Wednesday, May 7, 2014

“ሰልፉ የተካሄደው በእኛ ትዕግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግሥት አልተፈለገም” ”

May 7/2014
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታዩ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ላይ ያተኮረ “የእሪታ ቀን” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። ሰላማዊ ሰልፉ ከተከናወነ በኋላ የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራውን አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ (ሚያዚያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም) የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ምን ያህል የተሳካ ነበር?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ሰልፉ እንዳይካሄድ ከነበረው ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ አንፃር ከፍተኛና ስኬታማ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር።
ሰንደቅ፡- ሕብረተሰብ ውስጥ አለ ካላችሁት ችግር አንፃር እንደምትጠብቁት በቂ የሆነ ሕብረተሰብ በሰላማዊ ሰልፉ ወጥቷል የሚል እምነት አላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ካለው ሁኔታ አንፃር አዎ። አንደኛ ለመቀስቀስ ዕድል አልሰጡንም። የሰላማዊ ሰልፉን እውቅና ያገኘነው በእኛ ትዕግስት እንጂ እውቅናውን መስጠት አልፈለጉም። ከሕግ ውጪ በሆነ መልኩ ሰልፉን ለማካሄድ ማንም ሰው መፈረም ቢችልም አመራሩ ካልፈረመ እውቅና አልሰጥም አሉ። ሶስት የፓርቲ አመራሮች ሄደው ፈረሙ። እኔ በአጋጣሚ በማኅበራዊ ጉዳይ ሀዘን ላይ ስለነበርኩ እሱም ካልመጣ በመባሉ ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ እኔ አራተኛ እንድፈርም ተደርጓል። በእርግጥ የእኔ መፈረም ችግር አይመስለኝም። ነገር ግን ህግ የማክበር ጉዳይ አይደለም። ጊዜ የማጣበብ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጎንለጎን ለቅስቀሳ የወጡ አባሎቻችንን አሰሩብን። እውቅና ያለው ሰልፍ መሆኑን እያወቁ አባሎቻችንን አሰሩ። ለምሳሌ የፓርቲያችን የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ኃይሉ ታስሯል። እንደዚሁም ዘላአለም የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ታስሯል። ከዚህ አንፃር ስታየው ሰላማዊ ሰልፉ ስኬታማ ነበር።
ሰንደቅ፡- የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አጋርነታችሁን በሰልፉ ላይ ለመግለፅ ሙከራ ቢያደርጉም መከልከላቸውን ገልፀዋልና ለምን ተከለከሉ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ማንም ሰው አልተከለከለም። በእርግጥ እኔን አላገኙም። ነገር ግን በኋላ ሳጣራ ማንም ኢትዮጵያዊ በዚያ ሰልፍ መሳተፍ የእኛ ፍላጎት ነው። ነገር ግን እንደሰማሁት የእነሱን (የሰማያዊ ፓርቲ ማለታቸው) ቲሸርት የራሳቸውን አርማ ይዘው ለመካፈል ሞክረዋል የሚል ነው። እነሱ ሰልፍ ባካሄዱ ጊዜ የእኛ አባሎች የእነርሱን አርማና መፈክር ይዘው ነው የተሳተፉት። እና እነሱ የሰማያዊ ፓርቲን በአንድነት ሰልፍ ለማስተዋወቅ ሙከራ ያደረጉ ይመስላል። በእኛ አባላት በኩል ሰልፉ የአንድነት ፓርቲ መሆኑን በመግለፅ መፈክሩም፣ አካሄዱም በአንድነት ፓርቲ የሚመራ መሆኑ ተነግሮአቸዋል። ይሄ ደግሞ ትክክል ነው። በእኛ በኩል ሁሉም መፈክር ላይ ማህተም አድርገናል። ከዚያ ውጪ ያለው መፈክር እኛን እንደማይወክል ቀደም ብለን ሰርተናል። ባጅም አድለናል። እና ሰልፉ የሌላ ፓርቲ ማስታወቂያ ወይም መፈክር ማቅረቢያ አይደለም። በተጠየቅ (logic) ብታየውም ሁሉም የሰልፉ አካሄድ የአንድነት መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ሰንደቅ፡- በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል እንደተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ ያለው ግንኙነት ጤናማ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኔ እንደማስበው ይሄ ለጥያቄ የሚቀርብ አይመስለኝም። በእኛ በኩል በራሳችን ትዕግስት ሁሉንም ፓርቲ የምናየው በእኩልነት ነው። ከሁሉም ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራት በራችንን ከፍተናል። ከዚያም አልፎ የእኛ አላማ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ነው። እንግዲህ እነሱ በዚህ ላይ ይስማሙ አይስማሙ እነሱን መጠየቁ ይሻላል። አንድነት ግን ከሁሉም ፓርቲ አብሮ ለመስራት እስከውህደት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። 
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ቀጣይ አቅጣጫችሁ ምንድነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እሁድ እለት የተካሄደው ሰልፍ እራሱን የቻለ የአዲስ አበባ የፓርቲው መዋቅር ያዘጋጀው ነው። ይህንን እንደ ትልቅ መዋቅር ነው የምናየው። ከአዲስ አበባ ውጪም በሲዳማ እና በምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዳማ ይኖረናል። እነዚህ አካላት በራሳቸው አየጠነከሩ የአቅም ግንባታ እንዲያደርጉ በማድረግ እንዲቀጥሉ ነው። ለምሳሌ በደራሼ ጊዶሌ ከተማ በተመሳሳይ እሁድ እለት ሰልፍ ተካሂዷል። ወዲዚያው አንድ የስራ አስፈፃሚ አመራርና የቀጠና አስተባባሪ ልከናል። ወደፊትም ዞኖቹ የራሳቸውን አቅም ገንብተው የማዕከል የፖለቲካ አቅም ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ይካሄዳል። ከዚህ ጎንለጎን የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ አሁን ለመሬትና ለፍትህ እየተካሄደ ነው። በቀጣይ ደግሞ በሶስተኛው ፌዝ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ” መርሀግብር ይኖረናል። ከሰኔ 30 በኋላ የሚጀመር ይሆናል። ይህም ፖለቲካውን ከአንድነት ወደ ሕዝብ የማውረድ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህ ጎንለጎን በስትራቴጂው ዘርፍ አማራጭ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት፣ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የምርጫ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና የአማራጭ ፖሊሲ ትውውቅ ውይይቶች ይካሄዳሉ። በዚህም በአዳራሽ ስብሰባ የተለያዩ ምሁራን በተገኙበት የሚደረግ ይሆናል።
ሰንደቅ፡- ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመዋሃዱ ጉዳይ ያበቃለት ጉዳይ ሆኗል ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ያበቃለት ነገር የሚባል ነገር የለም። በእኛ በኩል ለውህደት ሙሉ በሙሉ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ አንድ ጠንካራ አብይ ብሔራዊ ፓርቲ መፈጠር አለበት ብለን እናምናለን። ውህደትን እንደ ጠንካራ ግብ ስለያዝነው ምንጊዜም ቢሆን የምንቀጥልበት ጉዳይ ነው።
ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑ አንፃር የፖለቲካ ምህዳሩ በምን ደረጃ ላይ ነው ትላላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- የፖለቲካ ምህዳሩ በእጅጉ እንደተዘጋ ነው። ሰልፍ ማካሄድ ወደማንችልበት ደረጃ ነው የደረስነው። የትናንትናውን ሰልፍ ለማካሄድ አንድ ወር ፈጅቶብናል። የሰልፍ እውቅና ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ለፖለቲካ ምህዳሩ አለመስፋት ዋነኛ ምሳሌ ነው። ሕዝባዊ ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ ለማካሄድ አስበን አዳራሽ አጥተናል። የአዲስ አበባ አስተዳደር የሁላችንም አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ካልቻለ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ለሰልፍ አንድ ወር መፍጀት የለበትም። እኛም ታግሰን ሁኔታውን አክብረን እውቅና ሲሰጠን ማየት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን አያሳይም። አሁንም ከሁለት ወር በፊት የጀመርነው የአዳራሽ ስብሰባ በአዳራሽ እጦት ማካሄድ አልቻልንም።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ሰላማዊ ሰልፍ ስታደርጉ አይታይም፤ አሁን ግን ወደ አደባባይ የመውጣቱ ሁኔታ ከመታየቱ አንጻር በፖለቲካ ምህዳር መስፋት በኩል የተሻሻለ ነገር አለ ብለው የሚያምኑ አካላት አሉና እርስዎስ ምን ይላሉ?
     ኢንጂነር ግዛቸው፡- አንተ ማየት ያለብህ ሂደቱን ነው። ሰልፉን በነፃነት እያካሄድን አይደለም። እውቅና ለማግኘት አንድ ወር እየፈጀብህ ምህዳሩ ሰፍቷል ማለት አይቻልም። ሰልፉ በእኛ ትእግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግስት በኩል አልተፈለገም። ሰልፍ ስናካሂድ ብዙ ሰዎች ይታሰራሉ እና ሰልፉ መካሄዱ አይደለም ዋና አላማው፤ ሂደቱ ላይ አሁንም ነፃ አይደለንም። ሂደቱ ላይ አሁንም አፈና ይካሄድብናል። የማስፈራራት ዘመቻው ከፍተኛ ነው። ሚዲያው ሙሉበሙሉ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ሆኗል። እኛን አያስተናግደንም። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ሰልፉን እንደምናካሂድ ማስታወቂያ አዘጋጅተን ሄደን ተከልክለናል። የፍትህ አካላት አካባቢም ችግር አለ። የእኛ አባላት በመኪና ስለቀሰቀሱ ለአስር ቀናት ፖሊስ አሰራቸው። ሕግ አስከባሪውም በሕገ-መንግስቱ መሰረት እየሰራ አይደለም። ነፃ የሲቪል ማህበረሰብ የለም። ያሉትም የኢህአዴግን ቡራኬ ያገኙ ናቸው። እና ከድሮው በጣም ተዘግቷል። ሚዲያው ሚዛናዊ መሆን ሲገባው በእኛ ላይ ፕሮፓጋንዳ ያደርጋል እና ደምረው ስታየው በእጅጉ እየተዘጋ ነው።

No comments: