Friday, May 30, 2014

ግንቦት 20- የመከራ የስደትና ዘረኝነት አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ

May 30/2014

























ወያኔ ለንግሥና የበቃበትን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓመተ ምህረት መታሰቢያ በአል ለ23ኛ ጊዜ ለማክበር ሰሞኑን ደፋ ቀና ሲል ሰንብቷል። በኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ህዝብ የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የውጪ አገራት የተመደቡ የወያኔ ቆንስላ ጽ/ቤቶች በዚሁ የግንቦት 20 በአል አከባበር ሥራ ተጠምደው ከርመዋል። ለኢትዮጵያ አገራችንንና ለህዝቦቿ ባርነትን ለህወሃትና ለግብረ አበሮቹ ደግሞ አልመውት የማያውቁትን ድሎትና ብልጽግናን ያጎናጸፈው ግንቦት 20 በየአመቱ ሲዘከር ልብ ልንላቸው ከሚገቡ በርካታ ትሩፋቶቹ ጥቂቶቹ ማስታወስ ይችላል፦
  1. ኢትዮጵያ አገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአብራኳ በተገኙ ከሃዲዎች መዳፍ ውስጥ ወድቃ ሉአላዊነቷና አንድነቷ የተናጋበት ሁኔታ መፈጠሩ፤
  2. በዘመናት ጥረት የተቋቋመው ህብረ ብሄር የአገር መከላኪያ ሠራዊታችን ፈርሶ በምትኩ ለጠባብ የዘውግ ጥቅም የተሰባብሰቡ መንደርተኞች ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት ተቋም መመስረቱ፤
  3. በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት አገራችንን ከውጪ ጠላት ተከላክለው ነጻነት ያወረሱን ጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ እየተብጠለጠለ በታሪካችን እንድናፍር መደረጉ፤
  4. ዜጎች በብሄር ማንነታቸው ከመንግሥት ሥራና የግል ይዞታ የሚፈናቀሉበት ዘመን መፈጠሩ፤
  5. የመንግሥትና የህዝብ ሃብት የነበሩ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ተቋሞች በሙሉ ወደ ህወሃት የግል ይዞታነት መዛወራቸው፤
  6. የዘር የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት መስፈርት የሆነበት ሥርዓት ተቋቁሞ ዜጎች እርስ በርስ የሚላተሙበት ፤ ለዘመናት በሰላም ከኖርበት ቀያቸው በነቂስ የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ደጋግሞ መከሰቱ፤
  7. በልማትና እድገት ሥም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቻችን ለህንድ፤ ለቻይናና ለአረብ ከበርቴዎች በመቸብቸቡ የነገው ትውልድ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ውስጥ እንዲወድቅ መንገዶች መመቻቸታቸው፤
  8. በሚሊዮን የሚጠጉ ለጋ ወጣቶች ተስፋቸው ተሟጦ ለአሽከርነትና ለግርድና ወደ አረብ አገር የሚፈልሱበት ችግር እየተባባሰ መምጣቱ፤
  9. በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ስደትና እንግልት ሰለባ መሆናችን ወዘተ
  10. ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ተጥሶ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው በእስር ቤት እንዲማቅቁ፣ እንዲገደሉና እንዲሰደዱ ተደርገገዋል ።
ወያኔ ሰሞኑን ባወጣው “የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ” የግንቦት 20 ድል በሀገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረውን የዓፈናና የጭቆና ስርዓት የተወገደበትና በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ፅኑ መሰረት የተጣለበት ፣የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በተለይ ደግሞ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የማረጋገጥ ቁልፍ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበትበመሆኑ ልዩ ቦታና ክብር ይሰጠዋል። የግንቦት 20 ድል ሀገራችን ተደቅኖባት የነበረውን የመበታተን አደጋ በመታደግ የኋልዮሽ ጉዞዋን በአስተማማኝ ሁኔታ በመቀልበስ ድሮ ወደነበረችው የስልጣኔ ማማዋ ለመመለስ የሚያስችል በህዝቦች ይሁንታና መከባበር ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የተጣለበት የህዳሴአችን ጮራ የፈነጠቀበት የድል ቀን ነው።” ብሏል።
ይህንን መግለጫ እንዳነበብን ወይም እንደሰማን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሰን እንድንጠይቀው ግድ ይለናል።
  • በአገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው አፈናና ጭቆና ደጋግመህ እንደምትነግረን ተወግዶአል ለማለት የአንድ ብሄር የበላይነት የሰፈነበት መከላከያ ሠራዊትህ መላው አገሪቱን በመቆጣጠር በአሶሳ፤ በአርሲ፤በሃረር ፤ በኦጋዴን ፤ በጋምቤላ ፤ በአዋሳ፤ በዋካ፤ በአረካ ፤ በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ፤ በጎንደር፤ በአዲስ አበባና በሌሎችም በርካታ ቦታዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸማቸው ግዲያዎች፤ እስርና እንግልት በምን ቋንቋና መስፈርት ነው በቀድሞ ስራዓቶች ከተፈጸሙት ተሽለው የተገኙት?
  • የደህንነት ሃይሎችህ በዜጎች ላይ የሚወስዱት ዘግናኝ እርምጃዎችና አብዛኛውን ህዝብ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የከተተው አንድ ለአምስት ጥርነፋህ እንዴት ተደርጎ ነው የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብቶች ግንባታ ጽኑ መሠረት የሆነው?
  • ትናንት በበረባሶ ጫማ አዲስ አበባ የዘለቀው ወታደርህና ቤሳ በስቲን ያልነበራቸው መሪዎቹ ዜጎችን ከቄያቸው በማፈናቀል በተቀራመቱት የከተማ ቦታዎች የጦፈ ንግድና በጨበጥከው የመንግሥት ሥልጣን በተመቻቸ ዘረፋ የገነቡት የንግድ ድርጅቶች፤ ህንጻና ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች በተገኘ ገንዘብ የተሠሩ መንገዶች እንዴት የዲሞክራሲና የልማት መሠረት ሊሆኑ ይችላሉ ?
  • በምስሌኔዎችህ የምታስተዳድራቸው ብሄር ብሄረሰቦች የእጅ አዙር አገዛዝህን አንፈልግም በስማችን አትነግድብን እያሉህ ከትውልድ መንደርህ ጀምሮ ነፍጥ እያነገቡ እያየህና እየሰማህ ስለየትኛው የብሄር ብሄርሰብ እኩልነትና ነጻነት ነው የምትደሰኩረው?
  • ከውጭ በተገኘ የመሳሪያና የትጥቅ ድጋፍ የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ለማስገንጠል 17 አመት ሙሉ አገራችንን የወጋህ አንተው ሆነህ እያለህ ከየትኛው የአገር መበታተን አደጋ ነው እንደታደከን መላልሰህ እየነገርክ የምትደነቁረን ?
  • የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ነው በማለት የኩራት መሠረታችንን ስታፈርስ ከኖርክና በተለይ አዲሱን ትውልድ ታሪክ አልባ አድርገህ ካበቃህ ቦኋላ በየትኛው ዘመን ወደነበረው የሥልጣኔ ማማ ልትመልሰን ነው ባለ አዲስ ራዕይ የሆንክልን ?
” ጆሮ ለባለቤቱ …” እንዲሉ እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ ወያኔ እንደለመደው ” የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች ፤ጸረ ሠላምና ጸረ ልማት ሃይሎች ፤ የብሄር ብሄረሰብ መብት የማይዋጥላቸው የአማራ ትምክህተኞች ፤ የኤርትራ የጥፋት መልዕክተኞች ፤ ሽብርተኞች” የሚሉ አራምባና ቆቦ የሆኑ መልሶችን እንደሚሰጥ መጠራጠር አይቻልም። የወያኔ ታሪክ ሁሌም የክህደት፣ የውሸት፣ የማስመሰል እና የማጭበርበር መሆኑን ሁሉም ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በየአመቱ የሚያከብረው ግንቦት 20 ደርግ የንጉሰ ነገሥቱን ዘውድ ገርስሶ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ ተገፍቶ ከስልጣን እስከወደቀበት ዕለት ድረስ ያከብረው ከነበረው መስከረም 2 የተለየ ነው ብሎ አያምንም። ወያኔ ደርግን በሃይል ከሥልጣን የገረሰሰበትን ግንቦት 20ን በመስከረም 2 እንደተካው ሁሉ ህዝብ ለነጻነቱ የጀመረው ትግል ተጠናክሮ ወያኔን በሃይል ከሚቆጣጠረው ሥልጣን ሲያሽቀነጥረው የግንቦት 20 በአከባበርም አብሮት እንደሚያከትም ነጋሪ አያሻውም። ህዝብ በዘር በተሰባሰቡ ባንዳዎች መዳፍ ውስጥ የገባበትን ዕለት ፤ብሄራዊ ኩራቱንና ማንነቱን የተነጠቀበት ቀን፤ በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች የሆነበትን የወያኔ የድል ቀን መልሶ የሚዘክርበት ምክንያት አይኖረውም። ወያኔ በየአመቱ የሚያከብረው ግንቦት 20ንና የድል ፍሬዎቹን ህዝብ እንደማይጋራው ግንቦት 7 ቀን 1997 ህዝብ በግልጽ ተናግሯል።
የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና የትግል አላማ ነጻነት ናፋቂው የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ግንቦት 7 ቀን 1997 ያስመዘገበውን ድል መልሶ እንዲቀዳጅ ማድረግ ነው። ስለዚህም ሰላም ፍትህና እኩልነት የተጠማኸው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ፤ በገዛ አገርህ ሠርቶ የመኖር ተስፋህ ተሟጦ ለስደት በባህርና በየብስ ለማምለጥ እያኮበኮብክ ያለህ ወጣት፤ በየስፍራው የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ ለማፈን እየተላክ ከገዛ ወገንህ ጋር ደም እየተቃባህ ያለኸው ወታደር፤ የገዥዎችን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም በፖሊሲ ሃይል፤ በደህንነትና ጸጥታ ጥበቃ የተሰማራሃው ወገን ፣ ግንቦት 7 የጀመረው የነጻነት ትግል እናንተንም ጭምር ከአፈናና ከጉስቁልና ነጻ ለማውጣት ስለሆነ ዛሬውኑ ትግሉን ትቀላቀሉ ዘንድ ድርጅትህ ግንቦት 7 ወገናዊ የትግል ጥሪውን ያቀርብልሃል።
የግንቦት 20 ድል መቀሌ ውስጥ የአፓርታይድ ሠፈር የገነቡ የሥርዓቱ ቅምጥሎች ፤ አዲስ አበባ ውስጥ የመቀሌ ሠፈር ተብሎ የተሰየመውን ህንጻ ያሳነጹ ሌቦች ፤ በጋምቤላ፤ በአፋር፤ በቤነሻንጉልና ማሃል ኦሮሚያ የእርሻ መሬት እየዘረፉ የተቀራመቱ ህወሃቶችና የጥቅም ተካፋዮች እንጂ የሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አለመሆኑን በተግባር ለማሳየት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የወያኔን የአገዛዝ ሥርዓት ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን ለመጣል ከምንጊዜውም በላይ መነሳት ያለብን ጊዜው አሁን ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments: