Monday, May 26, 2014

ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የመሰከሩ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ተፈጸመባቸው።

May 26/2014
ምንሊክ ሳልሳዊ

የአወሊያ ትምህርት ቤት ኮሌጅና ሀይ ስኩል መምህራኖች ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ያነሱት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን ከአመፅ ጋር በማያያዝ ለኮሚቴዎቹ በመሰከሩ መምህራኖች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ተገለፀ ።
FITH RADIO [ፍትህ ሬዲዮ]
ከኑሮው ውድነት ጋር ተያይዞ የሚከፈላቸው ደመወዝ ከእጅ ወደ አፍ የሆነባቸው የአወሊያ ትምህርት ቤት መምህራን ግንቦት 4\2006 በአወሊያ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በመሰባሰብ የአወሊያ ትምህርት ቤት አስተዳደር እስከዛሬ በሰሩት ስራና ውጤት ፍትሃዊ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው መጠየቀቸው የሚታወስ ነው ፡፡
መምህራኖቹ ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ይህን ጥያቄ በሰላማ መንገድ ሲጠይቁ ትምህርት ቤቱ ከቻለጥያቄያቸውን ሰምቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው ካልሆነ ደግሞ መጪው የትምህርት ዘመን ከመድረሱ በፊት የተሻለ ነው የሚሉትን አማራጭ ለመወሰን እንዲያመቻቸው ፈጣን ምላሽ መጠየቃቸው እየታወቀ የመንግስት ደህንንቶችና የፀጥታ ሰዎች ግን ሂደቱን የመምህራን አመፅ አስመስለው በማቅረብ አንዳንድ መምህራንን እያሸማቀቁና እያስፈራሩ መሆኑን ምንጮች ለፍትህ ሬዲዮ ገልፀዋል ፡፡
ከ 5 እስከ 30 አመታት ባገለገልንበት ተቋም እየተከፈለን ያለው ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ አስተዳደሩ ማሻሻያ ያድርግልን የሚል ጥያቄ ከማንሳታቸው በቀር አንድም ማስፈራሪያ እንዳልሰነዘሩ በወቅቱ ተሰብስበው በነበረ ጊዜ የያዙት ቃለ ጉባኤ አስርጂ እንደሆነ የፍትህ ሬዲዮ ምንጮች ጠቁመዋል ፡፡ በቅርቡ በፍርድ ቤት ተገኝተው ለኮሚቴዎቻችን የመከላከያ ምስክር የነበሩ መምህራኖችን ታርጌት ያደረገ የሚመስለው ይህ ማስፈራሪያ ሆን ተብሎ በመንግስት የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ ተገልፇል ፡፡ ይህን የመምህራኖች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ አስተዳደሩ ፍትሃዊና ሰላማዊ መሆኑን ቢያምንበትም አንዳንድ የመንግስት ሃላፊዎች ግን የትምህርት ቤቱን አስተዳደር መምህራኖቹ እንደረበሹ አስመሰለው ክስ እንዲያቀርቡ በመጎትጎት በስብሰባው ላይ የተሳተፉትንና ለኮሚቴቻችን መከላከያ ምስክርነት የቀረቡትን መምህራኖች ለማሸማቀቅ እየተሞከረ ለመሆኑ ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለፍትህ ሬዲዮ አጋልጠዋል ፡፡

No comments: