Sunday, May 11, 2014

የኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች በማስተር ፕላኑ የተነሳውን ተቃውሞ ለማርገብ ተጠምደዋል

May 11/2014

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሞ ተወላጅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቀስቅሶ የተስፋፋውን ተቋውሞ ለማርገብ ያለፈውን ሳምንት በሥራ ተጠምደው አሳልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ለሕዝብ ውይይት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የኦሮሞ ተወላጆች የቀሰቀሱት ተቃውሞ፣ በተለይ በአምቦ ከተማና አካባቢው ተዛምቶ ሕይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተቃውሞው የቀዘቀዘ ቢሆንም፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ ሙሉ በሙሉ ትምህርት ማስቀጠል አለመቻሉን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተለይ ችግሩ በተከሰተባቸው የአምቦና አካባቢው እንዲሁም በባሌና በወለጋ አካባቢ ከፍተኛ የኦሕዴድ አመራሮች የአካባቢውን የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሰብስበው ሲያነጋገሩ ሰንብተዋል፡፡ ከፍተኛ ግጭትና ተቃውሞ በተስተዋለበት የአምቦ ከተማና አካባቢው በመገኘት ኅብረተሰቡን ለማወያየት የተጓዙት የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው፡፡

የኦሕዴድ መካከለኛ አመራር የሆኑ የዞን አመራሮች ደግሞ በሰበታ፣ በሆለታ፣ በቡራዩና በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ውይይቶችን ከኅብረተሰቡ ጋር ተገናኝተው ሲያካሂዱ ሰንብተዋል፡፡

በሁሉም ውይይቶች ላይ እየተነሳ ያለው ማስተር ፕላኑ በጭራሽ የኦሮሚያ ክልልን መሬት ቆርሶ ለአዲስ አበባ እንደማይሰጥ፣ ዓላማው በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች መካከል ተመጋጋቢ ልማትን ማምጣት የሚቻል መሆኑን የሚያስገነዝብ ቢሆንም፣ በይበልጥ ግን ትኩረት እየተሰጠ ያለው ብጥብጡን ያነሱት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን ማየት የማይፈልጉ ወገኖች ስለመሆናቸው የሚገልጽ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች ገልጸዋል፡፡

በአምቦ፣ በጉደርና በአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያነጋገሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ይህንኑ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲያንፀባርቁ ተስተውለዋል፡፡ በውጭ ኃይሎች የተጠመዘዘ ተቃውሞ መሆኑን የተናገሩት አቶ አባዱላ፣ የኦሮሞ ተወላጅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሆኑ ነዋሪዎች በጉዳዩ ላይ ማንኛውንም ጥያቄ የማንሳትና ምላሽ የማግኘት መብት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ማስተር ፕላኑ በሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት ካልቻለ ተግባራዊ እንደማይደረግ ፍንጭ የሰጡት አቶ አባዱላ፣ ‹‹በሕዝብ ተቀባይነት ያላገኘ ጉዳይን አንፈጽምም፡፡ ይህንን ሕዝቡም ሆነ ኦሕዴድ ያውቁታል፡፡ ኦሕዴድ የሚመራው መንግሥትም ያውቀዋል፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ ዕለት የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ የሐዲድ ዝርጋታን ለማስጀመር በድሬደዋ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ከድሬዳዋ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር መክረዋል፡፡

ከኦሕዴድ አመራሮች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምክንያት ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹አገሪቱን የመገነጣጠል ፍላጎት ያላቸው ወገኖች የቀሰቀሱት ብጥብጥ ነው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በማስተር ፕላኑ የተደናገሩ መኖራቸውን በመገንዘብ ‹‹ይችን አጋጣሚ እንጠቀም›› ያሉ የውጭ ኃይሎች ብጥብጡንና ተቃውሞውን እንደቀሰቀሱ አስረድተዋል፡፡

‹‹ተማሪዎችን በሚገባ እናስረዳለን፣ የጠላትን ሴል አንድ በአንድ ለይተን መልክ እናስይዛለን፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ባደረጉት ጥረት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ብጥብጦች መርገባቸውን አንድ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸው፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ከተማሪዎች ጋር በስፋት ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሒደትም እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

በሁከቱ ምክንያት በሰው ሕይወት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ መንግሥት 11 ሰዎች መሞታቸውን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

No comments: