እስኪ ኦጋዴን፤ ከጋምቤላ እስከ ቤንሻንጉል ድረስ ይህን ለማስፈፀም የሚተጉ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋልና፡፡ በርግጥ እነዚህ ኃይሎች የቆሙበት መሰረት ማሕበረሰቡን የሚወክል ነው ወይስ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ብቻ የሚያረካ? የሚለው ገና ያልጠራ፣ አሁንም አጥጋቢ መልስ ያላገኘ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፖለቲካዊው ፍላጎት ማሕበራዊ ውሉን የዋጠው ይመስላል፡፡
ኤርትራን ያጣንበት ምክንያትም ከዚህ ብዙም እንደማይርቅ ጥርጥር የለውም፡፡ አሁንም የዚህን ጥያቄ ውል ከሳትን ሌላ የምናጣው ክፍለ-አካል መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም ነው በ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› እንደ አዲስ በምትገነባው ኢትዮጵያችን ጥያቄዎቹ በቀዳሚነት ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብዬ የምከራከረው፡፡ በለውጡም፣ እነዚህ ጎታች የፖለቲካ አቋሞች እና አቀንቃኞቹ ዘላቂ መፍትሔ አግኝተው የአንድነት ዘመን አብሳሪ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡
በተቀረ በኦሮሞ ላይ አንድ ብሔር በተለየ መልኩ በደል አድርሷል፣ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፅሟል… መሰል ትርክቶች ጭራና ቀንድ ተሰክቶባቸው ግብረ-ሂትለርና ፋሽስታዊ ድርጊቶች ተመስለው የሚቀርቡበት አውድ ከተራ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት ያለፈ፣ በዕውን ለመፈፀማቸው ምንም አይነት የታሪክ ሰነድ አልተገኘም፡፡ ከጥቂት ሳምንት ቀደም ብሎ በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ከታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ስንወያይ ‹‹ወደ አኖሌ (አርሲ) ከዘመተው የአፄ ምኒሊክ ሠራዊት መካከል አብላጫው ኦሮሞ ነው›› ሲሉ መግለፃቸውም፣ ከዶ/ሩ የትምህርት ደረጃ፣ ከረዥም ዓመት የሥራ ልምዳቸው እና ከቋንቋው ተናጋሪ አብራክ የተገኙ ከመሆናቸው አኳያ ችግሩን ወደ አንድ ብሔር ማላከኩ ስህተትለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ ታቦር ዋሚም ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፍ (ከገፅ 275-278) ከአማራው ነገስታቶች ጋር ጋብቻ የፈፀሙ ኦሮሞ ንጉስና ንግስት በማለት በስዕላዊ መግለጫ አስደግፈው ያቀረቡት የቋንቋው ተናጋሪ ንጉሦችና ነገስታት ስም ዝርዝር እንደተጨማሪ ማስረጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ጸሐፊው ለማሳያነት ከጠቀሷቸው ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ-እቴጌ ተዋበች፣ የአፄ ምኒሊክ-ጣይቱ ብጡል፣ የንግስት ዘውዲቱ-ወሌ ብጡል፣ የአፄ ኃይለስላሴ-እቴጌ መነን፣ የምኒልክን እህት ያገቡት-ንጉስ ሚካኤል… የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት እንደነበሩ አትተዋል፡፡ ከዚሁ ጋርም አያይዘው በተለያየ ጊዜ በሀገሪቷ የተከሰቱት የኃይል ግጭቶች አሰላለፍ በብሔር ከመቧደን ይልቅ፣ በሥልጣንና በጥቅመኝነት ላይ የተመሰረቱ እንደነበረ ፈራ-ተባ እያሉም ቢሆን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡- ‹‹በጣም የሚገርመው ከሣህለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ድረስ በኦሮሞው ላይ ሲካሄዱ ለነበሩት ዘመቻዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከነገሥታቶቹ ጋር ጊዜያዊና ዘላቂ ዝምድና የፈጠሩ እራሳቸው ኦሮሞዎች መሆናቸው ነው፡፡ …(ራስ ጎበና) እኚህ የኦሮሞ መስፍን የታወቁ ፈረሰኛ፣ ጀግና፣ ተዋጊና ወታደራዊ ስትራቴጂስት ከመሆናቸው በላይ በኦሮሞ የውጊያ ስልትና በኦሮሞ ሥነ-ልቡና ላይ የጠለቀ እውቀት ነበራቸው፡፡
ይህንን ብቃት ሙሉ በሙሉ ለምኒሊክ አገልግሎት አውለውታል፡፡ ከሁሉም በፊት ምኒልክ ሳይሆኑ የኦሮሞን ግዛት ያሸነፉት ራስ ጎበና ነበሩ፡፡›› (ገፅ 499-500 እና 503)፡፡ ይህን መሰሉ የኃይል ትንቅንቅ ከአርሲና ባሌ በፊት ቤጌምድርና ትግራይ ውስጥ በተከሰተበት ወቅት ኦሮምኛ ተናጋሪው በአሸናፊነት በመውጣቱ ለ86 ዓመት ያህል ሥልጣን ይዞ መቆየቱን ከላይ አይተናል፡፡ መቼም የጁዎች፣ ጎንደሮችን ድል አድርገው ሥርወ-መንግስታቸውን ደብረ ታቦር ላይ የመሰረቱት በምርጫ ካርድ (ያለነፍጥ) ነበር ካልተባለ በቀር፣ አንዱን ወገን ለይቶ በሂትለርነት መኮነኑ ፍትሃዊ ካለመሆኑም ባለፈ፤ የሚጠቅመው ከመከራ ነፃ እንዲወጣ የምንዋትትለትን ሕዝብ ሳይሆን፣ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ነው፡፡
በተጨማሪም በራሱ በቋንቋው ተናጋሪዎች ብቻ ከተዘጋጁ ድርሳናት የጠቀስኳቸው እነዚህ ሁነቶች፣ በማስረጃ ያልተደገፈውን (አፈ-ታሪኩን) የአኖሌ ጡት ቆረጣ ትርክት ተአማኒነት ያሳጡታል፡፡ ከዚህ ባለፈ የተሸነፈ ሠራዊትን እጅ-እግር መቁረጥ ምኒሊክም ሆኑ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ገዥዎች ይፈፅሙት የነበረ ጭካኔ መሆኑ አይስተባበልም፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ፣ በሸዋ ላይ ሾመውት የነበረው የምኒሊክ አጎት አቤቶ ሠይፈ ‹‹ሸፍቶብኛል›› በሚል አንኮበር ድረስ መጥተው ወግተው ድል ካደረጉት በኋላ ሠራዊቱ በሙሉ አንድ እጅና አንድ እግሩ እንዲቆረጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ፡- “አፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ”ተብሎ መገጠሙ የጉዳዩን እውነታነት ለማሳየት በቂ ነው፡፡ (የእስልምና እምነት እና የኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ጥያቄዎች፣ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የሚኖራቸውን የመፍትሔ ሃሳብ በተመለከተ ሳምንት እመለስበታለሁ)