Thursday, May 15, 2014

ጁነዲን ሰዶ አትላንታ አሜሪካ ገቡ

May 14, 2014

Junedin Sado“ይሄ ፋሽስት መንግሥት!” ማለት ጀምረዋል!

አገር ለቀው የኮበለሉትና የኦሮምያ ፕሬዚዳንትነትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት ማዕረግ ያገለገሉት እንዲሁም የኦህዴድና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሰዶ አሜሪካ መግባታቸውን በዋሺንግተን ዲሲ የሚታተመው ዘ-ኢትዮጵያ የተባለው የአማርኛ ጋዜጣ ይፋ አድርጓል። ኬንያ ለአንድ ዓመት ያህል በስደተኝነት ተቀምጠው የአሳይለም ወረቀታቸውን አግኝተው አትላንታ ከገቡ ሁለት ወራት እንደሆናቸውም የዘኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ ጁነዲን በአባ ዱላ ገመዳ እስኪተኩ ድረስ ከኦክቶበር 28/2001 እስከ ኦክቶበር 6 /2005 የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት ነበሩ። ከዚያም የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር በመሆን እስከ ኦክቶበር 2008 አገልግለዋል። በመቀጠልም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ከሠሩ በኋላ በመጨረሻም በ2010 የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር በመሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን መንግሥት አገልግለዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም የቦርድ ሊቀመንበር ነበሩ። መንግሥታቸው ብዙ ዓመት ከኖሩበት የሚኒስትሮች ካቢኔ ያሰነባታቸው የአቶ ኃይለማርያም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን ሲጀመር ነው።የስደት ኑሯቸውን ማቃናት የያዙት አቶ ጁነዲን ከወዳጆቻቸው ጋር ሲያወጉ “ይሄ ፋሽስት መንግሥት እኮ የሚያደርገውን አያውቅም” በሚል መገረም ሲናገሩ መደመጣቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል። ባለቤታቸው ወ/ሮ ሀቢባ መሀመድ “በሽብር ተግባር ተጠርጥረዋል፣ ከሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና መጽሐፍት ይዘው ሲወጡ ሐምሌ 9 ቀን 2004 እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል” በሚል ተዘውታሪ ሰበብ በእስር መቆየታቸው ይታወሳል። ከሥልጣናቸው በመስመጥ ላይ ለነበሩት አቶ ጁኒዲም ይህ የባለቤታቸው እስር ተጨምሮ ከአገር ለመኮብለል መንስኤ መሆኑ ሲዘገብ መሰንበቱ ይታወቃል።

ባለቤታቸውና ልጃቸው አሁንም በኢትዮጵያ የሚገኙ በመሆኑ አቶ ጁኒዲን በይፋ ምንም አስተያየት ሳይሰጡ ተቆጠበው መቀመጡን መምረጣቸው ተነግሯል። ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል ተማሪዎች ላይ እየደረሰው ያለው ግድያና ሁከት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚመለከታቸው ቢሆንም፣ እንደ ተራ ሰው “ይሄ ፋሽስት መንግሥት ምን እያደረገ ነው” ብለው መገረማቸው መልሶ ማሰገረሙን ምጮቻችን ገልጸውልናል። የኦሮምያ ክልል ፕሬዘዳንት ከነበሩት ውስጥ ሀገር ጥለው የኮበለሉ ፕሬዘዳንቶች ከአቶ ሀሰን ዓሊ ጋር አቶ ጁነዲን ሲደመሩ ሁለተኛ መሆናቸው ነው። ሁለቱም አትላንታ መሆናቸው ሲገለጽ አቶ ጁነዲን በአንድ ዩኒቨርስቲ መምርህነት ሥራ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባታቸውም ተነግሯል።

No comments: