Wednesday, May 7, 2014

“የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሐዊና ሕጋዊ ነው”

May 7/2014
ሰንደቅ ጋዜጣ
አቶ አባዱላ ገመዳ
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔ
በአዲስአበባዙሪያያሉትንበኦሮሚያክልላዊመንግስትውስጥየሚተዳደሩከተሞችንከአዲስአበባጋርበማስተሳሰርበጋራለማልማትየወጣውንየተቀናጀመሪዕቅድ በመቃወም ሰሞኑን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄደው ተቃውሞ ተከትሎ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በጅማ፣ በመደወላቡ፣ በአምቦ፣ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎችና በጠቅላላው በ11 ዩኒቨርሲቲዎች የተቀጣጠለው ተቃውሞ መነሻው የአዲስአበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ትግበራ ጉዳይ ነው። ዕቅዱ “የኦሮሚያ ከተሞችን በመቁረስ ወደአዲስአበባ ለማጠቃለል የታቀደ ነው፣ በርካታ ኦሮሞዎች ከቤት ንብረታቸው ሊፈናቀሉ ነው” የሚሉ አስተያየቶች በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት በመሰራጨታቸው ተማሪዎች ግራ በመጋባት የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ይታመናል። መንግሥታዊ አካላትም በወቅቱ ሕዝቡን በማሳተፍ ስለፕላኑ (ዕቅዱ) በቂና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን አለማድረጋቸው ለግጭቱ መነሳት አንድ ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው።
የመንግሥት ኮምኒኬሸን ጽ/ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በመደወላቡ እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 10 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ እግርኳስ በመመልከት ላይ ባሉ ተማሪዎች ላይ ባልታወቁ ሰዎች በተወረወረ ፈንጂ 70 ያህል ተማሪዎች ሲቆስሉ አንድ ተማሪ መሞቱን አስታውቋል።
ጽ/ቤቱ በዚሁ የመንግሥትም አቋም በገለጸበት መግለጫው በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ኃይሎች ትብብር ሁከቱ በተፈጠረባቸው ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት መቻሉን ጠቅሶ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ከበስተጀርባ በመሆን ሁከቱን በማነሳሳትና በማቀነባበር ተግባር ላይ የተሰማሩት ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ብሏል። ከዚሁ ግርግር በስተጀርባ የቆሙትና ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች እጃቸውን ሲያስገቡ የነበሩ የአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ኃይሎች በሚቆጧጠሯቸው ሚዲያዎች እየታገዙ ይህንን የተማሪዎችን ጥያቄ ለጥፋት ዓላማቸው መጠቀሚያ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸውና ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው መንግስት የተሰማውን ሐዘን የገለጸ ሲሆን የጥፋቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የነበሩትን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የሚተዳደሩ ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር በማስተሳሰር በጋራ ለማልማት የወጣውን የተቀናጀ መሪ ዕቅድ ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ስለተነሳው ጥያቄና በመንግሥት ስለተወሰደው እርምጃ የአሜሪካ ድምጽ አማርኛ ክፍል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔ የሆኑትን አቶ አባዱላ ገመዳን ከትላንት በስቲያ አነጋግሯል። እንደሚከተለው ቀርቧል።
ጥያቄ፡- ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ሰልፉ የተካሄደው ባልታጠቁ ተማሪዎች ነው። በሮቤ፣ በአምቦ፣ በጅማ፣ በነቀምት፣ በመዳወላቡ፣ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። መንግሥትም ራሱ ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ እስከ 10 ሰዎች መገደላቸውን አምኗል፣ በዚህ ላይ የሚሰጡን ምላሽ ምንድነው?
አቶ አባዱላ፡- እውነት ነው፤ በኦሮሚያ ክልል ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች የተነሳ የተቃውሞ ጥያቄ አለ። ጥያቄው የተነሳው በኦሮሚያና የአዲስ አበባ የጋራ ማስተር ፕላን በሚመለከት የተነሳ የተቃውሞ ጥያቄ ነው። በሁሉም አካባቢ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ ፍትሃዊና ሕጋዊ ነው። እነዚህን ፍትሃዊና ሕጋዊ ጥያቄ በየአካባቢው ያሉት፣ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደርም ሆነ በየአካባቢው ያሉት አስተዳደሮች ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ጉዳዩን በቅርበት ይከታተሉ የነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎችም በጉዳዩ ሒደት ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረዋል። ይሁንና አንዳንድ ቦታ ተማሪዎቹ ጠየቁ፣ በቂ መልስ አላገኘንም አሉ። ለበላይ አካልም ጥያቄያቸው እንዲሄድላቸው ጠየቁ፣ ግን ደግሞ ያ-ምላሽ ከመምጣቱ በፊት ነው ሰልፍ ወጡ። እንግዲህ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው። ይህ በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠ ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሠላማዊ ሰልፍ ሲወጣ አስቀድሞ ማሳወቅ እንደሚገባ ይደነግጋል። ይሄ የሚሆነው በአካባቢው ያለ የመንግሥት አስተዳደር ሰልፍ የወጣው ሕዝብ አንድም ጉዳት እንዳይደርስበት ለመከላከል ነው። ሁለተኛ ደግሞ በሌላው ዜጋ ንብረትና ሐብት ጉዳት እንዳይደርስ ለመጠበቅ ነው። እነዚህ ሁለቱ ካልተሟሉ ችግር ሊከሰት እንደሚችል በአገራችንም በሌሎች ዴሞክራሲያዊና ባደጉ አገራትም ይታወቃል። መጀመሪያ ተማሪዎቹ ጥያቄያቸው ፍትሐዊ ሆኖ ሠላማዊ ሰልፉ ሕጉን ተከትሎ ያለማካሄድ ችግር ያጋጠመበትና ሳያሳውቁ በኃይል ስለተወጣ ከተማ ላይ በንብረት ላይ የደረሰ ኪሣራ አለ። ይሄ ወደባሰ ችግር እንዳይሰፋ የፀጥታ ኃይሎች ለመከላከል የወሰዱት እርምጃ አለ። የፀጥታ ኃይሎች አድማ ለመበተን ጢስ እና ውሃ ተጠቅመዋል። ይህን አልፎ ለሕይወት መጥፋትና ለሌሎችም ችግሮች የተከሰቱበት ሁኔታ አለ።
ጥያቄ፡- የተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሐዊና ሕጋዊ ነው ብለዋል። ሠላማዊ ሰልፍ ደግሞ በሕገመንግሥቱ የተቀመጠ መብት ነው ብለዋል። ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ የሚፈልግ ለመንግሥት አካላት ማሳወቅ ነው ብለዋል። ነገር ግን የታጠቁ ኃይሎች ልጆቹ ላይ ተኩስ እንደከፈቱና በዚህም ምክንያት የማይተካ ሕይወት እንደተሰዋ ነው የሚነገረው። ጥያቄያቸው ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ ለዚህ ግድያ ምን መልስ ይሰጡናል?
አቶ አባዱላ፡- በመጀመሪያ ይህ መምጣት የሌለበት ነው። ሕይወትም ንብረትም መጥፋት በጣም የሚያሳዝን ነው። መንግሥትም ሐዘኑን ገልጿል። እኔም በቦታው ደርሼ አይቻለሁ፣ አዝኛለሁ። መሆን የማይገባው ጉዳይ ነው። በቦታው በኃይል ለመመለስ ወይም በጥይት ለመመለስ አይደለም ዝግጅቱ። አንድ ምሳሌ ለማንሳት ልሞክር። የአድማ በታኝ የፌዴራል ፖሊስ በቦታው የደረሰው ብዙ ተሽከርካሪዎችና ንብረት ከተቃጠለ በኋላ ማታ ላይ ነው። ማምሻውን 11 ሰዓትና ከዚያ በኋላ ነው የደረሰው። ቃጠሎው እየሰፋ ሲሄድ ነው፣ የክልሉ መንግሥት ይሄ ነገር የከፋ ሕይወት ሊያጠፋ ስለሚችል የሚቆጣጠር ኃይል መግባት አለበት ብሎ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል።
ጥያቄ፡- ተማሪዎቹ መኪናዎችን ሲያቃጥሉ ነበር ነው የሚሉኝ?
አቶ አባዱላ፡- እንግዲህ በአምቦ ከተማ ቀደም ሲል ሠላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ማሳወቅ ይገባል ያልነው ባመፈፀሙ፣ ቅድመ ዝግጅት ባለመደረጉ፣ ተማሪዎቹ በግቢያቸው ውስጥ የመጨረሻውን ዝግጅት አድርገው የወጡ ቢሆንም፤ ከውጪ ግን ተማሪዎችን የተቀላቀለ ብዙ ኃይል አለ። የዘረፋ ፍላጎት ያለው፣ የማውደም ፍላጎት ያለው ኃይል ተቀላቅሏል። ከተቀላቀለ በኋላ ለምሳሌ በአምቦ አበበች መታፈሪያ የሚባል ሆቴል ተዘርፏል። ሆቴል ውስጥ የነበሩት የቱሪሰት መኪናዎች ተቃጥለዋል። እንደዚህም የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ተቃጥሏል። የምዕራብ ሸዋ ፍ/ቤት ዶክመንቶችና ፍ/ቤቱ ራሱ ተቃጥሏል። እንዲያውም ተማሪዎች ናቸው ለማለት የማያስችለው ከጥበቃ ኃይሎች ትጥቅ በመቀበል ወደተኩስ የተገባበት ሁኔታ ነበር። ይሄ ነገር ሄዶ ሄዶ ብዙ ሕይወት፣ ብዙ ንብረት እንደሚያወድም ይታወቃል። መንግሥት ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት።

No comments: