Saturday, May 3, 2014

በዝዋይ የሚገኙ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መልዕክት አስተላለፉ፤ (የረሃብ አድማ መምታት ጀምረዋል)

May 2/2014
በዝዋይ የሚገኙ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥያቄያቸው እንዲመለስ ጫና ለመፍጠር የምግብ ማቆም አድማ ጀመሩ። አድማው ለ3 ቀን እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ ጥያቄያቸውም፡-

1ኛ፦ የፖለቲካው ሥነ -ምህዳር እንዲሰፋና የፓርቲዎች በነፃነት የመንቀሳቀስና የመደራጀት መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር፣

2ኛ፦ አፋኝ የሆኑት የመያዶች ህግ፣ የፀረ-ሽብር ህግ፣ የፕሬስ ህግ እንዲሻሩና ነፃ የሙያ ማህበራት ላይ የሚደረገው አፈና እንዲቀም፣

3ኛ፦ በግሉ ሚዲያ ላይ የሚደረገው ማስፈራሪትና አፈና በአስቸኳይ እንዲቆምና የፕሬስ ነፃነት ሳይሸራረፍ እንዲከበር፣

4ኛ፦ የመከላከያ፣ የፖሊስና የደህንነት አካላት በህገ መንግሥቱ መሠረት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በገለልተኝነት እንዲወጡ፣

5ኛ፦ ፍርድ ቤቶች፣ የምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ ሚዲያው ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲዋቀር፣

6ኛ፦ የፖለቲካ እስረኞች፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የህዝበ ሙስሊሙ ተወካዮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣

7ኛ፦ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ እስር ቤቶችን በተመለከተ፡-

ሀ) የሰብአዊ መብት ጥሰትን የፈፀሙ ማለትም በድብደባ አካል ያጎደሉና በድብደባ የሰው ህይወት ያሳለፉ የተቋሙ አባላት ህግ ፊት እንዲቀርቡ፣

ለ) በደረቅ ወንጀል ለታሰሩ እስረኞች የሚደረግ ዝውውር፣ ይቅርታ፣ ምህረት እና አመክሮ ህግ በሚፈቅደውና መድሎ በሌለበት ሁኔታ እንዲፈፀም፣

ሐ) በሁሉም እስር ቤቶች ውስጥ ‹‹ጨለማ ቤት›› በመባል በሚጠሩት የብቻ እስር ቤቶች ውስጥ የታሰሩ እስረኞች ከጨለማ ቤቶቹ ወጥተው ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዲቀላቀሉ።

መ) የምግብ፣ የውሃ፣ የአልባሳት፣ የግል ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦት በአስቸኳይ እንዲሻሻል እንዲሁም እስረኞች ከሚጎበኟቸው ሰዎች በወር የሚፈቀድላቸው 1ዐዐ ብር በቂ ባለመሆኑ ክልከላው እንዲነሳ፣ የመረጃ በነፃነት የማግኘት መብታችን እንዲከበር (ሬድዩ የማዳመጥና የግሉ ሚዲያ ውጤቶች የሆኑ ጋዜጦች እንዲገቡልን) የርቀት ትምህርት መማር እንዲፈቀድ፣ ከውጭ የሚላኩልንን ፖስታዎች በአግባቡ እንዲደርሱን።

8ኛ፦ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ላይ በተደነገገው መሠረት በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ድብደባና አካል ማጉደል ወንጀል መሆኑን በመፃረር በሀገሪቱ ያሉ የምርመራ ጣቢያዎች በተለይም በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ (ማእከላዊ) ውስጥ ይህንን ወንጀል የፈፀሙና እየፈፀሙ ያሉ የፖሊስና የደህንነት አባላት ለፍርድ እንዲቀርቡ።

9ኛ፦ በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምስቅልቅል በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥትና ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ መግባባትና እርቅ እንዲያወርዱ። በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ በአግባቡ በመረዳት ልዩነትንና ህልውናን ጠብቆ ለጋራ የነፃነት አጀንዳ በጋራ ተባብሮ መታገል የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ በመሆኑ የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ተባብረው እንዲታገሉና የኢትዮጵያ ህዝብም ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን። በመጨረሻም ከዚህ በላይ በዝርዝር ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ ያገኙ ዘንድ ለጊዜው ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረው የፖለቲካ እስረኞች ከአርብ ሚያዚያ 24 ቀን እስከ እሁድ ሚያዚያ 26 ቀን የሚቆይ የ3 ቀን የረሃብ አድማ አድርገናል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
1ኛ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር
2ኛ አቶ ደረጀ አበበ
3ኛ አቶ ናትናኤል መኮንን
4ኛ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)
5ኛ አቶ አንዷለም አያሌው
6ኛ ሻ/ል የሽዋስ ይሁንአለም
7ኛ አቶ ምትኩ ዳምጤ
8ኛ አቶ አበበ መልኬ
9ኛ አቶ ማንደፍሮ አካልነው
1ዐኛ አቶ ገበየሁ ብዙነህ
11ኛ አቶ ዩሐንስ ተረፈ
12ኛ አቶ መሠለ ድንቁ
13ኛ አቶ ፍቃዱ ባሳዝን
14ኛ አቶ የገባው አለሙ
15ኛ አቶ እሱባለው አሌ
16ኛ አቶ ጥላሁን ባለው
17ኛ አቶ አስቻለው አራጋው
18ኛ አቶ በእውቀት ደሳለኝ
19ኛ አቶ ካሳሁን ጌጡ

ግልባጭ
- ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ
- ለተባበሩት መንገሥታት ድረጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
- ለአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
- ለአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መ/ቤት
- ለአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብት ኮሚች
- ለ Human Rights watch
- ለ Amnesty international
- ለ CPJ እና ለሀገር ውስጥና ለውጭ የሚዲያ ተቋማት በሙሉ፡፡

No comments: