Sunday, May 4, 2014

አራት የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላት ታሰሩ

May 3/2014-
ርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)አራት ከፍተኛ አመራሮች ሚያዝያ 22 እና 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸው ታወቀ፡፡ ሁለት አመራሮች በ1,500 ብር ዋስትና መለቀቃቸውም ተገልጿል፡፡ 
አንድነት ሚያዝያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሚያደርገው ሰላማዊ ሠልፍ ለቅስቀሳ ወጥተው የነበሩት የፓርቲው የአዲስ አበባ ልዩ ዞን ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባልና የምክር ቤቱ አባል አቶ ዘለዓለም ደበበ፣ እንዲሁም የፓርቲው ልሳን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ነብዩ ኃይሉ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ተይዘው መታሰራቸውን፣ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ልዩ ዞን የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

ሦስቱም ግለሰቦች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መታሰራቸውን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡

በመሆኑም ፖሊስ አባላቱ ፈቃድ ሳይዙ በሕገወጥ መንገድ ሲቀሰቅሱና ሲረብሹ መገኘታቸውን ገልጾ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት 11 ቀናትን መጠየቁን አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡ የታሰሩት የፓርቲው አባላት ለቅስቀሳ የወጡት፣ ለአስተዳደሩ አሳውቀውና ይሁንታ አግኝተው መሆኑን ቢያስረዱም፣ ፖሊስ ፈቃድ ያገኙት ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እንጂ ለቅስቀሳ አለመሆኑን በማስረዳት የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ሲጠይቅ ጊዜው እንደተፈቀደለት አስረድተዋል፡፡ ከፓርቲው አመራሮች ጋር የተከራዩት የመቀስቀሻ ተሽከርካሪ  ከነሾፌሩ የታሰሩ ቢሆንም፣ ተሽከርካሪው 500 ብር ተቀጥቶ ሲለቀቅ ሾፌሩ ግን መታሰሩን አቶ ሀብታሙ አክለዋል፡፡

ሌላው የፓርቲው አባላት በቅስቀሳ ላይ እያሉ የታሰሩት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብታሙ አባላቱ አቶ አሸናፊ አሳመረ፣ አቶ ኤፍሬም ሰለሞንና አቶ ስንታየሁ ቸኮል እንደሚባሉ ገልጸዋል፡፡

እነሱም የታሰሩት በቅስቀሳ ላይ እያሉ መሆኑን የገለጹት ሕዝብ ግንኙነቱ በአካባቢው ባለው ፍርድ ቤት ቀርበው በፖሊስ ጣቢያ አካባቢ የቅስቀሳ ፈቃድ ሳይዙ ሲቀሰቅሱ ፖሊስ ማግኘቱን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና የማይከለክል መሆኑን በመግለጽ፣ እያንዳንዳቸው 1,500 ብር ከፍለውና የራሳቸውን መታወቂያ ኮፒ አስይዘው እንዲፈቱ ማዘዙን ተናግረዋል፡፡

No comments: